“ወደ ተከዜ ግንባር የዘመትኩት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተጋድሎን ለመቀላቀል ነው” ረዳት ፕሮፌሰር አማረ ጥጋቡ

አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይልን ለማጥፋት ባለ ሀብቶች፣ አርሶ አደሮች፣ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ ምሁራን እንዲኹም የተለያዩ በርካታ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊውን ወደ ግንባር ዘምተዋል፣ እየዘመቱም ይገኛሉ። የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘመቻዉን መቀላቀላቸው ለመከላከያ ሠራዊቱ ጠንካራ ደጀን መኾናቸውን ያሳዩበት ነው።

የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን ያነጋገራቸው የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አማረ ጥጋቡ በየ ግንባሩ የሽብር ቡድኑን ለሚደመስሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ክብር መስጠት የሚያንስበት ነው ብለዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሕዝብ ሕልውና ሲባል ጀብዱ እየፈጸመ ይገኛል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ መከላከያ የበለጠ ድል እንዲያስመዘግብ ጠንካራ የሕዝብ ደጀንነት ያስፈልገዋል ብለዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሀገር እንደ ሀገር ሕዝብም እንደ ሕዝብ ሉዓላዊነታቸውና ክብራቸው ተጠብቆ እንዲቀጥሉ ህይወቱን የሚሰጥ የቁርጥ ቀን ልጅ በመሆኑ ክብር የሚገባው እንደሆነም አስረድተዋል።

እኔ በበኩሌ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ የሚሰጠኝን ተልዕኮ ኹሉ በመወጣት ደጀንነቴን በተግባር ለማሳየት ዘምቻለሁ። በየ ማኅበራዊ ሚዲያው የሚሰራጨውን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ አይቼና ሰምቼ ውዥንብር ውስጥ ከምገባ በተግባር ለሀገሬ ተጋድሎ ባደርግ የተሻለ ስለኾነ ነው የዘመትኩትብለዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር አማረ እንዳሉት ጠላትን በአጭር ጊዜ ለማጥፋት ሀገራዊ ተልዕኮን ኹሉ ለሀገር መከላከያ ሠራዊትና ለወገን ዘማቾች ብቻ መተው ሳይኾን የሕዝባዊ ማእበል ርብርብ ወሳኝ ነው። ጠንካራ የሕዝብ ደጀንነት በታዩባቸው አካባቢዎች ጠላት ንፍሮ እንደሆነ በምሳሌነት ጠቅሰው አስረድተዋል። በተለይ በአሁኑ ወቅት ወጣቱ የሚጠበቅበትን ተጋድሎ ከማድረግ በተጨማሪ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት እግርን በመከተል ቁሳቁስን መሸከም፣ ትኩስ ስንቅ ማቀበል፣ ሞራል መስጠት ይጠበቅበታል ብለዋል። ወጣቱ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ውጣ ውረድን የሚቀንስ ተግባር መፈጸም እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በግንቦት 7-አርበኞች ግንባር ውህደትና በኢሳት ጋዜጠኞች የአስመራ ጉዞ ዙሪያ ለህብር ራድዮ የሰጠው ቃለምልልስ

መታገል መስዋእትነትን ይቀንሳልያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ጠላትን በትግል አንገቱን አንቆ በመድፋት በነፃነት የሚኖር ትውልድ መፈጠር አለበት ብለዋል። አሸባሪው ኀይል ሕፃናት፣ አረጋውያን፣ ነፍሰጡር እናቶችን ሳይቀር እያሰቃየ ወጣቶች ይህን አረመኔ ኀይል ለማጥፋት መነሳት አለባቸው ብለዋል። ረዳት ፕሮፌሰሩ ወደ ግንባር የዘመቱት ነፃነትን ለማጣጣምና ቀጣዩ ትውልድ በሰላም እንዲኖር በማሰብ እንደኾነም ጠቁመዋል።

ኹሉንም ዋጋ ለመክፈል ወደኋላ ለማይመለስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ መስጠት፣ መዘመር፣ ማወደስ፣ ማክበር፣ ማንገሥ፣ ከፍ ከፍ ማድረግና እሱ የሚኾነውን ኹሉ መኾን ያንስበታል እንጂ አይበዛበትምብለዋል።

ወጣቱ ወደ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መቀላቀል እንደሚገባው ያሳሰቡት ምሁሩ በተለይ የአማራ ሕዝብ ነገ ጀኔራልና ኮማንደር የለንም ብሎ ከሚጠይቅ ጀኔራልን ለማፍራት ዛሬ ወደ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መቀላቀል እንዳለበት አስገንዝበዋል። በተለይ የአማራ ሕዝብ ሕልውናውን ለማስጠበቅ የመጨረሻውን ትንቅንቅ በማድረግ አሸባሪውን መቅበር እንደሚገባው ረዳት ፕሮፌሰሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:-ቡሩክ ተሾመከተከዜ ግንባር

 

ሕዳር 17/2014 .(አሚኮ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share