አድዋ የድል አምባ (ተፈራ ድንበሩ)

 

አውሮፓ አርግዞ ለመውለድ ፋሽት

ሲሰላ ዘመኑ ሲያምጥ የቆየበት

12 ዓመቱ በሰማኒያ ስምንት።

ጣልያን ቢቀላውጥ ከምኒልክ ቤት

እቴጌ ጣይቱ ፊት ነሥተውት

ውሀ አጠጥተው አፈር አስበሉት።

ፒያትሮ ቶሴሊ እና ባራቴሪ

ባለጥቁር ሸሚዝ ምንደኛ አስካሪ

ሊደፍሩሽ አልቻሉም አገራችን ኩሪ

የድል አምባ አድዋ ዘለዓለም ክበሪ።

ሐዲያ፣ ሲዳማ፣ ቦረና  ኮንሶው

ወላይታ፣ ቤንች፣ ጉጂና ዶርዜው

አማራ፣ ኦሮሞ፣  ሽናሻ፣  ጉራጌው

ሶማሊ፣  አፋር፣  ጉሙዝ፣  ጋምቤላው

ከምባታ፣ አደሬ፣  አርጎባ፣ አገው

ኧረ ማንስ ቀርቷል ደም ያላፈሰሰው?

ከፋ፣ ኩሎ ኮንታ፣ ጌዲዮ ቡርጂው

በአጥንታቸው ማገር ጊድጊዳ ሠርተው

ባንድ ላይ ተባብረው ምሰሶ አቁመው

ኢትዮጵያን ያቆዩን ሁሉም በኅብረት ነው።

ያፄ ካሌብ አገር የነአምደጽዮን

ያፄ ዘርዓ ያዕቆብ የቴዎድሮስን

የዶጋሊ አርበኛች የነአሉላን

የመተማው ሰማዕት ያፄ ዮሐንስን

የጣይቱ ብጡል ያፄ ምኒልክን

የአቡነ ሚካኤል ያቡነ ጴጥሮስን

የጎበናን አገር የነገበየሁን

የበቀለ ወያ የአብዲሳ አጋን

የዳንኤል አበበ የአሞራው ውብነህን

ሸዋረገድ ገድሌ የነአብቹን

የባልቻ አባነፍሶ የገረሱ ዱኪን

የኃይለማርያም ማሞ የበላይ ዘለቀን

የነአበበ አረጋይ የጃጋማ ኪሎን

የመንሥቱ ንዋይ የሙሉጌታ ቡሊን

ባንዳ አያጠፋውም በደም የቆየውን።

በደም ያለሙትን እነ ባሐታ ሐጎስ

እንክርዳዱን ዘርተው እነ ባሻ አስረስ

ይፈታተኑናል እስከዛሬው ድረስ።

የአድዋ ገበሬ ጀግና አገር ወዳድ

በቅሎበት አይቀርም በማሳው እንክርዳድ

ነቃቅሎ ያርማል ያጠፋል ከሁዳድ።

በቋንቋ በቀለም አገር መከለል

በነፃ እንዳንኖር በመቀላቀል

ተፈጥሮን ለማገት እድገት መከልከል

ኅብረትን ማጥፋት ነው እንዳንደግም ድል።

አገር ሲጠባበቅ ለወረት በተርታ

በወንድማማቾች የቁማር ጨዋታ

በእህትማማቾች የካርታ ጨዋታ

አሸናፊ አይኖርም ማንም ማን ቢረታ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጠቅላዩ ሹመቶች፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ተሰበሰበ፣ ከትግራይ ወደአማራ ገባ የጠባለው መሳሪያ | ፋኖ የመጨረሻ ክተት አወጀ

ብዙ እምነት ቢኖርን ቢለያይ ቋንቋችን

አንድ ቤተሰብ ነን ተዋህዷል ደማችን

እንኮራባታለን በጋራ እናታችን።

የአድዋ ባለቤት መላው ሕዝብ ነው

ምንም ቢዥጎረጎር እምነት የማይለየው

ተወራራሽ ቋንቋ ያስተሳሠረው

ባህሉን በመካፈል ያወራረሰው

በዘር ተቀያይጦ የተዋለደው

መለያው ኢትዮጵያ ማንም አይደፍረው።

አድዋ አንቺ ነሽ ክብሬ

እቆምልሻለሁ ከጎሬ

ወለጋ፣  ጎጃም፣ ጎንደሬ

ከፋ፣  ሲዳማ፣  አደሬ

ከባሌ፣ ከፋ፣ ሐረር፣ ትግሬ

ከ ወንድም እህቶቼ ተባብሬ

ጅረት፣  ተራሮች ተሻግሬ

እደርስልሻለሁ በየትም ዞሬ

ባንቺ ነው ከቶ መታፈሬ

እናት ኢትዮጵያ አገሬ።

 

 

 

Share