March 3, 2014
10 mins read

Sport: ማንቸስተር ዩናይትድ ከድጡ ወደ ማጡ

man 2

ከይርጋ አበበ

የማንቸስተር ዩናይትድ ስታዲየም ከአፍ እስከ ገደፉ ክለባቸውን በሚያፈቅሩ እንግሊዛውያን ተሞልቷል። ከቁጥራቸው በተጨማሪም ለሰከንድ በማይቋረጥ ዝማሬያቸው ስታዲየሙን ልዩ ድባብ ሰጥተውታል። በዴቪድ ሞይስ የሚሠለጥነው ማንቸስተር ዩናይትድ የምዕራብ ለንደኑን ፉልሃምን እያስተናገደ ነው። ከእነዚህ የኦልድትራፎርድ አድማቂዎች መካከል አንዱ የቀድሞው የክለቡ አሠልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ይገኙበታል። ያች እለት ለኦልድትራፎርዱ ክለብ ደጋፊዎች ልዩ ነበረች። ምክንያታቸው ደግሞ በ1968 ሙኒክ ላይ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ የሞቱትን የቀድሞ ኮከብ ሰማዕቶቻቸውን የሚዘክሩበት እለት መሆኑ ነው። የሰር አሌክስ ፈርጉሰን በእለቱ በስታዲየም ተገኝተው ጨዋታውን መከታተላቸው ግን ከእዚያ ክስተት ጋር ግንኙነት የለውም፤ ምንጊዜም እንደሚያደርጉት ክለቡ ሲጫወት ስታዲየም እየተገኙ መከታተል ስለሚወዱ ነበር።

ጨዋታው ተጀመረ። ስቲቭ ሲድዌል የተባለ የፉልሃም አማካይ እንግዳውን ክለብ ቀዳሚ ያደረገች ግብ ሲያስቆጥር ቀይ ፎጣ አንገታቸው ላይ አስረው ክለባቸውን የሚያበረታቱ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎችን አንገት ማስደፋት ጀመረ። ማንቸስተር ዩናይትድ ከተመሪነት ተነስቶ በእንግዳው መረብ ላይ ሮቢን ቫን ፐርሲና ማይከል ካሪክ ባስቆጠሯ ቸው ሁለት ግቦች መምራት ሲጀምር ሞራላቸው ወድቆ የነበረው የክለቡ ደጋፊዎች ትልቅ ተስፋ ሰንቀው መሳቅ ጀመሩ። ሰር አሌክስ ፈርጉሰንም በቀድሞ ክለባቸው ድል አድራጊነት ተማምነው ደስታቸውን ከጎናቸው ለተቀመጡት ጓደኛቸው ያጋሯቸው ጀመር። ዳሩ ግን መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቅቆ የእለቱ ዳኛ የጨመሩት አራት ደቂቃ ሁሉ ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩት ተቀይሮ የገባው የፉልሃሙ የፊት መስመር ተሰላፊ ዳረን ቤንት የሰር አሌክስ ፈርጉሰንንና የዴቪድ ሞይስን አንገት ያስደፋች፤ የክለቡን ደጋፊዎችም አንጀት ያሳረረች ግብ በማስቆጠር ማንቸስተር ዩናይትድ ነጥብ እንዲጥል አስገደደው።

ይህ የሆነው ከአራት ሳምንታት በፊት ነበር። ከዚያች እለት ጀምሮ ክለቡ ካደረጋቸው ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች በማሸነፍ ከገባበት የውጤት ቀውስ ያገገመ ቢመስለም ከሰሞኑ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የገጠመው ውጤት አስደንጋጭ ተብሏል። በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛው ዙር (ጥሎ ማለፍ) ተሳታፊ ከሆኑት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ማንቸስተር ዩናይትድ ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ምሽት ወደ አቴንስ ተጉዞ የግሪኩን ኦሎምፒያኮስን ገጥሞ ነበር። በዚህ ጨዋታ ማንቸስተር ዩናይትድ በቀላሉ ባያሸንፍ እንኳ ለመልሱ ጨዋታ የሚጠቅመውን ውጤት ይዞ ይመለሳል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ዳሩ ግን ባለሜዳዎቹ ሁለት ለባዶ አሸንፈው የዴቪድ ሞይስንም ሆነ የክለባቸውን የቁልቁለት ጉዞ አፋጠኑባቸው።

ከጨዋታው በኋላ አስተያየቱን የሰጠው የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ አምበል ሮይ ኪን «ለማንቸስተር ዩናይትድ መጫወት ምን ማለት እንደሆነ ያልተረዱ » ሲል ነበር በቀድሞ ክለቡ ተጫዋቾች ላይ የተሳለቀው። ማንቸስተር ዩናይትድ በእለቱ ሁለቱን አጥቂዎች (ዋይኒ ሩኒንና ሮቢን ቫንፐርሲን) በቋሚነት ቢያሰልፍም በ90ደቂቃ የሜዳ ላይ ቆይታ የተጋጣሚውን ግብ ጠባቂ መፈተን የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነበር።

አሁን ሁኔታዎች ሁሉ ለዴቪድ ሞይስ ከባድ እየሆኑባቸው ነው። ምክንያቱ ደግሞ ክለቡ ከሚወዳደርባቸው ሦሰት ውድድሮች ( ካፒታል ዋን፣ ኤፍ ኤ ካፕ፣ፕሪሚየር ሊግ) ዋንጫዎች ቀስ በቀስ ከተፎካካሪነት ውጪ ሆኗል። ክለቡ ዋንጫ አገኝበታለሁ ብሎ ተስፋ ያደረገው ደግሞ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ነበር። ከወዲሁ በጥሎ ማለፉ የመጀመሪያ ጨዋታ ሁለት ለባዶ መሸነፉ ደግሞ ዋንጫ የማግኘት ተስፋውን አጨልሞበታል።

እንደዚህ አይነት የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ የገቡት ዴቪድ ሞይስ በኦልድትራፎርድ የሚኖራቸው ቆይታ «የዛፍ ላይ እንቅልፍ ሆኗል፤» ቢባሉም እንደ አርሴን ቬንገር አይነት አሰልጣኝ ግን ለዴቪድ ሞይስ ጠበቃ መቆም የፈለጉ ይመስላሉ። ቬንገር ምክንያት አላቸው። የቀድሞው የዴቪድ ሞይስ ክለብ ኤቨርተን በ2006 የውድድር ዘመን ፕሪሚየር ሊጉ ተጀምሮ ስምንት ጨዋታዎች ቢያልፉም ሃያኛ ደረጃን ማለፍ ተስኖት በደረጃው ግርጌ ላይ ለረጅም ጊዜ ተኝቶ ቆይቶ ነበር። ሆኖም በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ኤቨርተን እንደ ቶተንሃም፣ ኒውካስትልና ማንቸስተር ሲቲ አይነት ክለቦችን ቀድሞ አምስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቀቀ። ቬንገር ይህ ታሪክ ሊደገም ባይችል እንኳ ዴቪድ ሞይስ ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባል ባይ ናቸው።

በርካቶች ግን በቬንገር ሃሳብ አይስማሙም። ለሃሳባቸው ማጠናከሪያ የሚያቀርቡት ደግሞ ማንቸስተር ዩናይትድ በዴቪድ ሞይስ አሰልጣኝነት እየተመራ ባለፉት ሰባት ወራት ያስመዘገበውን ደካማ ውጤት በመጥቀስ ነው። ከእነዚህም መካከል ክለቡ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከ1972 የውድድር ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳው በኒውካስትል ዩናይትድ መሸነፉ፣ ከ1978 በኋላ ዌስትብሮሚች ኦልድትራፎርድ ላይ አግኝቶት የማያውቀውን ሙሉ ሦስት ነጥብ በዚህ ዓመት ማሳካቱ፣ የደቡብ ዌልሱ ስዋንሲ ሲቲ ኦልድትራፎርድ ላይ በታሪኩ የመጀመሪያውን ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት የቻለውም በዚሁ የውድድር ዓመት በዴቪድ ሞይስ አሰልጣኝነት ዘመን ነው። በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድ በታሪኩ በግሪኩ ኦሎምፒያኮስ ሲሸነፍ የመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፤ ስቶክ ሲቲና ኤቨርተንም ቢሆኑ ከረጅም ዘመናት ቆይታ በኋላ በማንቸስተር ዩናይትድ ሜዳ ሦስት ነጥበ ማግኘት የቻሉት በዚህ የውድድር ዓመት ነው። በተለይ ስቶክ ሲቲ በሰር አሌክስ ፈርጉሰን አሰልጣኝነት ዘመን ኦልድትራፎርድ ላይ ማንቸስተር ዩናይትድን አሸንፎት አያውቅም ነበር። እንዲሁም ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎችን ሲሸነፍ የዘንድሮው ከ13ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው ነው። ይህንን ሁሉ የተመለከቱ የክለቡ ደጋፊዎችና የስፖርት ተንታኞች «የማንቸስተር ዩናይትድ ጉዞ የቁልቁለት ነው» እያሉ መናገራቸውን ተያይዘውታል።

1 Comment

  1. i said it before and i say it again that the golden days of Man-united seem to be over. It is now on decline heading towards relegation zone .No class players would like to join the club in summer .Because Man-u is counting down to become history in foot ball industry. Moy has to go for the best interest of the club.

Comments are closed.

Previous Story

የተምቤን ስብሰባችን ጉድ አደረገን (አብርሃ ደስታ)

Next Story

የፈራ ይመለስ! (ከተመስገን ደሳለኝ)

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop