February 15, 2022
12 mins read

ለቸኮለ! ማክሰኞ የካቲት 8/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

2322

1፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በመላ ሀገሪቱ የተጣለውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ63 ተቃውሞ እና በ21 ድምጸ ተዓቅቦ አንስቷል። የአዋጁን መነሳት የተቃወሙ አባላት በተለይ በአፋር እና ኦሮሚያ ክልሎች ግጭቶች በቀጠሉበት ሁኔታ መንግሥት ችግሩን በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት እወጠዋለሁ ብሎ ማሰቡን ተቃውመዋል። በርካታ አባላት ጥያቄ ለመጠየቅ እጃቸውን ቢያወጡም፣ በስብሰባው ከተገኙት 312 አባላት የጥያቄ ዕድል ያገኙት 11 አባላት ብቻ ናቸው። ምክር ቤቱ አዋጁን ያነሳው፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድ ሪፖርት ሳያቀርብ ነው። ምክር ቤቱ ሕወሃት በሀገሪቱ ሕልውና ላይ የደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ በሚል አዋጁን የደነገገው ጥቅምት 23 ነበር።

በተያያዘ ዜና

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየካቲት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተለይም በሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ እንዲነሳ መወሰኑን ኮሚሽኑ በበጎ ተመልክቷል:: ኮሚሽኑ በአስቸኳይ ሁኔታ ወቅት ከአዋጁ አተገባበር ጋር ተያይዞ በቁጥጥር የዋሉ እና አሁንም ያልተለቀቁ ሰዎች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ በድጋሚ ያሳስባል።

በተጨማሪም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቁጥጥር ስር ውለው የተለቀቁ ሰዎችም በእስር ስለመቆየታቸው ማረጋገጫ ባለማግኘታቸው ወደ ስራ መመለስ አለመቻልን ጨምሮ ለተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መጋለጣቸውን ባደረገው ክትትል ተገንዝቧል፡፡ ስለሆነም ሰዎች በእስር የቆዩበትን ጊዜ ማስረጃና ሌሎች አስፈላጊ ሰነዶች የመስጠቱን ሂደት እንዲፋጠንና ሰዎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው መመለስ እንዲችሉ እንዲደረግ ኢሰመኮ ያሳስባል

2፤ “ኢቤይ” (eBay) በተሰኘው ዓለማቀፍ የቅርስ መገበያያ በይነ መረብ ላይ ለሽያጭ የቀረቡ የኢትዮጵያ ሐይማኖታዊና ጥንታዊ ቅርሶችን ጉዳይ የውጭ ዜና አውታሮች ፖለቲካዊ ለማድረግ ሞክረዋል ሲሉ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው ለዋዜማ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ቅርሶች በበይነ መረብ ለሽያጭ ሲቀርቡ የመጀመሪያ አለመሆኑን የጠቅሱት አበባው፣ አሁን ገበያ ላይ ቀረቡ የተባሉት ቅርሶች በትግራዩ ጦርነት ወቅት ስለመመዝበራቸው ማረጋገጫ እንደሌለ ገልጸዋል። ሆኖም ባለሥልጣኑ ካሁን ቀደም እንዳደረገው የኢትዮጵያ ለሆኑት ቅርሶች የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሠራ፣ ቅርሶቹ እንዳይሸጡ ሻጩን አካል እንደሚያግባባ ወይም ከዓለማቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንደሚያደርግ አበባው ተናግረዋል። Link- https://bit.ly/3JtGshD

3፤ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ የአሜሪካው ሕግ መምሪያ ምክር ቤት ውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያጸደቀው “ኤችአር 6600” ረቂቅ ሕግ የመንግሥትን የሰላም ጥረቶች ወደኋላ ሊመልስ ይችላል ሲሉ ዛሬ ለኢፕድ በሰጡት ቃል አስጠንቅቀዋል። ረቂቅ ሕጉ በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመረኮዘ እና ሰላም ለማስፈን የማይጠቅም እንደሆነ የገለጹት ዲና፣ ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅ ሁሉም ወገን ድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል። “በኢትዮጵያ መረጋጋትን፣ ሰላምን እና ዲሞክራሲን ለማስፈን” በሚል የተረቀቀው ረቂቅ ሕግ ከያዛቸው የውሳኔ ሃሳቦች መካከል፣ የሰሜኑ ጦርነት እንዳይቆም እንቅፋት በሆኑ አካላት ላይ አሜሪካ ማዕቀብ እንድትጥል የሚጠይቅ ይገኝበታል።

4፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ማኅበር ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ መንግሥት ጋዜጠኞችን ማሰሩን እና ማንገላታቱን እንዲያቆም ጠይቋል። ማኅበሩ በአሃዱ ኤፍኤም ሬዲዮ፣ በተራራ ኔትዎርክ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኀን፣ በፍትህ መጽሄት፣ በባላገሩ ቴሌቪዥን፣ በአውሎ ሜዲያ እና አሶሴትድ ፕሬስ ጋዜጠኞች ላይ ተፈጽመዋል ያላቸውን የዘፈቀደ እስሮች፣ አፍኖ የመውሰድ፣ ፍርድ ቤት ሳያቀርቡ አድራሻ የመሰወር እና በፍርድ ቤት ጥፋተኛነታቸው ይልተረጋገጠባቸውን ተጠርጣሪዎች በመገናኛ ብዙኀን ስማቸውን የማጥፋት ድርጊቶች አጥብቆ ኮንኗል። ማኅበሩ አያይዞም፣ ባለፉት 3 ዓመታት በመገናኛ ብዙኀን ነጻነት ላይ ለውጥ እንዳልታየ እና ይልቁንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፕሬስ ነጻነት ክፉኛ እየተሸረሸረ እንደሄደ ጠቅሷል።

5፤ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን የሚገኘው ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የኦሮሞ ነጻነት ታጣቂዎች በፈጸሙበት ጥቃት ሳቢያ ከየካቲት 2 ጀምሮ ምርት ማቆሙን ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ሰምቻለሁ ሲል ብሉምበርግ ዘግቧል። የቡድኑ ታጣቂዎች በፋብሪካው ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽሙ እንደቆዩ የገለጸው ኮርፖሬሽኑ፣ በቅርቡ የፋብሪካውን የሸንኮራ አገዳ እርሻ እና ትራክተሮችን በእሳት ማጋየታቸው ለምርቱ መቆም ምክንያት መሆኑን ገልጧል። ባካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ሳቢያ ፋብሪካው ለረጅም ጊዜ ነዳጅ ማስገባት እንዳልቻለ የገለጸው ኮርፖሬሽኑ፣ ፋብሪካው ምርት ማቆሙን ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በማሳወቅ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን ተናግሯል። የአንጋፋው ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ አማካይ ዓመታዊ የስኳር ምርት 270 ሺህ ቶን ይደርሳል።

6፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን የሚገኘው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ንብረት የሆኑ 2 ሰብዓዊ አገልግሎት ሰጭ አምቡላንሶች ሰሞኑን በኃይል እንደተወሰዱበት ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። ለሰብዓዊ አገልግሎት በተሠማሩ የማኅበሩ አምቡላንሶች ላይ የተፈጸመው ድርጊት ኢትዮጵያ ያጸደቀችውን ዓለማቀፉን የጄኔቫ ኮንቬንሽን እንደሚጥስ የገለጸው ማኅበሩ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሁለቱን አንቡላንሶቹን እንዲያስመልሱለት ተማጽኗል። ማኅበሩ ሁለቱ አምቡላንሶቹ መቼ እና በትክክል የት ቦታ ላይ እንደተወሰዱበት እና በኃይል አስገድዶ የወሰዳቸው አካል ማን እንደሆነ ግን ለይቶ አልጠቀሰም።

7፤ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ ከከተማዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ጋር መደማመጥ የሰፈነበት ውይይት ማድረጋቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል። የሁለቱ አካላት ውይይት ያተኮረው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በመስቀል አደባባይ እና በጃን ሜዳ ባሕረ ጥምቀት ቦታዎች ባለቤትነት ላይ ባነሳቻቸው ጥያቄዎች ዙሪያ እንደሆነ የገለጹት ከንቲባዋ፣ ለጥያቄዎቹ ባጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ እና መፍትሄ ለመስጠት አስተዳደሩ እና ቤተ ክርስቲያኗ የጋራ ኮሚቴ በማቋቋም ተከታታይ ውይይቶችን እንዲያደርጉ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

8፤ በሱማሌ ክልል መንግሥት ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እንደተደረገ ተደርጎ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰራጨው መረጃ የተሳሳተ ነው ሲል የክልሉ ኮምንኬሽን ቢሮ ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ አስተባብሏል። በክልሉ መንግሥት ላይ የተሞከረ አንዳችም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የለም- ብሏል መግለጫው። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የክልሉ መንግሥት ከትናንት ወዲያ ባወጣው መግለጫ ከክልሉ ብልጽግና ፓርቲ እና ከመንግሥት መዋቅር የወጡ እና የተባረሩ የቀድሞ አመራሮች እና አባላት በክልሉ ግጭት ለመቀስቀስ፣ ትርምስ ለመፍጠር እና የክልሉን መንግሥታዊ ሥልጣን በኃይል ለመንጠቅ ያሴራሉ በማለት ከሶ፣ የክልሉ ጸጥታ ኃይሎች የእነዚሁን ሕገወጥ ኃይሎች ሴራ እንዲመክቱ ጥሪ አድርጎ ነበር።. [ዋዜማ ራዲዮ]

Leave a Reply

Your email address will not be published.

127190
Previous Story

ልማታዊው ማጭበርበር እና የእማማ ልጣሽ መታመም ተስፋሁን ከበደ – ፍራሽ አዳሽ – 25 – ጦቢያ@Arts Tv

273692578 914528229127584 3846536896697971036 n
Next Story

የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ፀጋ አራጌ ብልፅግናን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሰሱት

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop