ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የተሳተፉበት ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ


ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የተሳተፉበት ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በአሜሪካ ኒውጀርዚ ግዛት ዛሬ ተካሄደ፡፡
ሰልፉ የተካሄደው ሕጉን ባረቀቁት የኒው ጀርዚ የኮንግረስ አባል ቲም ማሊኖውስኪ የሚሰሩበት ቢሮ ፊት ለፊት ሲሆን እሳቸውንና ሕጉን የሚቃወሙ መልዕክቶች በሰልፉ ላይ መተላለፉን ኢዜአ ከሰልፉ አስተባባሪዎች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የዳያስፖራው ተወካዮች ሕጉን በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እንደሚቃወሙትና አፍራሽ ከሆነ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ የሚያሳስብ ደብዳቤ ለኮንግረስ አባሉ ተወካዮች ሰጥተዋል።

ቶም ማሊኖውስኪ ያረቀቁት ሕግ ለረጅም ጊዜ የቆየውን የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነት የሚጎዳና የሁለቱን አገራት የማይጠቅም እንዲሁም በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድር መሆኑን ለተወካዮቻቸው የማስረዳት ስራ መከናወኑ ተገልጿል።
“ቶም ማሊኖውስኪ ሽብርተኞችን መርዳት ያቁሙ ‘ኤችአር 6600’ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነው” የሚል መልዕክት የያዘ ባነር አውሮፕላን በኮንግረስ አባሉ ቢሮ ሲያንዣብብ እንደነበረም ተገልጿል።

ረቂቅ ሕጉ ኤርትራንም የሚመለከት በመሆኑ በሰልፉ ላይ በአሜሪካ ከሚገኙት የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች በተጨማሪ ኤርትራውያንም ተሳትፈውበታል።
በቀጣይ በአሜሪካ ትላልቅ ከተሞች ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፎች ለማካሄድ መታሰቡ ተነግሯል።

ረቂቅ ሕጉን የሚቃወሙ እንዲሁም በአሜሪካ ኮንግረስ ለውይይት ቀርቦ ውሳኔ እንዳይሰጥበት ለማድረግ ዘመቻዎች እየተካሄዱ እንደሚገኙ ተመልክቷል።
የ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን በመቃወም በአሜሪካ ኒውጀርዚ ግዛት የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ተስፋ ለኢትዮጵያ ከ’አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’(ኤፓክ)፣ኤርትራ አሜሪካውያን ብሔራዊ ምክር ቤትና ሰላምና አንድነት የዋሺንግተን ዲሲ ግብረሃይል ጋር በመተባባር ያዘጋጀው እንደሆነ ተገልጿል።

ኢዜአ

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሃይማኖት ተቋማትን ማክበርና መንከባከብ የመንግስት ግዴታው ነው - ገለታው ዘለቀ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share