አንድነትና መኢአድ የውህደት ጥያቄያቸውን ለምርጫ ቦርድ አቀረቡ

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ለረጅም ጊዜ ሲያካሂዱት የነበረውን ድርድራቸውን አጠናቀው የቅድመ

ውህደት ስምምነት በቅርቡ ካደረጉ በኋላ፣ በመጪው ሐምሌ 5 እና 6 ቀን 2006 ዓ.ም. በሚያካሂዱት ጠቅላላ ጉባዔ ለመዋሀድ እየሠሩ መሆናቸውን የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሐሪ አስታወቁ፡፡ ምንም እንኳን ሐምሌ 5 እና 6 የሚለው በጊዜያዊነት የተያዘ ቢሆንም፣ በዚህ ጊዜ ለመዋሀድ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡

ቅድመ ውህደት ስምምነቱን ተከትሎ ከሁለቱም ፓርቲዎች የተውጣጡ አሥር አባላት ያሉት ኮሚቴ በመምረጥ የውህደት ሥራው እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ‹‹ይህም ሥራ ያለምንም እንከን በመካሄድ ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉትና ውህደቱን በጉጉት እየጠበቁት እንደሆነ የገለጹት አቶ አበባው፣ ውህደቱም በተያዘለት ጊዜ እንደሚከናወን ያላቸውን እምነት አስረድተዋል፡፡

በጊዜያዊነት ከተያዘው ቀን በፊት ሁለቱም ፓርቲዎች ባቋቋሙት ኮሚቴ አማካይነት የውህደቱ ስብሰባ የት እንደሚካሄድ እንዲሁም የፋይናንስና ተያያዥ ጉዳዮችን በሚመለከት እየሠሩ እንደሚቆዩም አክለው አብራርተዋል፡፡

በውህደት የሚፈጠረው ፓርቲ አዲስ ስያሜ ስለሚኖረው ሁለቱም ፓርቲዎች የየራሳቸውን አንድ አንድ ስያሜ በማቅረብ ከውህደቱ በፊት በውይይት እንደሚፀድቅና አዲስ ዓርማም እንደሚኖረው ጠቁመው የተቋቋመው ኮሚቴም እነዚህን ሥራዎች እየሠራ እንደሚቆይም አቶ አበባው አስረድተዋል፡፡

Source: Ethiopian Reporter

ተጨማሪ ያንብቡ:  Hiber Radio: ኢትዮጵያ መንግስቴን ለመገልበጥ የታጠቁ ሀይሎችን ወደ ግዛቴ ሰርገው እንዲገቡ እያደረገች ነው ስትል ኤርትራ ከሰሰች፣ኢትዮጵያ በያዘችው ያልተስተካከለ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ፖሊሲ የተባበሩት መንግስታትን የምዕተ ዓመቱን እቅድ ማሳካት እንደማትችል ተገለጸ፣አንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ በድንገት አረፈ፣በየመን የሚገኘው ጋዜጠኛ ግሩም ተጨማሪ የእስር ስጋት እንደተደቀነበት ገለጸ፣በግልገል ግቤ ሶስት ግንባታ ላይ ኢትዮጵያ ለቀረበባት ወቀሳ ጠንካራ ምልሽ ሰጠች እና ሌሎችም
Share