አማርኛ ቋንቋን የኢትጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያን ብሎም የዓለም ቋንቋ ማድረግ እንደሚገባ ኒጀራዊቷ ራህመቶ ኪታ ገለጸች፡፡
ጋዜጠኛ፣ የፊልም ዳይሬክተር፣ ፕሮዲዩሰር እንዲሁም የፍራንኮ አፍሪካን ፊልም አዋርድ አሸናፊ የሆነችው ራህመቶ ኪታ አማርኛን የአፍሪካ ህብረት የስራ ቋንቋ ለማድረግ ከዓመታት በፊት እንቅስቃሴ መጀመሯን ተናግራ አሁን ላይም አማርኛን ይፋዊ የአፍሪካ ህብረት የስራ ቋንቋ ተደርጎ ሊካተት እንደሚገባ እየሞገተች እንደሆነ ገልጻለች፡፡
እኛ አፍሪካውያን የራሳችንን ባህል በራሳችን ቋንቋ ካላስተዋወቅን የሌሎች ባህል ይወርሰናል የምትለው ራህመቶ አማርኛ የኢትዮጵውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያን እንዲሁም የዓለም ቋንቋ ልናደርገው ይገባል ትላለች፡፡
ራህመቶ በአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጉባኤ ላይ የፓንአፍሪካ ፊልም ውይይትን ለመታደም ከሰሞኑ አዲስ አበባ የገባች ሲሆን አፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በየዓመቱ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄድ ቢሆንም ስለሚካሄደው ጉባዔ ከጥቂት ከተማሩ ኢትዮጵያውያን ውጪ ስለምን እንደሚወራ አይሰሙም፤ ይህም ሊሆን አይገባም ትላለች፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን አነጋግራ እንደነበር የገለጸችው ራህመቶ፤ በቅርቡም ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳፋኪ መሀመት ይፋዊ ደብዳቤ መስጠቷንና የኬንያውን ፕሬዚዳንት ማናገሯን ገልጻለች፡፡
በዓለም ላይ በርካታ ቋንቋዎች ቢኖሩም እንደ አማርኛ ጥንታዊ የሆኑ ቋንቋዎች ጥቂት በመሆናቸው መንከባከብና ማስተዋወቅ ይገባል ብላለች፡፡
ለዚህም ቋንቋውን በተሰማራችበት የፊልም ሙያ ለዓለም እያስተዋወቀች ትገኛለች፡፡
ቋንቋውን በኪነ ጥበቡ ከማስተዋወቅ አኳያ በቅርቡ በሰራችው ‹ዘ ዌዲንግ ሪንግ› የተሰኘ ፊልሟ ‹የጋብቻው ቀለበት› የሚል የአማርኛ ስያሜን በመስጠት በተጨማሪም በፊልሙ ላይ የተሳተፉ ተዋናዮችን ስም በአማርኛ በመጻፍ ቋንቋውን ለማስተዋወቅ ትልቅ ሚና አበርክታለች፡፡
ራህመቶ በአማርኛ ለመጻፍ የመረጠችበት ምክንያትም አማርኛ እጅግ ጥንታዊ ቋንቋ ከሆኑ የዓለማችን የጽሁፍ ቋንቋዎች አንዱ በመሆኑ እንደሆነ ተናግራለች፡፡
በዚህ ስራዋ ላይም ኢትዮጵያዊ የፊልም ባለሙያ የሆኑት ሀይሌ ገሪማ፣ ሰለሞን በቀለ እንዲሁም በኒጀር የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ክቡር አምባሳደር አማዱ ሀሰን ሜዳዋ ከፍተኛ ትብብር ማድረጋቸውን ገልጻ ምስጋናዋን አቅርባለች፡፡
በተጨማሪም በቀጣይነት ፊልሞቿን ወደ አማርኛ አስተርጉማ በኢትዮጵያ ለእይታ የማብቃት ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች፡፡ ራህመቶ አማርኛ ቋንቋ የአፍሪካ ህብረት 7ኛ የህብረቱ ይፋዊ የስራ ቋንቋ እስኪሆን ጥረቴን አላቆምም ብላለች፡፡
ኢ ፕ ድ)