የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች 200 ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው የአንድ ከተማ ስም መቀየራቸው ተነገረ

  • ‹‹አንድን ብሔር ታጣቂዎች እየገደሉ ጨርሰው 50 እና 60 ሰዎች ቀርተዋል›› ተብሏል

የደቡብ ምዕራብ ክልል ኢትዮጵያን በሚያዋስነው የደቡብ ሱዳን ደንበር ታጣቂዎች ወደ ኢትዮጵያ እስከ 200 ኪሎ ሜትር ዘልቀው በመግባት፣ የአንድ ወረዳ ከተማ ስም መቀየራቸው በፓርላማ ተገለጸ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከሰሞኑ ደቡብ ሱዳንን በሚያዋስኑት የጋምቤላና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች  ድንበር አካባቢ በመገኘት፣ በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ፣ ዝርፊያና መፈናቀል ተረድቻለሁ ብሏል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ከመስክ የተመለሱ አባላት በተገኙበት፣ ባለፈው ሳምንት የአገር መከላከያ ሚኒስቴርን የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

ከመስክ ምልከታው ከተመለሱ የምክር ቤት አባላት፣ በደቡብ ምዕራብ ኦሞ ዞን የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ከ150 እስከ 200 ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አልፈው በመግባት ካምፕ በማቋቋም፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ እየገደሉና እያፈናቀሉ በርካታ የወርቅ ሥፍራዎችን እየተቆጣጠሩና የሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር እያካሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሱሪ፣ ቢሮና፣ ማጂና ሱርማ በተበሉ ወረዳዎች የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማጋጨትና በማጋደልና በርካቶችን እያፈናቀሉ እንደሆኑ የገለጹት የቋሚ ኮሚቴው አባል፣ ‹‹የሱሪ ወረዳ ዋና ከተማ የሆነችውን ከተማ በመቆጣጠርና ስሟን በመቀየር በጉግል ማፕ ላይ የደቡብ ሱዳን ከተማ እንደሆነች እያስመሰሉ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የሽመቤት መርሻ የተባሉ የኮሚቴው አባል ወደ ደቡብ ምዕራብ ክልል ለመስክ ምልከታው የሄደውን የኮሚቴ አባል፣ የቡድን መሪ ሆነው መሄዳቸውን ገልጸው፣ ክልሉ በተፈጥሮ የታደለ በመሆኑ ከራሱ አልፎ ኢትዮጵያን ሊቀልብ የሚችል ፀጋ ያለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ክልሉ የሚዋሰንበት የደቡብ ሱዳን ድንበር ከዚህ ቀደም በአገር መከላከያ ሠራዊት ሲጠበቅ የቆየ ቢሆንም፣ በቅርቡ በተጠናቀቀው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ምክንያት በደቡብ ምዕራብ ኦሞ ዞን ማጂ፣ ቤዚና ሱርማ የተባሉ አካባቢዎች መከላከያ ወደ ሌላ ተልዕኮ በመሄዱ ድንበሩ በአካባቢው ነዋሪዎች  እንደሚጠበቅ ለመረዳት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  Somali Refugees Fill UN Camp in Ethiopia Within One Month

በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎችን ኃይል መቋቋም ከባድ ሆኖበት ከቀዬው እየለቀቀ መሆኑን የገለጹት የኮሚቴው አባል ከደቡብ ሱዳን መጣ የተባለው ሽፍታና ታጣቂ የቡድን መሣሪያ የታጠቀና ለየት ያለ ሥልጠና ያለው በመሆኑ ኢትዮጵያውያን እየተገደሉ፣ ከብቶቻቸውን እየተዘረፉና ቀዬአቸውን ለቀው እንዲወጡ ስለመደረጋቸው አብራርተዋል፡፡

‹‹በጣም የሚያሳዝነው መልቀቁ ብቻ ሳይሆን በሁለትና በሦስት ቦታዎች ታጣቂዎቹ ሰፍረው፣ በአብዛኛው በከብት ዕርባታና በእርሻ ሥራ የሚተዳደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተፈናቅሎ መሥፈሪያ በማጣቱ እርስ በርስ መገዳደል ውስጥ መግባቱ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በመሆኑም ይህ በጣም ቀላል አይደለም፡፡ ይህን ያህል ርቀት ገብተው የራሳቸውን ኃይል ስላሰፈሩበት፣ ሕዝብ እየጠየቀ ያለው ጉዳይ መገለጽ ስላለበት እኛ ኢትዮጵያውያን አይደለምን ወይ? ለምን ሠራዊት አይደርስልንም? የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

‹‹እንዲያውም የአንደኛው ብሔር ወደ 50 እና 60 ሰዎች ብቻ ናቸው የቀሩት፣ ሌሎቹን ፈጅተዋቸዋል፡፡ በጠቅላላ እንዲህ ብዬ ልናገር፣ በጣም አሳሳቢ ነው፤›› ሲሉ የመከላከያ ሚኒስቴርን አበክረው ጠይቀዋል፡፡ ‹‹መከላከያ ይህ መረጃ የለውም ወይ? ክልሉ ከዚህ በፊት መረጃ እንዳደረሳችሁ እየተናገረ ነው፡፡ አሁንም መረጃው እጃችሁ የደረሰ በመሆኑ፣ ይህንን ይዛችሁ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ጋምቤላ ክልልን ጨምሮ ማዕድን ያለበት በሙሉ ወርቅ እየተዘረፈ፣ ከብት በያለበት በሙሉ እየተወረረ በመሆኑ፣ የአገር መከላከያ አገርና ሀብት የማዳን ተልዕኮ አፋጣኝ ምላሽ ይስጥ፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች በስተጀርባ ኢትዮጵያን መውጋት የሚፈልጉ ኃይሎች እንዳሉ ይገመታል ብለዋል፡፡  በመሆኑም ክልሉ አዲስ በመሆኑና እንደ ሌሎቹ የተደራጀ የፀጥታና የፖሊስ ኃይል፣ እንዲሁም ሀብት ሊጎድለው ስለሚችል የተፈጠረውን ችግር ብቻውን መቆጣጠር የሚችልበት አቅም ላይ እንዳልሆነ ተገንዝበናል ብለዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  Hiber Radio: በእስራኤል የዘረኝነት ጥቃት ሰለባ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የጠነከረ ተቃውሞ ተከትሎ ባለስልጣናት ዘረኛ እርምጃ የወሰደውን ፖሊስ እናባርራለን ማለታቸው፣ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን አቋም እንድትመረምር መጠየቁ፣በየመን ያሉ ኢትዮጵያውያን ሞተን ሻማ ከማብራታችሁ በፊት በሕይወት ታደጉን ሲሉ ጥሪ አስተላለፉ፣ዶ/ር መረራ በአገር ቤት ያለው የወጣቱ ሁኔታ ምርጫ 97ን ያስታውሳል ማለታቸው፣ የመኢአድ አባላት እየታፈኑ መወሰድ መቀጠሉ፣ የጦማሪ ሶሊያና ሺመልስ ቃለ መጠይቅ እና ሌሎችም

በዚህ ውይይት ከአገር መከላከያ ሠራዊት የመጡ አንድ የሥራ ኃላፊ፣ ‹‹የተከበረው የቋሚ ኮሚቴ እንዲረዳ የማሳስበው እንደሚታወቀው አገራችንን የማፍረስ ተዕልኮ ከውስጥም ከውጭም እንደተቃጣብንና የእነሱን ጋሻ ጃግሬ ተይዞ በየአቅጣጫው ዘመቻ እንደተወጣብን ይታወቃል፤›› ብለዋል፡፡  ይህ ደግሞ ሠራዊት ባለው ብዛት እያንዳንዱ ችግር ያለበትን አካባቢ በተፈለገው ጊዜና ቦታ ደርሶ ለመፍታት የራሱ ውስንነት ስለመኖሩ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም እንደ ተቋም ሲወሰድ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የአደጋ ደረጃቸው ከፍ ያሉና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች  የሚመጡ በመሆናቸው፣ ሠራዊቱ የሚሰማራው ከዚህ አንፃር ነው ብለዋል፡፡

በአካባቢዎቹ ያሉት ችግሮች የሚታወቁ መሆናቸውን ያብራሩት የሥራ ኃላፊው፣ ‹‹መታየት ያለበት ቅድሚያ ለማን የሚለው ጉዳይ በመሆኑ፣ አሁን በሰሜን ኢትዮጵያ ተፈጠረ የሚባለው የሰላማዊ ሁኔታ ተስተካክሎ ወደ አንድ ደረጃ የደረሰ አይደለም፡፡ ነገ ከነገ ወዲህ ምን ሊነሳ እንደሚችል ለመገመት የሚያስቸግር ሁኔታ ላይ ያለነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም ይህ ነው የሚከፋው፣ ያኛው ነው የሚለው ምርጫና የቅደም ተከተል የማስቀመጥ ጉዳይ በመሆኑ፣ ጉዳዩ በዚህ ማዕዘን መታየት አለበት፤›› ብለዋል፡፡ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና በጋምቤላ አካባቢዎች እንዲህ ዓይነት በተለይም የታጣቂ ኃይሎች ዝርፊያና ረብሻ፣ እንዲሁም ከስርቆት ጋር የሚያያዙ ነገሮች በዋናነት ሊሠሩ የሚችሉት ከአካባቢው በሚደራጁ ሚሊሻ፣ ፖሊስና ልዩ ኃይሎች መሆን እንዳለበት አብራርተዋል፡፡

እነዚህ ኃይሎች ጥምረት ፈጥረው ከአቅማቸው በላይ እስኪሆን ድረስ የሚሠሩበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ያሉት የመከላከያ ሥራ ኃላፊው፣ ‹‹በሕገ መንግሥቱም እንደ ተቀመጠው የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች መፍታት ያልቻሉት ጉዳይ ላይ የመከላከያ አቅም ሲጠየቅ ያንን አቅም ይዞ ተልዕኮውን ይወጣል፤›› ብለዋል፡፡

መከላከያ ሁልጊዜም ቢሆን እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ይሁን እንጂ መከላከያ የተሰጠው አገራዊ የቤት ሥራ ሰፊ በመሆኑ ከእነዚህ የቤት ሥራዎች መከላከያ የትኛውን ነው መሸፈን ያለበት? ከሚል አሠራር ውጪ በአገሪቱ አንድም ሰው በጠላትና በሌላ ኃይል እንዲጠቃ የሚፈልግ ሠራዊት የለም ብለዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  40 የዓድዋ ተወላጆች ታሰሩ

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር በዚህ አካባቢ በተመረጡ ቦታዎች፣ ቋሚ የመከላከያ ካምፕ ማቋቋምና ማደራጀት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ሪፖርተር

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share