የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ተካበ ዘውዴ የእናንተን እርዳታ ይፈልጋል

ተካበ ዘውዴ በኢትዮጵያ ታሪክ በችሎታው፣ በክብርና በህዝብ መወደድ ዋና ከሚባሉት የኢትዮጵያ አትሌቶች አንዱ ነው። የተካበ ተወዳጅነት በእግር ኳስ ተጫቾች ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ነው። ተካበ ዘውዴን ደግሞ ቀርበን ለምናውቀው በኳዝ ሜዳም ይሁን ውጭ ትልቅ ስብዕና ያለው፣ ጨዋ እና ጠንካራ ሰው ነው።

ባለፈው ወር ወንድማችን ተካበ ዘውዴ በካንሰር በሽታ እንደተያዘ አውቀናል። ይህ ዜና ሁላችንንም ያስደነገጠ ነገር ነው። ለተካበ ደግሞ ይህ በሽታ በህይወቱ ካጋጠሙት ፈተናዎች ዋናው ነው። ተካበም ይህንን ፈተና በሚገርም ግርማ ሞገስ እንደሚፋለመው ለአነጋገሩት ሰዎች ሁሉ ይናገራል። የተካበን የመንፈስ ጥንካሬ ብዙዎች የምናውቀው ቢሆንም በዚህ አስጊ ጊዜ በአለም ዙሪያ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን እሱንም፣ ባለቤቱንና ሁለት ልጆቹን በፀሎት እንድታስቧቸው እንጠይቃለን።

በኢትዮጵያ የበረኝነት ዘመን ከድሬዳዋ የካቲት 66፣ ድሬዳዋ ከነማ፣ ድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅና፣ ሐረርጌ ምርጥ እስከ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለሃገሩ ትልቅ ደስታን የሚፈጥሩ ትውስታዎችን የተወ ሰው ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ በ1980 ዓ.ም. በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ሁለት የፍፁም ቅጣት በማዳን፣ ሶስተኛውን ደግሞ የዚምባቡዌን ተጫዋች አርበትብቶ እንዲስት በማስደረግ ኢትዮጵያን የዋንጫ ባለቤት ያደረገበት ጨዋታ የማይረሳ ነው። ተካበ ዘውዴ አሜሪካን አገር ከገባበት ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በተጫዋችነት፣ አሰልጣኝነት፣ ቦርድ አባል እና ስራ አመራርነት እስከ አሁን ድረስ ለ28 አመታት ያገለግላል። በየትኛውም ሃላፊነቱ ተካበ በስራው ሁሉ ተወዳጅ እና ተግባቢ ሰው ነው።

ውድ ኢትዮጵያውያን! የካንሰር እና ተመሳሳይ በሽታዎች ቤተሰብና ታማሚው ላይ ከፍተኛ የገንዘብ ጫና እንደሚፈጥሩ የታወቀ ነው። ተካበ ዘውዴ ህይወቱን በሙሉ ለኢትዮጵያውያን እንደቆመ እኛም ለእርሱና ለቤተሰቦቹ የምንቆምበት አጋጣሚ ደርሶናል። ከሶስት አስርት አመታት በላይ ለዚህ ኢትዮጵያዊ ጀግና ምን አድርጌ ልካሰው ካላችሁ በዚህ ሊንክ ላይ በመሄድ ልባችሁ የፈቀደውን እንድትለግሱ በትህትና እንጠይቃችኋለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በግላቸው የሚሰሩ እንዴት ለጡረታቸው ገንዘብ ማጠራቀም ይችላሉ? - ጉዳዩ ለትናንሽ ድርጅቶች የሚሰሩትንም ያጠቃልላል

ተካበ ዘውዴ ህክምናውን በሰላም ጨርሶ፣ በተሻለ ጥንካሬና ጤንነት እንደምናገኘው እምነታችን ፅኑ ነው። እግዚአብሔር እድሜውን ያርዝምለት! ቤተሰቦቹንም ይባርክ!

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share