ለቸኮለ! ሰኞ ሐምሌ 19/2013 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዩኒቨርስቲው ባዘጋጀላቸው አውቶብሶች በአፋር ክልል ዞን ሁለት አብዓላ በተባለ ቦታ በኩል ከአፋር ክልል ዋና ከተማ ሠመራ እንደገቡ ተማሪዎቹ ለዋዜማ ተናግረዋል። ተማሪዎቹ ሠመራ የገቡት በመከላከያ ሠራዊት ታጅበው ነው። ተማሪዎቹ ዛሬ ማምሻውን ወደ ቤተሰቦቻቸው እንደተሸኙ የሠመራ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ለዋዜማ ተናግረዋል። በተያያዘ 45 የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአውቶብስ ራያ ዞን ቆቦ ከተማ የገቡ ሲሆን፣ ሆኖም በቅርብ ርቀት ሮቢት ከተማ ላይ የተኩስ ልውውጥ በመኖሩ ወደ ሰሜን ወሎ ዞን ወልድያ ከተማ እንዳያልፉ የሕወሃት ተዋጊዎች አግደዋቸው እንደነበር ተማሪዎቹ ለዋዜማ ተናግረዋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም። የአዲግራት እና አክሱም ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ያሉበትን ሁኔታ ግን እስካሁን ማወቅ አልተቻለም።
2፤ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ሕወሃት በሀገሪቱ ሕልውና ላይ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን እንዲቆሙ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ ማድረጋቸውን የከተማዋ ፕሬስ ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። በሕወሃት መሪነት በኢትዮጵያ ላይ የውክልና ጦርነት እንደተከፈተባት የገለጹት ምክትል ከንቲባዋ፣ እስካሁን መከለከያ ሠራዊቱን ያልተቀላቀሉ ወጣቶች በፍጥነት እንዲቀላቀሉ ጠይቀዋል።
3፤ ወደ ቦሌ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ያመሩ አውሮፕላኖች በአየር ማረፊያው አከባቢ በተፈጠረ ጭጋጋማ አየር ጠባይ ሳቢያ ማረፍ እንዳልቻሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትዊተር ገጹ አስታውቋል። ለጥንቃቄ ሲባል አውሮፕላኖቹ በአቅራቢያ በሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች እንዲያርፉ ማድረጉን ገልጧል። አየር ጠባዩ ሲስተካከል ሁኔታው ወደነበረበት እንደሚመለስ የጠቆመው አየር መንገዱ፣ ለጊዜው ለተፈጠረው መጉላላት መንገደኞችን እና አየር መንገዶችን ይቅርታ ጠይቋል። የተጠቀማቸውን አማራጭ አውሮፕላን ማረፊያዎች ግን አየር መንገዱ አልጠቀሰም። ዛሬ በርካታ አውሮፕላኖች ወደ ቦሌ ሲበሩ ውለዋል።
4፤ ማንኛውም በኢትዮጵያ አየር ክልል የሚበሩ አውሮፕላኖች መንግሥት ያወጣውን አዲስ የበረራ መመሪያ እንዲያከብሩ የመንግሥት የወቅታዊ ሁኔታዎች መረጃ ማጣሪያ በትዊተር ገጹ አሳስቧል። የአውሮፕላን አብራሪዎች እና የበረራ ኦፕሬተሮች መንግሥት ያወጣውን አዲስ የበረራ መረጃ ማሳወቂያ መመሪያ የሚጥሱ ከሆነ፣ ለሚደርሰው ጉዳት ሁሉ ሃላፊነት ይወስዳሉ ሲል መረጃ ማጣሪያው አስጠንቅቋል። ወደ ትግራይ ክልል ለሰብዓዊ ዕርዳታ በረራ ለሚያደርጉ ረድዔት ድርጅቶች መንግሥት ባለፈው ሰኔ 23 አዲስ የበረራ መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል።
5፤ በማይጠብሪ፣ በዋግ ኽምራ ልዩ ዞን በአበርገሌ ወረዳ እና በራያ አላማጣ አካባቢ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ሚሊሻዎች በአማጺው የሕወሃት ተዋጊዎች ላይ በርካታ ድሎችን እየተጎናጸፉ እንደሆነ የአማራ ክልል ኮምንኬሽን ሃላፊ ግዛቸው ሙሉነህን ጠቅሶ የክልሉ መገናኛ ብዙኀን ኮርፖሬሽን ማምሻውን ዘግቧል። መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ሕወሃት ከሚነዛው ፕሮፓጋንዳ የተለየ እንደሆነ ሃላፊው አመልክተዋል። ቀደም ሲል በሕወሃት ተዋጊዎች ተይዘው ሰሞኑን የክልሉ ልዩ ኃይል እና ሚሊሺያ በወሰደው መልሶ ማጥቃት ያስለቀቃቸው አካባቢዎች ስለመኖራቸው ግን ዘገባው በስም አልጠቀሰም።
[ዋዜማ ራዲዮ]
ተጨማሪ ያንብቡ:  ተመስገን በቀለ-ፋኖ ገሰገሰ- New Ethiopan music 2024

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share