ፍርድ ቤቱ በአቶ በቀለ ገርባ ላይ ተጨማሪ 8 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአቶ በቀለ ገርባ ላይ ተጨማሪ ስምንት ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የአራዳ ተረኛ ወንጀል ችሎት ጉዳያቸው ታይቷል።

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት እጃቸው አለበት ተብለው በተጠረጠሩት አቶ በቀለ ገርባ ላይ ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው 14 ቀናት ጠይቆ ስምንት ተጨማሪ ቀናት ተፈቅዶለታል።

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ባለፉት 11 ቀናት አከናወንኩ ያላቸውን ተግባራት በዝርዝር አቅርቧል።

በዚሁ መሰረት በተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ቀናት የተጠርጣሪዎችንና የምስክሮችን ቃል መቀበል እንዲሁም በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት የማጣራት ተግባራት ማከናወኑንና ከመዝገብ ጋር ማያያዙን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

መርማሪ ፖሊስ ባደረገው ማጣራት በተፈጠረው ሁከት በሶስት ተቋማት ብቻ ከ166 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት መውደሙን የሚገልጽ ማስረጃ ማግኘቱን ገልጿል።

በቡራዩ በደረሰ ጉዳት የአራት ሰው ህይወት መጥፋቱንና አራት ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው እንዲሁም ሰባት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ንብረት እንደወደመ በማስረጃ ማረጋገጡን ገልጿል።

በተለያየ አካባቢ ሁከት እንዲነሳ የስልክ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ተከትሎ መልዕክት የተቀበሉ ሰዎች ያደረሱትን ጉዳት እያጣራ እንደሚገኝ አስረድቷል።

በክልል የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ 17 ቡድን መንቀሳቀሱን ገልጾ፤ የቡድኑን ውጤት እየተጠባበቀ እንደሚገኝም አመልክቷል።

ቀሪ የምርመራ ስራዎች እንዳሉት ያመለከተው መርማሪ ፖሊስ፤ ቀሪ ምስክር መስማት፣ ሽጉጦችን ለፎረንሲክ ምርመራ ልኮ ውጤት እየጠበቀ እንደሚገኝ ጠቅሷል።

በንብረት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን በደብዳቤ ጠይቆ ከተቋማት ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጾ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

በወንጀል ድርጊት የጠረጠራቸው አቶ በቀለ ገርባ መርማሪ ፖሊስ ቃል እንዳልተቀበላቸው ገልጸዋል።

የተጠረጠሩበት ወንጀልም እሳቸውን እንደማይመለከት ተናግረዋል።

መርማሪ ፖሊስ ያቀረበውን ተጨማሪ 14 ቀናት የሚወስድ የምርመራ ጊዜ አለመኖሩንም ገልጸዋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆችም ደንበኛቸው ላይ ፖሊስ ያቀረበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ ደንበኛቸው የዋስ መብታቸው ተጠብቆ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

”መርማሪ ፖሊስ የሚያቀርበው የጅምላ ክስ በመሆኑ ደንበኛችንን የሚመለከት ብቻ እንዲያቀርብ” ሲሉ ጠይቀዋል።

ተጠርጣሪውና ጠበቆቻቸው የመገናኛ ብዙሃን ውሳኔ ባልተሰጠበት ጉዳይ ላይ ዘገባ እያቀረቡ በመሆኑ ትዕዛዝ ይሰጥልን ሲሉም ጠይቀዋል።

ጠበቆች ደንበኛቸውን ለማግኘት እንደተቸገሩ በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ አቶ በቀለ የተጠረጠሩበት ወንጀል ስፋት ያለው፣ ውስብስብና ሌሎች ግብረ አበሮች ያሉበት በመሆኑ የተጠርጣሪው ምርመራ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ሊለያይ እንደማይችል ገልጿል።

የምርመራ ስራውን በፍጥነት ለመጨረስ እየተሰራ ቢሆንም በየአካባቢው የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት ጊዜ የሚወስድ መሆኑን አስረድቷል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በሳምንት ሶስት ቀን ከደንበኛቸው ጋር እንዲገናኙ ፕሮግራም ቢወጣም ጠበቆች በተናጠል በመሄድ ፕሮግራሙን እያከበሩ እንዳልሆነ ገልጾ፤ በፕሮግራሙ መሰረት መስተናገድ ካልቻሉ ማጣራት አድርጎ የማስተካከያ ርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጧል።

ግራ ቀኙን ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ መርማሪ ፖሊስ ከዚህ ቀደም በተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በአግባቡ ማከናወኑን አይቷል።

ከወንጀሉ ስፋትና ውስብስብነት አንጻር ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደሚያስፈልገው በመግለጽ ተጨማሪ ስምንት ቀናት በመፍቀድ ለሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ተጠርጣሪና ጠበቆች መገናኛ ብዙሃንን በተመለከተ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ላቀረቡት አቤቱታ መገናኛ ብዙሃኑ በዘገባቸው ያቀረቡትን ጉዳይ የሚመለከት ዝርዝር አቤቱታ ቀጠሮ ሳይጠብቁ እንዲያቀርቡና አቤቱታው አግባብ ሆኖ ከተገኘ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ገልጿል።

በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩት እነ አራፋት አቡበከር እና እነ አዲሱ ቶሎሳ ላይ መርማሪ ፖሊስ ያደረገውን ማጣራት አቅርቦ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል።

ግራ ቀኙን ያደመጠው ፍርድ ቤቱም ተጨማሪ የምርመራ ቀናት በመፍቀድ ለነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ኢዜአ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.