ለዘ-ሐበሻ ድረ ገጽ ተከታታዮች በሙሉ: እንኳን ከ2014 ዓ.ም ወደ 2015 ዓ.ም በሰላም አሸጋገራችሁ

ውድ የዘ-ሐበሻ ድረገፅ ተከታታዮችና አንባቢያን!

መጪው ዘመን ሀገራችን የናፈቃትን ሰላምና መረጋጋት አግኝታ በዓለም ዙሪያ የተበተንነው ልጆቿ የምንሰባሰብበትና በልዩ ልዩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ችግሮች የሚሰቃየው ሕዝባችን እፎይታ የሚያገኝበት ዘመን እንዲሆን የዘሀበሻ ድረገጽ ዝግጅት ክፍል ልባዊ ምኞቱን ይገልጻል፡፡

ዘ-ሐበሻ  ድረ ገጽ ላለፉት በርካታ ዓመታት በእንግሊዝኛና በአማርኛ ቋንቋዎች በሚወጡ ጽሑፎችና ተጓዳኝ የምስልና የድምጽ ልጥፎች (posts) ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል ሌት ከቀን ሀገርንና ሕዝብን ስታገለግል መቆየቷ የሚታወቅ ነው፡፡ በነዚህ ፈታኝ ዓመታት የሕዝብንና የሀገርን ህመሞች በመታመም፣ ከጸሐፊዎች የሚደርሷትን ወቅታዊ ጦማሮችና መጣጥፎች እንዲሁም ዜናዎችን በየደቂቃና ሰዓቱ በመከታተል ለዕይታና ለንባብ በማብቃት የበኩሏን ድርሻ ስትወጣ ቆይታለች፡፡ አሁንና ወደፊትም በዚሁ በመቀጠል ሀገራችን ውስጥ የተደላደለ ሰላምና መረጋጋት ተፈጥሮ እውነተኛው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እስኪገነባና የዜጎች ስደት፣ መፈናቀል፣ እስር፣ እንግልትና ሞት እስኪቀር ድረስ ትግሏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ማሳወቅ እንፈልጋለን፡፡ ይህንንም የምናደርገው ሀገር ከሌለ ሁሉም ከንቱ መሆኑን ከመረዳት ነው፡፡ ለሁላችንም የምትሆን ሀገር እስካልተፈጠረች ድረስ በአሁኑ አካሄዳችን የትም ልንደርስ እንደማንችል የዘ-ሐበሻ ድረ ገጽ አዘጋጆችና ተባባሪ ጸሐፊዎች እምነት ነው፡፡

አዲሱ ዓመት የምንናፍቀውን ሀገራዊ ሰላምና እውነተኛ ዴሞክራሲ የምናይበት፣ ዘረኝነትና ጎጠኝነት ተወግደው ኢትዮጵያ ሀገራችን የሁሉም ዜጎች እኩል የምትሆንበት እንዲሆን እየተመኘን መጪው ዓመት የሰላም የዕድገትና የብልጽግና እንዲሆንልን በድጋሚ መልካም ምኞታችንን እንገልጻለን፡፡

አልዩ ተበጀ

የዘ-ሐበሻ ድረ ገጽ ዝግጅት

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር "የተከበርከው የኢትዮጵያ ህዝብ እራስህን ከወያኔ አሽከርነት(መጠቀሚያነት) ልታርቅ ይገባል" አለ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share