በኢትዮጵያ የመኪናው አምራች ድርጅት ሃገሪቱን ባመሳት የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ በምርት ላይ ችግር እንዳጋጠመው አስታወቀ

March 8, 2016

(ሪፖርተር) የቻይናው ሊፋን ግሩፕ ኩባንያ አካል የሆነው ሊፋን ሞተርስ፣ በአሁኑ ከቻይና እያስመጣ ከሚገጣጥማቸው ባሻገር ሙሉ ለሙሉ እዚሁ የሚመረቱ ተሽከርካሪዎችንና ሞተር ብስክሌቶችን ለመፍበረክ የነበረው ውጥን በውጭ ምንዛሪ እጦት ሳቢያ እየተጓተተበት እንደሚገኝ ገለጸ::

መንግሥት በተለይም ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ላይ ያለበትን ችግር ቢቀርፍለት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሞተር ብስክሌቶችን እዚሁ ለመገጣጠም እንደሚችል የሊፋን ሞተርስ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ማ ኩን (ማርክ) ለሪፖርተር አስታውቀዋል:: ማርክ እንዳብራሩት ከሆነ በኢትዮጵያ ሞተር ብስክሌት ለመፈብረክ የሚያስችል አቅም እንዳለው ቢገልጹም፣ አውቶሞቢሎችን ለመገጣጠም ግን በርካታ መሟላት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ተናግረዋል:: ያልተቋረጠ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ጨምሮ ሌሎች መሠረተ ልማቶች ግብዓቶች በአንድ ጊዜ ተሟልተው መቅረብ እንዳለባቸው አብራርተዋል:: ይሁንና እንዲህ ያሉ አቅርቦቶችን ያለምንም ችግር ሁሉንም በአንድ ጊዜ
ማግኘት ባለመቻሉ እንጂ መኪኖችን ከመገጣጠም ወደ ማምረቱ ለማቅናት ሊፋን ዝግጁ መሆኑን ይገልጻሉ::
የገጠመውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ አማራጭ አድርጎ የወሰደው የተገጣጠሙ መኪኖችን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሆነ የተናገሩት ማርክ፣ በተለይ ወደ ግብፅ ለመላክ የሚያስችሉትን ጥናቶች አጠናቆ ገበያውን ለመቀላቀል መቃረቡን አስታውቀዋል:: የመንግሥት ተቋማትን ጨምሮ ግለሰብ ደንበኞች መኪኖቹን እንደሚገዙት ያስታወቀው ሊፋን፣ በዓመት በአማካይ ከ500 እስከ 1,000 መኪኖችን ገጣጥሞ እየሸጠ እንደሚገኝ አስታውቋል:: ኩባንያው ዱከም ከተማ በሚገኘው የቻይና ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ 20 ሺሕ ካሬ ሜትር የማምረቻ ቦታ በመግዛት ማምረት ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል:: ከሆላንድ ካር ጋር በመኪና አካላት መለዋወጫ

አቅራቢነት አብሮ ሲሠራ ቆይቶ ከስምንት ዓመት በፊት ራሱን ችሎ ወደ መገጣጠሙ ሥራ የተቀላቀለው ሊፋን፣ ከዚያ በፊትም ወደ ኢትዮጵያ ገበያ የመጣው በሞተር ብስክሌት አቅራቢነት እንደነበር ይታወሳል::
ለገበያ ያቀረባቸውን ሁለት አዳዲስ ሞዴል መኪኖች ይፋ ማድረጉን በማስመልከት ሐሙስ፣ የካቲት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በሸራተን ሆቴል ባካሄደው ዝግጅት ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ሊፋን ኩባንያ እስካሁን ኢንቨስት ካደረገው በላይ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ማካሄድ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል:: ኩባንያው ከስምንት ዓመት በፊት ኢንቨስት ያደረገው 1.5
ሚሊዮን ዶላር እንደነበርና በአሁኑ ወቅትም ስድስት ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረጉን ዶ/ር ቴድሮስ አስታውሰው፣ ኩባንያው ሊያካሂድ ይገባቸዋል ያሏቸውን ሦስት አስተያየቶችንም ለኩባንያው ኃላፊዎች አቅርበዋል::
የመጀመሪያውና ኩባንያውም እየሠራበት እንደሚገኝ የገለጸው ወደ ውጭ የመላክ ተግባር ላይ እንዲሳተፍ የጠየቁበት ነው:: እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ሊፋን በቀጣናው ያለውን ገበያ በአንክሮ ሊመለከተው ይገባል:: ለዚህ የሚያመች ዕድል አለ ብለው የጠቀሱትም፣ አገሪቱ የምትገኝበት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ስትራቴጂካዊ በመሆኑ ነው::
ኢትዮጵያ በስምንት ሰዓት የአውሮፕላን በረራ ከ3.5 ቢሊዮን በላይ ሕዝቦችን ለማዳረስ የሚያስችላት አቀማመጥ ላይ የምትገኝ በመሆኗ፣
ለአገሪቱ ከሚያቀርበው ባሻገር ለቀጣናውና ከዚያም በላይ ላለው ገበያ የሚገጣጥማቸውን መኪኖች ማቅረብ እንደሚገባው ጠቁመዋል:: ዶ/ር ቴድሮስ ያቀረቡት ሌላኛው ሐሳብ ኩባንያው በአሁኑ ወቅት አሥር በመቶ እሴት በመጨመር

የሚያመርትበትን አሠራር ይበልጥ እንዲያዳብር፣
የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት የሚያስችለውን
ሚናውንም እንዲያሳድግ የኩባንያውን አመራሮች
እባካችሁ ብለዋል:: በመቀጠልም ‹‹ኢትዮጵያ
ለኢንቨስትመንትና ለኢንቨስተሮች ምቹ የመሆኗን
ዜና ለሌሎች አዳርሱ፣ ወሬውን አሰሙ፤›› በማለት
ጠይቀዋል::
ከዚህ በተጓዳኝም ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት
በማድረግ ትልቅ ድርሻ ከያዙት አገሮች መካከል
ቻይና ቀዳሚ መሆኗን፣ ቱርክ፣ ህንድ፣ ሳዑዲ
ዓረቢያ፣ ኔዘርላንድስና ዩናይትድ ኪንግደም በቅደም
ተከተላቸው ቻይናን በመከተል ከሁለተኛ እስከ
ስድስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙ አገሮች መሆናቸውን
ዶ/ር ቴድሮስ አስታውቀዋል:: የቻይና መንግሥት ‹‹ጎ
ግሎባል›› በሚል ይፋ ያደረገውና አገሮችን ለመደገፍ
ባወጣው ፕሮግራምም በቻይና መንግሥት ቀዳሚ
ትኩረት ከተሰጣቸው አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ
ዋናዋ እንደሆነች አብራርተዋል::
የብረታ ብረትና ኢንዱስትሪና ኢንጂነሪንግ
ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ
ደለለኝ፣ ኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በተለይም
በአውቶሞቢልና በኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች መስክ
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት ጭላንጭል
የሚታይበት ጊዜ ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል::
ይሁንና ይህ ሒደት ገና በእንጭጭ ደረጃ ላይ
ይገኛል ብለዋል::
ሊፋን ሞተርስ ኩባንያ፣ ኢትዮጵያን የአፍሪካ
ማዕከል በማድረግ ፋብሪካ ገንብቶ መንቀሳቀስ
ጀምሯል:: ምንም እንኳ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ
እየጨመረ የመጣ ገበያ ቢኖረውም፣ የጠበቀውን
ያህል ሆኖ እንዳላገኘው ባለፈው ዓመት አስታውቆ
ነበር::
ባለፈው ዓመት ያስተዋወቀውን ሊፋን 530
ሞዴል መኪና ውስጥ አሥሩን ለገዥዎች ባስረከበበት
ወቅት፣ በኢትዮጵያ ሊፋን ሞተርስን በሚያካትተው
ያንግፋን ሞተርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ
ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊዩ ጂያንግ እንዳስታወቁት፣
ሊፋን ሞተርስ በአፍሪካ ለሚኖረው የመኪና ገበያ
ኢትዮጵያን ቀዳሚ ምርጫው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ
ቢሆንም በገበያ ችግር ምክንያት ኢትዮጵያን
የጠበቀውን ያህል ሆና አላገኛትም:: ገበያው ባገለገሉ
ተሽከርካሪዎች ጫና ውስጥ በመሆኑም ሳቢያ
አዳዲስ መኪኖችን የሚገጣጥሙ ኩባንያዎች ጫና
ውስጥ ወድቀዋል:: ይህንን መኪና በመጀመሪያ ዙር
እስከ አንድ ሺሕ የሚደርስ ብዛት ለአዲስ አበባ
የታክሲ ባለንብረቶች ማኅበር ለማቅረብ ስምምነት
ማድረጉን ምክትል ሥራ አስኪያጁ ለሪፖርተር
በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል::
በየዓመቱ ከአንድ ሺሕ ያላነሱ መኪኖችን
የሚሸጠው ሊፋን፣ ገበያው ውስጥ ከሚታየው
ያገለገሉ መኪኖች ገበያ ባሻገር፣ በሎጂስቲክስ፣
በትራንስፖርትና በታክስ ወጪዎች ጫና እየደረሰበት
እንደሚገኝም አስታውቋል:: ገጣጣሚ ኩባንያዎች፣
ለገቢ ዕቃዎች ከ60 እስከ 70 በመቶ ያህል ግብር
የሚከፍሉ ቢሆንም፣ በተጨማሪ እሴት ታክስና
ኤክሳይስ ታክስ ምክንያት አስመጪዎች ከሚከፍሉት
እኩል እንደሚሆንና ይህም ለዘርፉ የተሰጠውን
ማበረታቻ እየቀነሰው መምጣቱን ይገልጻሉ::
በዕቅድ ደረጃ በዓመት አምስት ሺሕ
ተሽከርካሪዎችን እዚሁ ገጣጥሞ ለገበያ የማቅረብ
ሐሳብ እንዳለው ያስታወቀው ሊፋን፣ በሌሎች
አገሮች ውስጥ ያለው ዓመታዊ የመኪና ሽያጭ
መጠን ከመቶ ሺሕ በላይ በመሆኑ የኢትዮጵያ
እንቅስቃሴው ከሚጠብቀው በላይ ዝቅተኛ ሆኖ
እንዳገኘው ደጋግሞ ገልጿል::
ወጣት ቢንያም መንገሻ የሊፋን ሞተርስ የገበያና
የሽያጭ ኃላፊ ናቸው:: አቶ ቢንያም፣ የኩባንያው
የሽያጭ መጠን በየጊዜው እየጨመረ ቢመጣም፣
በአገር ውስጥ የሚታየው ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች
ከፍተኛ ተፈላጊነት ሳቢያ የአዲስ መኪኖች ገበያ ላይ
ችግር ይታያል ብለው ነበር::
ይሁንና በዚህ ዓመት ሁለት ተጨማሪ አዳዲስ
ሞዴሎችን እዚህ ገጣጥሞ ለገበያ ማቅረቡን ይፋ
አድርጓል:: ሊፋን X-50 እንዲሁም ሊፋን L-7
የተባሉትን ዘመናዊ አውቶሞቢሎች በ550 ሺሕ
ብር ተመሳሳይ ዋጋ ለገበያ ማቅረቡን ኩባንያው
አስታውቋል::
Previous Story

አገር በሕወሓት ቀጥተኛ አገዛዝ ስር

mengistu hailemariam
Next Story

የአሜሪካ አከራካሪና አስተዛዛቢ አቋም – በአጼ ሀይለስላሴ፣ በደርግና በወያኔ ዘመን | ከኤርትራ መገንጠል በፊትና በኋላ (ልዩ ዘገባ)

Latest from Blog

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ | ስለአማራ ክልል ከነዋሪዎች የተሰማው | አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል” | “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል”| “እጅ ከመስጠት ውጭ አማራጭ አይኖረንም” ፊ/ማ “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |

ከውጭ በተላከ ገንዘብ ሀብት አፍርቶ የተላከበትን ደረሰኝ ያላቀረበ ንብረቱ እንዲወረስ የሚደነግግ አዋጅ ቀረበ

ዮሐንስ አንበርብር በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ ንብረት የመውረስ ድንጋጌም በአዋጁ ተካቷል አዋጁ የሚፀድቅ ከሆነ 10 ዓመት ወደኃላ ተመልሶ ተፈጻሚ ይሆናል ከውጭ በተላከ ገንዘብ ሀብት አፍርቶ የተላከበትን ደረሰኝ ያላቀረበ ሰው ወይም ሊታወቅ ከሚችል ገቢው በላይ ሀብት አፍርቶ ምንጩ ሕጋዊ መሆኑን ማረጋገጥ ያልቻለ ሰው፣ ንብረት በመንግሥት እንዲወረስ የሚፈቅድ ድንጋጌ የያዘ
Go toTop