ሃይማኖትንና ሃይማኖታዊ በዓላትን መንግሥት የግጭት መነሻ ከማድረግ ይቆጠብ!

ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ጭምር የምትታወቅበት በአብሮነት የመኖር፣ የመረዳዳት፣ የመተሳሰብ እና የመቻቻል ውብ የሆነው እሴታችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመንግሥት መዋቅር ድጋፍ ጭምር ከፍተኛ አደጋ ውስጥ የወደቀ ሲሆን በዚሁ ከቀጠልን ደግፈው የያዙት ጠጠሮች ተበትነው እንደማኅበረሰብ አንድ አድርገው ያቆዩንን መልካም ወዳጅነት እንዳናጣ እንሰጋለን፡፡

የቀድሞው አገዛዝ በሕዝብ መራር ትግል እንዲያከትም ከተደረገ በኋላ በትረ ሥልጣኑን የያዙት አመራሮች ሀገራችንን ወደተሻለ ሰላም እና እድገት ያደርሷታል ተብሎ ቢጠበቅም እየተደረገ ያለው ግን ከሚጠበቀው በተቃራኒ እየሆነ በየቀኑ የምንሰማው በሙሉ አሳዛኝና አሸማቃቂ ከሆነ ከርሟል፡፡ ከጊዜ ጊዜ ይታረማሉ ተብለው የታሰቡ ጉዳዮችም ይልቅ ስር እየሰደዱ ለማኀበረሰባችን አብሮ መኖር እንቅፋት እየሆኑ የመጡ ሲሆን በፀጥታ እና የመንግስት መዋቅሮች የሚፈፀሙ ተግባራት ደግሞ ችግሩን የበለጠ እያወሳሰቡት ይገኛሉ፡፡

በትላንትናው ዕለት ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም የቃና ዘገሊላ በዓል ሲከበር በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ከሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ በተለይም የወይብላ ቅድስት ማርያም እና ታቦተ ቅዱስ ሚካኤል ወደ ቤተክርስቲያን በመመለስ ላይ ሳሉ የጸጥታ አካላት በፈጸሙት አላግባብ የሆነ ድርጊት ብዙ ሰዎች በመረጋገጥ፣ በድብደባ ጉዳት ሲደርስባቸው ቁጥራቸው በውል ያልተረጋገጠ የበዓሉ ታዳሚዎች ውድ ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡

የኦሮሚያ የፀጥታ ዘርፍ አካላት ታቦታቱ እየተመለሱ ባለበት ወቅት ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ማለፊያውን መንገድ አጥረው በመያዝ ታቦታቱን ያጀቡ ምዕመናን አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያለባቸውን ማንኛውንም ቁሶች (ግንባር ላይ የሚታሰር፣ እጅ ላይ የሚደረግ፣ የሴቶች የሀገር ባህል ቀሚስ ጥለት፣ ቲሸርት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን መገልገያ የሆኑ ከበሮዎችን) ይዘው እንዳይገቡ በመከልከላቸው ከፍተኛ የሆነ ችግር ተፈጥሯል፡፡ በዚህም ግጭት ሃይማኖታዊ በዓሉ በጸጥታ አካሎች ምክንያትነት ከመረበሹም በላይ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ሊደርስ ችሏል፡፡ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥፋት ያጠፉ አካላት ድርጊታቸው በአግባቡ ተጣርቶ እርምጃ ሳይወሰድባቸው በመቅረቱ ተመሳሳይ ጥፋቶች እንዲበራከቱ በር ከፍቷል፡፡ የፀጥታ ሀይሎች የሕዝብን ደሕንነት ከማስጠበቅ ይልቅ እራሳቸው ስጋት ከመሆን መታረም አለባቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የተመድ የሰብዓዊ መብት ም/ቤት በአማራ ጉዳይ | “ተፀፅችያለሁ ይቅርታ ለመጠየቅ እፈልጋለሁ” አብይ | የመራዊ ፖሊስ ጣቢያው ሙሉ በሙሉ በእሳት ጋየ

ሀገራችንን ወደ ሃይማኖት ግጭት ለማስገባት ቀን ከሌት የሚጥሩ ኃይሎች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ጭምር ተሰግስገው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አካላትን የሚቆጣጠር አቅም እና ፍላጎት ያለው ተጠያቂ የሆነ አመራር ባለመኖሩ ልንወጣው ወደማንችለው ችግሮች ውስጥ እየገባን እንገኛለን፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ ይህን የመሸከም ጫንቃ የሌላት በመሆኗ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ለጠፋውም ጥፋት ይቅርታ ሊጠይቅ እንዲሁም ከቤተክርስቲያኗ ሀላፊዎች ጋርም በመምከር ችግሮች ዳግም እንዳይፈጠሩ ሊሰራ ይገባል፡፡ ይህም ጉዳይ እንደ ከዚህ ቀደም ኩነቶች እናጣራለን ተብሎ ብቻ የሚተው እንዳይሆን በፅኑ እናሳስባለን፡፡

ኢዜማ ይህን መሰል ችግር ድጋሚ እንዳይፈጠር በጋራ መሠራት እንዳለበት የሚያምን ሲሆን በዚህ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ያሳውቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተፈጠረውን ችግር በጽኑ ያወግዛል፡፡ ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን ይመኛል፡፡

የ #ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ)

ጥር 14 ቀን፣ 2014 ዓ.ም

1 Comment

  1. መቸም እጅግ አስከፊውና አደገኛው የተረኞች ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የማያስቆጣውና ለማውገዝ የሚዳዳው ጤናማ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለሽኝም። ከዚህ መሪር እውነታ አንፃር ከነልፍስፍስነቱም ቢሆን ሲታይ መግለጫው ተገቢ ብሎ ለመግለፅ አያስቸግርም።

    ችግር የሚኖረው እውን —? የሚል እጅግ ፈታኝና ግልፅ ጥያቄ ሲነሳ ነውና ይህንኑ በሚመለከት የሚከተለውን ልበል፦

    መከረኛው የአገሬ ህዝብ ከእንዲህ አይነት የፖለቲካ ውድቀትና የሞራል ጉስቁልና (ባዶ የመግለጫ ጋጋታ) እንዴትና መቸ ሊላቀቅ እንደሚችል ከምር ሲያስቡት በእጅጉ ይከብዳል (ያስጨንቃል) ።
    መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ እውን እስካልሆነ ድረስ ፈፅሞ እረፍት እንደሌላቸው በየአደባባዩ፣በየአዳራሹና ባገኙት ሌላ አጋጣሚ ሁሉ “ቃል ለምድርም ለሰማይም” ሲሉንና ሲያስጨበጭቡን የነበሩ የቀድሞ ግንቦት ሰባቶችና የአሁኖቹ ኢዜማዎች ቃላቸውን ቀርጥፈው በመብላት የሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ ተረኛ ኢህአዴጎችን “መቶ በመቶ እናምናቸዋለን ፤ ያሻግሩናልም” በሚል በአስከፊ የፖለቲካ አመንዛራነት ውስጥ መዘፈቃቸውን ጨርሶ ማስተባበል አይቻልም ።
    ይህ ብቻ ይደለም የእነዚህ ወገኖች ውደቀት ። የሸፍጠኛ፣ የሴረኛ፣ የፈሪና የጨካኝ ተረኛ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች የካቢኔ አባልነትን ሹመት አከናንበው ይበልጥ ታማኝ አገልጋዮቻቸው ሲያደርጓቸው የእኩይ ፖለቲካ ሥርዓት መሣሪያ በሆነው ህገ መንግሥት ተብየ ስም ቃለ መሃላ በመፈፀም እጅ ነስተው የተቀበሉ እለት ነበር ከደመ ነፍስ እንስሳት በታች በሚያወርድ የፖለቲካ ሰብእና ውስጥ የተዘፈቁት።
    ለዚህ ነው ክስተትን እየተከተሉ የሚያስነብቡን ወይም የሚያሰሙን የመግለጫ ጋጋታ ፈፅሞ ስሜት የማይሰጠው ።
    በእውነት ለእውነት ከተነጋገርን መከረኛው ህዝብ ያካሄዳቸውና መሪር መስዋእትነት የከፈለባቸው የዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንቅስቃሴዎች በተደጋጋሚና በአሳዛኝ ሁኔታ እየከሸፉ መላልሶ በመከራውና በውርደቱ አዙሪት ተጠልፎ እንዲወድቅ ካደረጉበት ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ይኸው እጅግ አሳዛኝ እውነታ ነው።
    ይህም አልበቃቸው ብሎ እጅግ በለየለት ርካሽ የፖለቲካ ተውኔት መግለጫ እያስነበቡ “እመኑን የለውጥ ሃይላት ነን” ሲሉን ህሊናቸውን ጨርሶ አይጎረብጠውም።
    ቀን መግለጫውን አስነብበውን ማታ ማታ ከተረኛ ኢህአዴጋዊያን ጋር ስለ ታማኝነታቸው ቁርጠኝነት የሚተርኩ ወገኖችን “ነውር ነውና ወደ ትክክለኛው ህሊናችሁ ተመለሱ ወይም በአስከፊው ፖለቲ ወለድ ወንጀል ይበልጥ ከምትጨማለቁ ይበቃልና አርፋችሁ ተቀመጡ “ ሊባሉ ይገባል። አዎ! ቤተ መንግሥቱን በተቆጣጠረው የገዳይ፣ የአስገዳይና የአገዳዳይ ኢህአዴጋዊያን ሥርዓት ላይ ተለጥፎ የሥርዓቱ መሥራችና የበላይ አለቃ የነበረውን እኩይ የህወሃትን ቡድን ለቁጥርና ለአይነት የሚታክት ስያሜ እየሰጡ ማውገዝና መራገም እንኳንስ የዴሞክራሲ ስሜትሊኖረው የለውጥ ሽታም የለውም።
    እናም ከምር ለአገር (ለወገን) የሚጨንቀን ከሆነ ከዚህ አይነት እጅግ ወራዳና አዋራጅ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ በመውጣት መቀረኛው ህዝብ ይበልጥ ነቅቶና ተደራጅቶ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ያደርግ ዘንድ ተገቢና ወቅታዊ እገዛ ማድረግ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share