“በሐረር ከተማ በደረሰው ቃጠሉ ከዛም የክልሉ ፖሊስ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት ማድረሱን በቸልታ አንመለከተውም” – አንድነት

ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ(አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)

በሐረር ክልል ሕዝብ ላይ የደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት አንድነት በቸልታ አይመለከተውም

የካቲት 30 ቀን 20006 ዓ.ም በታሪካዊቷ የሐረር ከተማ በጀጎል ሸዋበር በደረሰው ቃጠሎ እና ከዚያም በኋላ የክልሉ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ በዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱ የፓርቲያችንን አመራሮች፣ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ያሉ አባላትና ደጋፊዎችን በእጅጉ አሳዝኗል፡፡

ምንም እንኳን የቃጠሎው መንስኤ ተጣርቶ ይፋ ያልተደረገ ቢሆንም በጀጎል ሸዋ በር እየደረሰ ያለው ተደጋጋሚ ቃጠሎ ድንገቴ ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም፡፡ በተለይም በየካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም የተነሳውን ቃጠሎ በተገቢ ፍጥነት ለመቆጣጠር የክልሉ መንግስት ፍላጎት ያልታየበት መሆኑ፤ ይልቁንም ግሬደር መኪና አስጠግቶ ቦታውን ለማፅዳት መሞከሩ አጠያያቂ ነው፡፡ የክልሉ መንግስት ቃጠሎውን ለመቆጣጠር ተገቢውን ሁሉ ባለማድረጉ የጉዳቱ ሰለባ የሆነው ህዝብ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖበት ክፉኛ እንደ ተማረረ በዚሁ ምክንያትም ቁጣ ተቀስቅሶ ፖሊስ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሱንም በክልሉ የሚገኙ የፓርቲያችን አመራሮች መረጃውን አድርሰውናል፡፡

በመሆኑም ፓርቲያችን የክልሉ መንግስት ትክክለኛው የቃጠሎ መንስኤ በአስቸኳይ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ፤ በማንኛውም ምክንያት ኃላፊነታቸውን በብቃት ያልተወጡ የመንግስት ኃላፊዎች በግልፅ ለተጠያቂነት እንዲቀርቡ፤ የክልሉ ፖሊስ በህዝቡ ላይ የወሰደው የኃይል እርምጃ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ይፋ እንዲደረግ፤ የክልሉ ፖሊስ በወሰደው የኃይል እርምጃ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ብዛትና የጉዳቱ መጠን በአስቸኳይ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ ተገቢ ህክምና እና ካሳ እንዲከፈላቸው፤ ይህንን የፈጸሙ አካላትም ለፍርድ እንዲቀርቡ በአጽንኦት እንጠይቃለን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሚኒስትሮች ምክርቤት ከስልጣኑ በላይ ያፀደቀው ሰነድ አወዛገበ

በአንድነት ፓርቲ በኩል ይህንኑ በህዝብ ላይ የደረሰ ጉዳት ለማጣራትና ለመከታተል በስራ አስፈጻሚው አስቸኳይ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፡፡ ግብረ ኃይሉ ወደ ቦታው በማቅናት ጉዳዩን ካጣራ በኋላ የደረሰበትን መረጃ እና በፓርቲያችን የሚወስደውን ተጨማሪ አቋም በተመለከተ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ እናደርጋለን፡፡

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር
መጋቢት 4 ቀን 2006 ዓ.ም

1 Comment

Comments are closed.

Share