በ3ቱ የዞን 9 አባላት ፖሊስ ሊመሰረት ያሰበው የሽብርተኝነት ክስ በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደረገ

ከብስራት ወ/ሚካኤል

ዛሬ እሁድ ግንቦት 10 ቀን 2006 ዓ.ም. አራዳ በሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት በፍቃዱ ኃይሉ፣ አቤል ዋበላ እና ማህሌት ፋንታሁን ከረፋዱ 4፡20 ቀርበው ነበር፡፡ ይዟቸው የመጣውና እስካሁንም መደበኛ ክስ ያልመሰረተው የማዕከላዊ ፖሊስ ምርመራዬን አልጨረስኩም፣ ጉዳዩ ከሽብር ጋር ስለሚያያዝ ተጨማሪ የ 28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ ሲል ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል፡፡

ፍርድ ቤቱም ከዚህ በፉት ለ24 ቀናት አስራችሁ ያቀረባችሁት ከሽብር ጋር የተያያዘ ባለመሆኑ እና ሌላ አዲስ ሂደት ስለሌለ ከዚህ በፊት ያላቀረባችሁትን ከሽብር ጋር የተያያዘ የሚለውን ጭብጥ አልቀበልም፣ ተጨማሪ የ28 ቀናት የምርመራ ጊዜ የተጠየቀውም ተገቢ አይደለም ካለ በኋላ የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ በመስጠት ለእሁድ ግንቦት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም ፖሊስ ያቀረበውን ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ የሚውን ውድቅ አድርጎታል፡፡

ትናንት ግንቦት 9 ቀን 2006 ዓ.ም. የነበረው የ 6ቱ ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች ፖሊስ ጉዳዩን ከሽብር ጋር አያይዞ ተጨማሪ የ28 ቀናት የጠየቀው ተፈቅዶለት ለሰኔ 7 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ትናንት የነበረው የ6 ቱን ጉዳይ የተመለከተው ዳኛ ወንድ ሲሆን የዛሬውን ጉዳይ የተመለከተችው ዳኛ ሴት መሆኗ ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል አዲስ ጉዳይ መጽሄት የዛሬውን የፍርድ ቤት ውሎ እንደሚከተለው ዘግቦታል፦

ሦስቱ ጦማሪን የ 14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተሰጠባቸው
“ማልቀስ፣በጩኸት ሠላማታ መስጠትና ሰልክ መነካካት አይቻልም”
ፖሊስ
እሁድ ግንቦት 10 ቀን 2006 ዓ.ም በአራዳ ፍርድ ቤት አንድኛ ምድብ ችሎት የቀረቡት የዞን9 ሦስት ጦማሪያን ለግንቦት 23 ቀን 2006 ዓ.ም እንዲቀርቡ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ በዛሬው ዕለት የቀረቡት ሦስት ጦማሪያን በፍቃዱ ኃይሌ፣ማኀሌት ፋንታሁንና አቤል ዋበላ ሲሆኑ በትናትናው ዕለት የቀረቡት ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ፖሊስ በድንገት ጉዳዩን ከፀረ-ሽብር አዋጁ ጋር በማያያዝ ጠርጥሪያቸዋለሁ በማለቱ ፍርድ ቤቱ የፖሊስን ሐሳብ በመቀበል 28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ያስፈልገኛል በማለቱ የጠየቀውን የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፓርላማው ያሳለፈውን ያለመከሰስ ውሣኔ በ24 ሰዓታት ልዩነት አጠፈ፤ አቶ ቃሲም እየተፈለጉ ነው

በዛሬው ውሎ የቀረቡት ጦማሪያን ላይ ፖሊስ የጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ ልክ እንደትናቱ ተጠርጣሪዎቹን በፀረ-ሽብር ሕጉ እንዲታይልኝ በማለት የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ግን እነዚህ ልጆች ሚያዝያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም ስታቀርቧቸው አገርን በማኀበራዊ ድረ-ገፅ ለማተራመስና ራሱን የመብት ተከራካሪ ነኝ ከሚል የውጪ አካላት ጋር ይሰራሉ ብዬ እጠረጥራቸዋለሁ ብላቹ አሁን ድንገት ጉዳዩን ከፀረ-ሽብር ሕጉ ማያያዝ ተገቢ አይደለም በማለት የዕለቱ ዳኛ የፖሊስን ጥያቄ ወድቅ በማድረግ የጠየቀውን የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ውድቅ በማደርግ 14 ቀን እንዲሆን ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ የጋዜጠኞቹና ጦማሪያኑ ጠበቃ የሆኑት አቶ አምሐ መኮንን ጠይቀናቸው “ያቀረብነው ክርክር ተቀባይነት በማገኘቱ የጊዜ ቀጠሮ ከ28 ቀን ወደ 14 ቀን ሊዘዋወር ችሏል፡፡ መደበኛው ክስ ሲቀርብ ግን ምን ሊገጥመን እንደሚችል አናቅም ሲሉ ለአዲስጉዳይ ተናግረዋል”፡፡ በተጨማሪም የፀረ-ሽብር ሕጉ ደካማና ጠንካራ ጉን አለው፡፡ ደካማ ጎኑ የሚባለው አንድ ሰው በሽብር አዋጁ ሲከሰሰስ ለምርመራ ተጨማሪ ቀን ሲጠይቅ ፍርድ ቤቱ ለምርመራ የሚሰጠው 28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ሲሆን በጎ ነገሩ ግን 28 ቀኑ ከአራት ወር በላይ አይጓዝም ብለዋል፡፡ በትናትናው ዕለት የቀረቡት ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ፍርድቤቱ 28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ሲሰጥ እስካሁን የታሰሩት ከግምት ውስጥ ገብቶ በአዋጁ መሠረት ተጨማሪ ቀጠሮ የሚጠየቅ ከሆነ አንድ የጊዜ ቀጠሮ ብቻነው የሚሰጠው ብለዋል፡፡

በዛሬው ቀን የቀረቡትን ተጠርጣሪ የሆኑትን ጦማሪያን የፍርድ ቤት ሁኔታ ለመታደም በርካታ ሰዎች የተገኙ ቢሆንም ፖሊስ ከትናቱ በባሰ ከአንድ ቤተሰብ አንድ ሰው ብቻ ችሎት ገብቶ መከታተል እንዲችል ባቻ ፈቅዷል፡፡ በተጨማሪም ችሎት ከመሰየሙ በፊት ፖሊስ በፍርድ ቤት ጊቢ ውስጥ የነበሩትን ቤተሰብና ችሎቱን ለመታደሚ የተገኙትን ዜጎች ማልቀስ፣በጩኸት ሠላምታ መስጠት ፣ሞባይል አውጥቶ መነካካት እንደማይቻል በማስጠንቀቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ከዚህ መስመር የሚወጡትን በሕግ ለመጠየቅ እንደሚገደድ አሳስቧል፡፡ ችሎቱ የጊዜ ቀጠሮን ሰጥቶ ካጠናቀቀ በኃላ ፖሊስ በፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የነበሩትን ታዳሚያን ተጠርጣሪዎቹን መሰናበት አትችሉም በማለት ከጊቢ እንዲወጡ አድርገዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሰሜን ሸዋ ዞን የተፈፀመውን ጥቃት የሚያወግዝ የተቃውሞ ሰልፍ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሄደ
Share