ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ላልተወሰነ ጊዜ ወደ ቃሊቲ ተዛወረ

(ነገረ ኢትዮጵያ) በሽብርተኝነት ክስ ጥፋተኛ ነህ ተብሎ የአስራ አራት አመት እስር የተፈረደበት ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በእስር ከሚገኝበት የዝዋይ እስር ቤት ላልተወሰነ ጊዜ ወደ ቃሊቲ ተዛወረ፡፡

የጋዜጠኛ ውብሸት ባለቤት ወ/ሮ ብርሃኔ ተስፋዬ ለነገረ ኢትዮጵያ እንደገለጸችው ውብሸት ከዝዋይ ወደ ቃሊቲ ከተዛወረ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ‹‹ሆኖም ግን ብዙ ሰዎች ውብሸት ወደ ቃሊቲ መዛወሩን መረጃው የላቸውም›› ያለችው ወ/ሮ ብርሃኔ፣ ‹‹አሁን ውብሸት ቃሊቲ በፊት ለፊት በር በኩል ዋይታ ቤት በሚባለው በኩል ይገኛል፡፡ ከሰኞ እስከ አርብ ሙሉ ቀን ሊጠይቀው የፈቀደ ሁሉ መጠየቅ ይችላል›› ብላለች፡፡

ውብሸት ወደ ቃሊቲ የተዛወረበት ምክንያት የቤተሰብ ጉዳይ ስላለበት መሆኑን የጠቀሰችው ወ/ሮ ብርሃኔ ባለቤቷ ቃሊቲ የሚቆየው ላልተወሰነ ጊዜ መሆኑን ገልጻለች፡፡ ‹‹እስከ መቼ ቃሊቲ እንደሚቆይ ባላውቅም መስከረም 29 ቀጠሮ ስላለው እስከዚያው በዚሁ እንደሚቆይ እገምታለሁ›› ብላለች፡፡
ጋዜጠኛ ውብሸት የአንድ ልጅ አባት ሲሆን ቀደም ሲል ዝዋይ እስር ቤት እያለ ልጁን ለማየት ፈተና እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ‹‹አሁን ለጊዜውም ቢሆን ልጃችንን ይዠ ስለምጠይቀው ልጁን ቶሎ ቶሎ ማየት ችሏል›› ስትል ወ/ሮ ብርሃኔ ለነገረ ኢትዮጵያ ተናግራለች፡፡
የውብሸት ልጅ ፍትህ ውብሸት ይባላል፡፡ ይህ ህጻን ‹‹እኔም ሳድግ እንደ አባቴ እታሰራለሁ?›› ሲል መጠየቁ ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ በእስር ቤት ሆኖ የጻፈው ‹‹የነጻነት ድምጾች›› መጽሐፍ ለንባብ መብቃቱን ባለቤቱ ወ/ሮ ብርሃኔ ገልጻለች፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የዛሬዋ ኢትዮጵያና የነገ ውሎዋ - አንዱ ዓለም ተፈራ

2 Comments

  1. እንደ ሻማ እየነደዱ ለሕዝብ ነፃነት ተሟጋችና የአገር ዓንድነት ጠባቂ በመሆን፥
    የሕዝቦች መብት ተከብሮ እንዲኖር በማለምና በአገራችን ሰላም እንዲሰፍን በግንባር ቀደም ወጥተው የግፍን በትርና የመከራን ፅዋ በጨካኙ የወያኔ መንግሥት ከሚጋቱት ውስጥ አንዱ ጀግናችን ውብሸት ታዬ ነው፦
    ይህ ሰውና ቤተሰቡ ለነፃነት የሚከፍሉት ዋጋ እጅግ ብዙ ነውና፥
    ለእርሱ ብርታትን ፣ ለባለቤቱ ጽናት፣ ለልጁ ፀጋና የእግዚአብሔር ከለላ እንዲበዛላቸው እመኛለሁ፦
    ወጣትዋ ጋዜጠኛ እርዮት ዓለሙ ፣ አይበገሬው እስክንድር ነጋ፤ ጀግናው ዓንዱዓለም አራጌ፣ ታዋቂው መምህር በቀለ ገርባ ፣ ናትናኤል መኮንን ፣ ኦልባና ለሌሳ፣ የፌስቡክ ወዳጄ አብርሃ ደስታ፣ ሃብታሙ አያሌው እና የዞን 9 ጦማርያን፥ አረ ስንቶቹን ልጥራ፥ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፥
    የምታልፉበት የጨለማ መንገድ ባንጋራችሁም መቸም ቢሆን ውለታችሁን አንረሳውም ፦ እንወዳችኋለን፥

Comments are closed.

Share