የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 78ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ ውሳኔ ያሳለፈባቸው ጉዳዮች፦
1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን ህጋዊ ሰውነት ለመስጠት በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ህጋዊ ሰውነት እንዲኖረው በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ህጋዊ ሰውነት እንዲሰጠው በሙሉ ድምጽ በመወሰን ረቂቅ አዋጁ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ምርምርና ልማት ማዕከል ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ በዚህም ሀገራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ በምርምር፣ ልማት እና ትግበራ የተመሰረቱ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አገልግሎቶች፣ ምርቶች እና መፍትሄዎችን መስጠትና የልህቀት ማዕከል ማቋቋም በማስፈለጉ እና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዙሪያ ላይ ለሚሰሩ ጀማሪ አልሚዎች ምቹ ምህዳር መፍጠር የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ ተቀባይነት ስላገኘ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ እንዲወጣና በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

3. የሲቪል አቪዬሽን አዋጅን ለማሻሻል የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ሌላው በምክር ቤቱ የታዬ ጉዳይ ነው፡፡ነባሩ የማስፈጸሚያ አዋጅ በቆየባቸው የትግበራ ዓመታት ውስጥ በህግ ያልተሸፈኑ አዳዲስ አስተሳሰቦች እና የቁጥጥር ስርአቶች በመኖራቸው የሰው ሀብት ስምሪትና የተፈላጊ ብቃት ተለዋዋጭነት መኖሩ በተለይም ከዘርፉ ልዩ የስራ ባህሪ አንጻር የአቬዬሽን ዘርፉን ለመምራት እና ለመቆጣጠር፣ የበረራ ደህንነትን ለማረጋገጥ እና የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ አለማቀፍ ድርጅቱ በየጊዜው የሚያወጣቸው ምክረ ሀሳቦች፣ ደረጃዎችና የተመረጡ አሰራሮች ተግባራዊነት ጋር በተያያዘ ክፍቶቶች በመፈጠራቸው እነዚህን ክፍተቶች በሚሞላና የወደፊት የኢንዱስትሪውን እድገት በጠበቀ መልኩ ለመደገፍ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሸዋ ሮቢት በፋኖ ቁጥጥር ስር ሆነች | ጀነራሉ ወደሰማይ ተሸኘ | የፕሬዝዳንቷ ለቅሶ | አባይ ብርጌድ ፍኖተ ዳሞት ሻለቃ

4. ም/ቤቱ ሌላው የተወያየበት ጉዳይ አገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ረቂቅ ስትራቴጂ ነው፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ፍትህ ፖሊሲ ጊዜው የሚጠይቀውን እና ደረጃውን የጠበቀ የህብረተሰቡን ፍላጎት የሚያረካ በግልጽነትና ተጠያቂነት መርሆዎች ላይ የተመሰረተና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የፍትህ ስርአት ለመገንባት የተፈጸሙ ወንጀሎችን መፍትሄ ከመስጠት ባለፈ ለወንጀል መነሻ ምክንያቶችን በመቀነስ ወይም በማጥፋት ጭምር ለመስራት የሚያስችል አገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ረቂቅ ስትራቴጂ የጠቅላይ አቃቤ ህግ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ምክር ቤቱም በረቂቅ ስትራቴጂው ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ስትራቴጂው በሥራ ላይ እንዲውል ም/ቤቱ ሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

5. ሌላው ም/ቤቱ የተመለከተው የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ነው፡፡በሀገር መከላከያ ሰራዊት ውስጥ የተጀመረው የሪፎርም ስራዎች አንድ አካል የሆነውና በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1097/2011 መሰረት ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎችን ቀደም ሲል ከነበሩበት ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ወደ መከላከያ ሚኒስቴር እንዲዛወሩ ተወስኗል፡፡ በዚሁ መሰረት የደጀን አቪየሽን ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የጋፋት አርማመንት ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የሆሚቾ አሚውኒሽን ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ እና የፊውል /ነዳጅ እና ፕሮፒላንት ንኡስ ኢንዱስትሪ መዋቅራዊ አደረጃጀቱን በአንድ ኮርፖሬሽን ስር በማደራጀት ብቁና ተወዳዳሪ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች መገንባት ይቻል ዘንድ የመከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ እንዲወጣና በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ድምጻችን ይሰማ መግለጫ አወጣ፦ "በህዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች ላይ በማረሚያ ቤት እየተደረገ ያለው ወከባ በአስቸኳይ ይቁም!"

6. በመጨረሻ ም/ቤቱ የተወያየው የማህበረሰብ ተፋሰሶች ልማት፣ አስተዳደር እና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡የአካባቢ መራቆትንና የተፈጥሮ ሀብት መመናመንን በመከላከል፣ የውሃ ሀብትን በማጎልበትና የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት በመቀነስ የመሬት የማምረት አቅም ተጠብቆ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ እና በዚህም ለእርሻ ስራ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥና ለስራ እድል ፈጠራ ምቹ መደላድል ለመፍጠር ይቻል ዘንድ ቀደም ሲል የተጀመሩትን የተፋሰስ ልማት ስራዎች ማስቀጠል አስፈላጊ በመሆኑ የግብርና ሚኒስቴር የማህበረሰብ ተፋሰሶች ልማት፣ አስተዳደር እና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share