ለቸኮለ! የዛሬ ዐርብ ጥር 1/2012 የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1. በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ትናንት ማታ በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ጠብ 1 ተማሪ እንደሞተ DW ከስፍራው ዘግቧል፡፡ ሟቹ የተፈጥሮ ሳይንስ 1ኛ ዐመት ተማሪ ነው፡፡ 44 ተማሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው፡፡ የሟቹ አስከሬን ወደ ትውልድ ቦታው ወልድያ ተልኳል፡፡

2. በቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ለተቃውሞ የወጡ ተማሪዎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው 1 የ3ኛ ዐመት የኢንጅነሪንግ ተማሪ በጥይት ተመቶ ሕይወቱ አልፏል፡፡ 12 ተማሪዎች ደሞ ቆስለዋል፡፡ ትናንት ቡሌ ሆራን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ በርካታ ዩኒቨርስቲዎች መንግሥት በምዕራብ ኦሮሚያ የሚወስደውን የሃይል ርምጃ በመቃወም ሰልፎች እንዳደረጉ የዘገበው አዲስ ስታንዳርድ ነው፡፡

3. በኦሮሚያ ክልል የታገቱ 17 የአማራ ክልል ተወላጅ ተማሪዎችን መንግሥት እንዲያስለቅቅ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ዛሬ በፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መግለጫ ጠይቋል፡፡ 14 ሴቶች እና 3 ወንድ ተማሪዎች ባልታወቁ አካላት ከታገቱ 1 ወር አልፏቸዋል፡፡ አጋቾቹ በአማራ ክልል ያሉ የኦሮሞ ተማሪዎች በክልላቸው ባሉ ዩኒቨርስቲዎች ካልተመደቡ አንለቃቸውም ማለታቸው ታውቋል፡፡

4. የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጨረሻ የሦስትዮሽ ድርድር ትናንት ያለ ውጤት መበተኑን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡ ተደራዳሪዎች ካልተስማሙ፣ 3ኛ ወገን አሸማጋይ ሊጠይቁ ወይም ጉዳዩን ለሀገሮቻቸው መሪዎች ሊመሩት እንደሚችሉ በ2015ቱ የመግባቢያ መርሆዎች አንቀጽ 10 ላይ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ በፊት ጥር 4 ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በዋሽንግተን ይገናኛሉ፡፡

5. የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት በቀጣዩ ምርጫ ዕጩዎቹን እንደሚያሳትፍ አስታውቋል፡፡ ከከተማዋ ውጭ ደሞ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ቅንጅት ወይም ጥምረት ይፈጥራል፡፡ ለፓርቲ ቅድመ ዕውቅና ዝግጅት ለዕሁድ ስብሰባ ጠርቷል፡፡ ሰኞ ከምርጫ ቦርድ የዕውቅና መጠየቂያ ያስገባል፡፡ ከዚያም የምስረታ ጉባዔ እንደሚያደርግ ሰብሳቢው እስክንድር ነጋ ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች ተናግሯል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  Meles Zenawi’s VOA blacklist unveiled

6. በኢትዮጵያ የተከሰከሰው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ንድፍ ነዳፊዎችን እና የአሜሪካ ሲቪል አቬሽን ተቆጣጣሪ ተቋምን የሚያጋልጡ መረጃዎች እንደወጡ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የኩባንያው ሠራተኞች ኢሜል ልውውጥ እንደሚያሳየው፣ የአውሮፕላኑን ንድፍ የነደፉት ባለሙያዎች ዋዘኞች ናቸው፡፡ በረራ ተቆጣጣሪ ተቋምም ችግር ላለበት እና አብራሪዎች በቂ ስልጠና ላልወሰዱበት አውሮፕላን የበረራ ፍቃድ የሚሰጥ ግዴለሽ ተቋም እንደሆነ በኢሜሎቹ ተጠቅሷል፡፡

7. የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያን (በስም በቀጥታ አልጠቀሷትም) ከቀውስ ያዳንኩ ሁኜ ሳለሁ፣ የኖቤል ሰላም ሽልማቱ ግን ለሀገሪቱ መሪ መሰጠቱ አሳዝኖኛል ሲሉ ባንድ መድረክ ላይ ትናንት ሲናገሩ በMSNBC ቴሌቪዥን ተመልክተናል፡፡ ለሀገሪቱ ሰላም ምን ሚና እንደተጫወቱ አላብራሩም፡፡ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባለስልጣን ግን ትራምፕ የጠቀሱት በኢትዮጵያ እና ግብጽ መካከል የተጫወቱትን ሚና እንደሆነ ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል፡፡
8. የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ፎርማጆ ለ2 ቀናት ጉብኝት ኤርትራ ይገኛሉ፡፡ የጉዟቸው ዐላማ ኤርትራ ባሰለጠነችላቸው ልዩ ሃይሎች ምረቃ ላይ ለመገኘት ነው ተብሏል፡፡ ሱማሊያ በያዝነው የፈረንጆች ዐመት ለምታካሂደው ምርጫ፣ ኤርትራ ተጨማሪ ወታደሮች እንድታሰለጥንላቸው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር እንደሚመክሩ ከሁለቱ ሀገሮች ዜና ምንጮች ተመልክተናል፡፡

(ይህን የዋዜማ ለቸኮለ ዜና በTelegram ቻናል በኩል Wazema Radio ብላችሁ ብትፈለጉንና ብትቀላቀሉን በየቀኑ ማግኘት ትችላላችሁ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share