ሰማያዊ ፓርቲ፤ ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት ውዝግብ ውስጥ ይገኛል

ሰንደቅ ጋዜጣ

ጋዜጣው ሪፖርተር

ሰማያዊ ፓርቲ የመመስረቻ ጉባኤውን ካካሄደ ጀምሮ ምንም አይነት ጉባኤ ባለማካሄዱ በሥራ አስፈፃሚውና ቅሬታ ባቀረቡ የምክር ቤት አባላት መካከል ውዝግብ መነሳቱን የሰማያዊ ምክር ቤት አባላት ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅር ይልቃል ለሁለት አመት በጠቅላላው ጉባኤ ፊት ቀርቦ አልተገመገመም። ጠቅላላ ጉባኤም ምክር ቤቱ እንዲጠራ አላደረገም። አሁንም የጠቅላላ ጉባኤው እንዳይጠራ ከፍተኛ ተፅዕኖ በሥራ አስፈፃሚው እየተደረገ መሆኑን ይገልፃሉ።

የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ስለሺ ሰይሳ በበኩላቸው “ጠቅላላ ጉባኤ መጠራቱ ችግር የለውም። አጠራሩ ላይ ግን ቴክኒካል የሆኑ ጉዳዮች ግልጽ መሆን አለባቸው። በጠቅላላ ጉባኤው መሳተፍ የሚችሉት ፓርቲው ሲመሰረት በመስራች ጉባኤው ላይ ተሳታፊ የሆኑ መቶ ሃያ ሁለት አባላት ብቻ ናቸው። የጉባኤ አባላቶች የስራ ዘመን ሶስት አመታት ብቻ ነው። ከዚህ ቀድሞ አዲስ አባላት ተይዞ ጉባኤ ማካሄድ አይቻልም። ልዩነታችንም ተሳታፊ መሆን ያለባቸው የጉባኤ አባላት እነማን መሆን አለባቸው የሚለው አንዱ ነው። ምርጫ ቦርድ ከመስራች የጉባኤ አባላት ውጪ የሚደረግ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባን ሆነ የስብሰባውን ውሳኔ አይቀበልም። ጉባኤውም ሊጠራ የሚችለው በምክር ቤቱ እንጂ በሥራ አስፈፃሚ አይደለም። ሌላው ፓርቲው የተመሰረተው መቼ ነው የሚለው ነጥብ አከራካሪ የሆነው። ጠቅላላ ጉባኤውን የሰራ ዘመን ለመወሰንም ይህ ወሳኝ የክርክር ነጥብ ሆኗል። ግማሾቹ መቆጠር ያለበት ፓርቲው ከተመሰረተበት ታህሳስ 22 ቀን 2004 ዓ.ም ነው ሲሉ፤ ሌሎቹ ሕጋዊ ሰርቲፊኬት ካገኘንበት ሐምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም ነው ይላሉ። አሁን ቅሬታ የሚያቀርቡትም ከሚሉት ብንቆጥር እንኳን አራት ወር ይቀራል። መስማማት ከቻልን ግን አሁንም መጥራት የሚከለክል ምንም ነገር የለም። ሌላው በጠቅላላ ጉባኤው ስብሳባ ላይ የሚቀርቡት አጀንዳዎች ምን መሆን አለባቸው የሚሉትንም ገና እየተመለከትናቸው ነው” ሲሉ የተነሳውን ክሬታው ተከላክለዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ራሳችሁን ቻሉ ለናንተ የሚሞት ወታደር የለም" ዐቢይ | ከወሎ ግምባር!/ 2 ፓትሮል ተማረከ/ፖሊስ ጣቢያው ተሰበረ!

ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ፓርቲው ጉባኤ አለመጥራቱ ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንፃር ሕጋዊ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል ወይ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ “እኛም ይህን ጉዳይ አይተነው ነበር። መተዳደሪያ ደንቡ በየአመቱ ጉባኤ መጠራት እንዳለበት ይደነግጋል። ይህ መደረግ ነበረበት። ሆኖም ግን በገጠመን የገንዘብ አቅም ማነስና በሌሎች ምክንያቶች ጉባኤውን ማካሄድ አልቻልንም። ቀጣይ ጉባኤ ለማድረግ በቀጣይ እሁድ ለምክር ቤት አባላት የስብሰባ ጥሪ ተደርጓል። በዚህ ስብሳባ ላይ ለሁሉም ጉዳዮች ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት በጠቅላላ ጉባኤ መጠራት አለመጠራት ላይ በምክር ቤት ውስጥ በተነሳ አለመግባባት ከዴሞክራሲያዊ አፈታት ውጪ ወደ ድብድብ ማምራቱን ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ የሰማያዊ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት ገልፀውልናል። አቶ ስለሺ ግን በስብሳበው ወቅት ከፍተኛ የኃይለ ቃል ምልልስ እንደነበር አምነው፤ ድብድብ ነበረ የተባለው ግን ፈጽሞ የተጋነነ መረጃ ነው ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

የጠቅላላ ጉባኤው ስብሰባ የማይጠራው በኢንጅነር ይልቃል ጌትነት በሊቀመንበርነት የመቀጠል፣ አለመቀጠል ጥያቄ በአጀንዳነት በመቅረቡ መሆኑን ቅሬታ ያቀረቡ አባላት ይገልፃሉ ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ “ኢንጅነር ይልቃል በአጀንዳነት መነሳቱ በእኛ በኩል የሚያስፈራ አጀንዳ አይደለም። ቅሬታ አለን የሚሉ ሰዎች ስለፈለጉ ብቻ የተለየ ነገር አይመጣም። ጠቅላላ ጉባኤው ሊቀመንበሩ የሰራቸውን ስራዎች ዘርዝሮ ቆጥሮ ነው የሚገመግመው። በዘፈቀደ በሰዎች ቅሬታ የሚሰራ አሰራር የለም። በዚህ ደረጃ ካየነው ሊቀመንበሩ ከሥራ አስፈፃሚው ጋር በመሆን የሚቆጠሩ የሰራቸው ስራዎች አሉ። ለዚህም ነው፣ በዓለም ዓቀፍ መድረክ በሀገር ውስጥ ትርጉም ያለው አመለካከት ፓርቲው ማግኘት የቻለው። ቅሬታ የሚያቀርቡ ወገኖች የሊቀመበንር ቦታውን ደፍረው ለመያዝ የሚሹ አይመስለኝም። ስለዚህም ጉባኤው መጣ፣ አልመጣ እኛ አያስፈራኝም” ብለዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በለንደን እና በአካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዛሬ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል።

በተጠናቀቀው በዚሁ ዓመት በአሜሪካን ሀገር በኢትዮጵያዊያን የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ሁለት የሰማያዊ ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚው አባላት እንዲገኙ የቀረበላቸውን ጥሪ ለመወሰን የተደረገውን የፓርቲው ስብሰባ የተመለከተ ሚስጥር አሳልፋ ሰጥታለች በሚል ከሥራ አስፈፃሚነት የታገደችው የወ/ሮ ሃና ደጋፊዎች አዲስ አንጃ ሆነው ፓርቲው ውስጥ ሁለት የኃይል አሰላለፍ መፈጠሩ ይነገራል። በዚህ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው? “ወ/ሮ ሃና ዋለልኝ ቅሬታ እንዳላት አውቃለሁ። ቅሬታዎንም ለፓርቲው ዲሲፒሊን አቅርባ እየታየላት ነው የሚገኘው። ሥራ አስፈፃሚውም ተገቢውን ውሳኔ በወ/ሮ ሃና ላይ ማስተላለፉን አውቃለሁ። በዚህ ቅሬታ መሰረት የተደራጀ አንጃ በፓርቲው ውስጥ አለ ለሚለው መረጃ የለኝም። ሆኖም አንድ ሁለት የሚሆኑ ቅሬታ የሚያቀርቡ ሰዎች ይኖራሉ። አንጃ ለመሆን ግን ቢያንስ ምክር ቤቱን ወይም ሥራ አስፈፃሚውን ለሁለት መክፈል የሚችል ደረጃ ላይ የደረሰ እንቅስቃሴ መኖር አለበት። በዚህ ደረጃ ፓርቲው ውስጥ ስለመኖሩ መረጃ የለኝም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

 

ሰንደቅ ጋዜጣ

1 Comment

  1. የይልቃል ጥርት ያለ የሃሳብ አቀራረብና ከአገር አገር እየዞረ የሠራው ሥራ ነው ድርጅቱን በአጭር ጊዜ ጎልቶ እንዲወጣ ያደረገው። ይህ እየታወቀ ምርጫ ሲቃረብ በርሱ ሊቀመንበርነት ላይ የሚነሳ ጥያቄ መኖሩ ምንጩ ከየት እንደሆነ ለመገመት አያስቸግርም።

Comments are closed.

Share