ለቸኮለ! ማክሰኞ ጥር 17/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የከተማና መሠረተ ልማት ሚንስቴር ካለፉት 3 ዓመታት ወዲህ አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ከተሞች አስከፊ ደረጃ ላይ የደረሰውን ሕገወጥ የመሬት ወረራ ለማስቆም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እገዛ እንዲያደርግለት ለምክር ቤቱ ባቀረበው ሪፖርት ጠይቋል። ድርጊቱ የተባባሰው፣ መንግሥት የመሬት ወረራን የሚያስቆም ወይም የሚያስቀር ሕጋዊ ማዕቀፍ ባለመዘርጋቱ እና ከተሞች የአስተዳደር ወሰናቸውን ያልከለሉና የመሬት ሃብታቸውን ቆጥረው የሚያስተዳድሩበት ሕጋዊ ሥርዓት የሌላቸው በመሆኑ እንደሆነ ተነግሯል። ችግሩ ሀገራዊ ቀውስ መሆኑ እንደማይቀር ያስጠነቀቀው ሚንስቴሩ፣ መፍትሄው ዘመናዊ የመሬት ምዝገባ ሥርዓትና ፍትሃዊ አስተዳደራዊ መዋቅር መዘርጋት እንደሆነ ገልጧል። ዝርዝሩን -https://bit.ly/3nVCGoX

2፤ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከነሐሴ ጀምሮ በመሬት ነክ አገልግሎቶች ላይ ጥሎት የቆየውን እገዳ ማንሳቱን የአስተዳደሩ ቃል አቀባይ ቢሮ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። አስተዳደሩ እንደገና ከጀመራቸው አገልግሎቶች መካከል፣ ለሕጋዊ ይዞታዎች የዋስትና ዕዳ ምዝገባ፣ የፍርድ ቤት እና የባንክ እግድ ምዝገባ እና ስረዛ እንዲሁም እግድ ማጣራት፣ የስም ዝውውር፣ ለነባር ይዞታዎች የቦታ ኪራይ እና የቤት ግብር ተመን፣ የንብረት ግመታ፣ የወሰን ማስከበር ሥራዎች እና ለልማት ተነሺዎች የሚሰጡ አንዳንድ አገልግሎቶች ተጠቃሽ ናቸው።

3፤ በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤት አማጺው ሕወሃት በአፋር ክልል ላይ በከፈተው አዲስ ጥቃት ሳቢያ ከአፋር ክልል ወደ መቀሌ የምግብ ዕርዳታ ጭነው የሄዱ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ካሚዮኖች ወደመጡበት ለመመለስ እንደተገደዱ በትዊተር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ይህም ሕወሃት ለጦርነት እና ለፖለቲካዊ ዓላማው ሲል የትግራይን ሕዝብ ሆን ብሎ ለርሃብ እየዳረገው መሆኑን ያሳያል- ብሏል ቋሚ መልዕክተኛው። በሕወሃት ጥቃት የተነሳ ስንት ካሚዮኖቹ እንደተመለሱ ግን ቃሚ መማዕክተኛው አልገለጸም። የዓለም ምግብ ድርጅት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ስለጉዳዩ ያለው ነገር የለም።

  1. የዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኻኖም በድጋሚ ዕጩ ሆነው እንዲቀርቡ እንደመረጣቸው ዓለማቀፍ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ዶ/ር ቴዎድሮስ ድርጅቱን ለተጨማሪ አምስት ዓመታት እንዲመሩ ዕጩነታቸው የጸደቀላቸው፣ 34 አባላት ያሉት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ዛሬ በጀኔቫ በሚስጢር በሰጠው ድምጽ ነው። በቦርዱ ውሳኔ መሠረት፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ በመጭው ግንቦት 192ቱ የድርጅቱ አባል ሀገራት በጠቅላላ በሚያደርጉት የዋና ዳይሬክተር ምርጫ ብቸኛው ዕጩ ሆነው እንደቀርቡ ያስችላቸዋል። የዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የኬንያ ጤና ጥበቃ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ፓትሪክ አሞት ናቸው።
ተጨማሪ ያንብቡ:  የአረና አመራሮች በሐውዜን ከተማ አዳራሽ ውስጥ ታግተዋል

5፤ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንደኛው መስራች የሆነው በርታ ብሄረሰብ ስያሜውን በመለወጥ “ቤንሻንጉል ብሄረሰብ” ተብሎ እንዲጠራ የብሄረሰቡ ምክር ቤት ዛሬ መወሰኑን የክልሉ መገናኛ ብዙኀን ዘግቧል። የብሄረሰብ ምክር ቤቱ የስያሜ ለውጡን የውሳኔ ሃሳብ ያጸደቀው በቀረበለት ጥናት ላይ ተመስርቶ እንደሆነ ተገልጧል። ብሄረሰቡ መጠሪያውን የቀየረው “በርታ” የሚለው ስያሜ በ1983 ዓ.ም ሕወሃት በብሄረሰቡ ላይ በግዳጅ የጫነው በመሆኑ ነው ተብሏል።

6፤ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት በሰላም እንዲቋጭ የምትፈልገው የመሠረተ ልማት ግንባታዋ በኢትዮጵያ ሰላም ላይ የተመሠረተ በመሆኑ እንደሆነ መናገራቸውን የሀገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ በቴሌኮም አገልግሎት የተሰማራውን የኬንያውን ሳፋሪኮም ኩባንያ ለዚሁ በአብነት ጠቅሰዋል። ኬንያታ ይህን ያሉት፣ በምሥራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድን በአካል ካነጋገሩ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት ነው። ኬንያ የገነባችውን አዲሱን ላሙ ወደብንም ይጠቀሙበታል ተብለው የሚጠብቁት ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ናቸው።

7፤ የአልጀሪያው ፕሬዝዳንት አብዱልመጅድ ተቦርን በግብጽ እያደረጉት ባለው ኦፊሴላዊ ጉብኝት በሕዳሴ ግድብ ውዝግብ ዙሪያ ከግብጹ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጋር እንደሚወያዩ የአልጀሪያ መንግሥታዊ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። አልጀሪያ የግድቡን ውዝግብ በሰላም ለመፍታት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ስታደርግ እንደቆየች ዘገባው ጠቁሟል። አምና በሐምሌ የአልጀሪያው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ራምታኔ ላማምራ በኢትዮጵያ እና ሱዳን ኦፊሴላዊ ጉብኝት አድርገው የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ ዓረብ ሊግ በሕዳሴ ግድብ ላይ የያዘውን የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲያስተካክል አልጀሪያ የበኩሏን ጥረት እንድታደርግ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ

ላማምራን እንደጠየቋቸው ይታወሳል። [ዋዜማ ራዲዮ]

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share