September 17, 2023
13 mins read

በገዛ ራሳችን መሪር እውነታ ዙሪያ እየዞርን ከቶ የትም አንደርስም!

September 16, 2023

T.G

በተፈጥሮ ወይም በመማር ወይም በልምምድ ወይም በሁሉም የምናገኘው የትኛውም መልካም  የሙያ ዘርፍ በማህበረሰብ ውስጥ ተወልዶ የሚያድግና መልሶ የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ምንነት፣ ማንነት፣ እንዴትነት፣ ከየት ወደ የትነት ፣ እስከ የትነት፣ ስኬትታማነት፣ ድክመት ፣ ወዘተ የሚያንፀባርቅ ወይም የሚያሳይ እና ስኬት ከሆን እንድንገፋበትና ውድቀት ከሆነም በወቅቱ አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምት እንድናደርግ የሚያስችለን መሆን አለበት። መቼም ከገዛ ራሳችን መሪር እውነታ እየሸሸን በመምሰሉና በማስመሰሉ መንገድ መንጎድ ክፉ ልክፍት ስለሆነብን ለመቀበል እየተቸገርን ነው እንጅ ነገረ ሥራችን ሁሉ ከዚህ በተቃራኔው መሆኑን ማስተባበል የምንችል አይደለንም።

ከዚህ በፊት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በእንደነዚህ አይነት ጉዳዮችና ባለጉዳዮች ዙሪያ ሂሳዊ አስተያየት መሰንዘሬን አስታውሳለሁ ። ይህችኛዋ አጭር ሂሳዊ ትዝብቴም ይህንኑ ክፉ ልማድ (ልክፍት) ደፍረን ልንጋፈጠው ባለመቻላችን (ባለመውደዳችን) ወደ መሪሩ እውነት መቅረብ እየፈራን በየሙያ ዘርፋችን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት የሚሻውን ሁለንተናዊ የመከራና የውርደት ምንነታችን፣ ማንነታችን፣ እንዴትነታችን፣እና ከየትና ወደ የትነታችን ፈፅሞ ጉዳያችን አላደረግነውም የሚል መሪር መልእክትን የያዘች ነች።

እንደ ሁልጊዜው ሁሉ የኮሚዲያን እሸቱን የሰሞኑን የሶሻል ሚዲያ ፕሮግራሞች ተከታተልኳቸው። ሂሳዊ አስተያየቴ እንዲህ አይነት ፕሮግራሞች ለምን ይቀርባሉ ሳይሆን አገር በተትረፈረፈ ሰላምና መረጋጋት  ላይ እንደምትገኝ በሚያስመሰል አኳኋን  በየአዳራሹና በየሶሻል ሚዲያው በመውረግረግ ከእኛ ወዲያ የመድረክ ሰውነት ላሳር ነው ማለት ግብዝነት ነው የሚል ነው።

በአግባቡ ቢያዙ መልካምና ውጤታማ ዜጋ ሊሆኑ ለሚችሉ ህፃናት እና ሌሎች ወገኖች የሚመች ሥርዓት የሚሰፍንባት አገረ ኢትዮጵያን ከሚመለከቱ እጅግ ወቅታዊ ከሆኑና የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች እየሸሸን በአግባቡ ቢያዙ ለአገር ትልቅ የሰው ሃብት ሊሆኑ የሚችሉ ድንቅ ልጆችን እና ሌሎች ስሜትን የሚስብ ተሞክሮ ያላቸውን ወገኖች በየመድረኩ እያቀረብን በአዳራሽ ውስጥ ካለው ጭብጨባና መውረግረግ ውጭ ሌላ ዓለም ፈፅሞ የሌለ በሚያስመስል አኳኋን የሶሻል ሚዲያ ገቢ ማሰባሰቢያ ማድረጋችን ቢያንስ ከሞራል አንፃር ነውር ነው።

አዎ! በእኩያን ገዥ ቡድኖች ምክንያት ዘመናትን ባስቆጠረና በተለይም ከአምስት ዓመታት ወዲህ እንኳንስ ለማመን ለማሰብ በእጅጉ የሚከብድ የመከራና የውርደት ዶፍ (ማዕበል) ሰለባ በሆነ ማህበረሰብ ውስጥ እየኖሩ የተከበረውን የሙያ ዘርፍ ምንም አይነት ፈታኝ ሁኔታ እንዳልተፈጠረ በሚያስመስል አኳኋን በየሶሻል ሚዲያውም ሆነ በየአዳራሹና በየአደባባዩ እየወጡ መውረግረግ (መድረክ ጠበበን ማለት) እና መሳሳቅ (መገለፋፈጥ ማለት ይሻላል) ቢያንስ ከሞራል ዳኝነት (ግዴታ) አንፃር የውድቀት ውድቀት ነው።

በግፍ በሚገደሉ ብዙ ሽዎች ፣  ታጉረው ሰቆቃ በሚቀበሉ አያሌ ሽዎች፣  ከገዛ አገራቸውና ቀያቸው ተፈናቅለው የምድር ፍዳ ላይ በሚገኙ ብዙ ሚሊዮኖች፣  ለመግለፅ በሚያስቸግር የርሃብና የእርዛት ሰለባዎች ሆነው የመቃብር ሙትነትን በሚጠባበቁ ብዙ ሚሊዮኖች፣ እና በአጠቃላይ እንደ ሰው  መኖር ሳይችል  በደስታ እየኖረ እንደሆነ አምኖ ራሱን እንዲያታልል  በተፈረደበት ህዝብ በተከበበ አዳራሽ ውስጥ ምንም እንዳለተፈጠረ በሚያስመስል አኳኋን መውረግረግና አጨብጭቡልን ማለት በፍፁም የመልካም ዜግነት (የአርበኝነት) ባህሪና ተልእኮ አይደለም!

እስኪወለዱ ድረስ በእናቶቻቸው ማህፀናት ውስጥ የመቆየት እድሉ የተነፈጋቸው ፣  እድለኛ ሆነው የተወለዱትም  የማደግ እድሉ ያልተፈቀደላቸው፣ ተወልደው በማደግ ላይ የሚገኙትም የገዛ ምድራቸውና ቀያቸው ምድረ ሲኦል የሆኑባቸው ህፃናት በሚገኙበት    እንኳንስ የትምህርት እድል በህይወት ለመኖር የሚያስችል ሁኔታ ጨርሶ የተነፈጋቸው፣ እድሉን ያገኙትም ቢሆን ካልተማሩት ባልተሻለ እጅግ  መሪር ሁኔታ ውስጥ ለመገኘት የተገደዱ፣  ተምረናል የሚሉትም ቢሆን በእጅጉ አሰቃቂና አሳፋሪ የህይወት ምህዋር ላይ እንዲሽከረከሩ የተገደዱ ወጣቶችና ጎልማሶች በሚተራመሱበት  አዛውንት ወላጆች የጧሪና የቀባሪ ያለህ የሚል የሰቆቃ ጩኸት በሚያሰሙበት ፣ እና በአጠቃላይ የአገሬ ህዝብ ባለጌና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴዎች  በሚያወርዱበት የመከራ ዶፍ ምክንያት እንኳን ለመስማት ለማሰብም የሚከብድ የሰቆቃ ጩኸት እየጮኸ ባለበት በዚህ አስጨናቂ ወቅት ለእናት እንኩሮ ማነኮርን፣ ወፍጮ መፍጨትን፣ የማገዶ እንጨት ማቅረብን፣ ቡሆ ማቡካትን  ወዘተ እንደ አስደናቂ ታዛዥነትና (ሰብእናእያገዘፉ ለሶሻል ሚዲያ ሳንቲም መልቀሚያነት (ንግድመጠቀም ቢያንስ  ወቅታዊ አስተማሪነት የለውም።

ወቅቱ በእጅጉ የሚጠይቀው እንደ አገር ወይም እንደ ህዝብ የመኖር ወይም ያለመኖር ጉዳይ (ጥያቄ) እንጅ በየአዳራሹና በየሶሻል ሚዲያው እየተጠራራንና እየተሰየምን ሁሉንም ነገር ተናግረንና ተንትነን ካልጨረስነው እያልን ችክ የምንልበት ጊዜ ፈፅሞ አይደለም።

እያልኩ ያለሁት እሽቱና መሰሎቹ ልክ አገር በመረጋጋትና በሰላም እየተንበሻበሸች ያለች እስኪመስል ድረስ የሚያቀርቡልንን ተውኔተ ሶሻል ሚዲያ ለዘመናት ከመጣንበትና ከአምስት ዓመታት ወዲህ እየሆነ ካለው መግለፅ የሚያስቸግር መከራና ውርደት አንፃር በመገንዘብ እውን ነገረ ሥራችንና የቅድሚያ ትኩረት አስተምህሯችን ትክክል ነውን? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ እንጅ ልጅ እናቱን የመርዳቱ በጎ ተግባር መነገርና መበረታት የለበትም አይደለም።

 

አዎ! እያልኩ ያለሁት ማህፀኗን በስለት ዘንጥለው በጉጉት ስትጠብቀው/ቃት የነበረውን/ የነበረችውን ልጇን ያስታቀፉበት፣ እንቦቃቅላውን/ዋን ወላጀቹን/ወላጆቿን  በግፍ ገድለው ከአስከሬን መካከል ተቀምጦ/ጣ እንቅልፍ እንዲያንገላታው/ታት የተደረገበት/የተደረገችበትን  ፣ አባትን ገድለው የሚወዳት ሚስቱን (የልጆቹን እናቱ) በመድፈር ለከባድ የአእምሮና የአካል ጉስቁልና እንዲዳረግ የተደረገበት  ፣ ንፁሃን ወገኖች በማንነታቸው ምክንያት በጅምላ ተገድለው በጅምላ የተቀበሩበት፣ ለእኩያን ገዥዎች የዙፋን ማፅኛ ሲባል የህዝብን ደህንነትና  አገርን መከላከል የሚገባው ሠራዊት  መብቱን የጠየቀን ሁሉ የሚያርድበት ፣ ወዘተ እጅግ መሪርና  አስጨናቂ ሁኔታ ግድ አልሰጣቸው ማለቱ አልበቃ ብሎ በየሶሻል ሚዲያና በየአዳራሹ  በሚፈጥሩት የውሸትና የማታለያ ተውኔት በህዝብ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ በመቸለስ ለእኩያን ገዥዎች እድሜ መራዘም አስተዋፅኦ የሚያደርጉትን የዚህ ትውልድ አባላት በቃችሁ ማለት ይገባል ነው።

የተወሰነ ተሰጥኦና ሙያ ያላቸውና ወደ ፊትም የሚኖራቸው የዚህ ትውልድ አባላት በቅጡ እያስተዋላችሁ ተራመዱና ተጠቃሚ ሁኑ ካልተባሉ በስተቀር በተወሰነ ነገር (ችሎታታዋቂ መሆን ማለት ሁሉን ማወቅ እየመሰላቸው ከህዝብ መንጭቶ የህዝብን ሁለንተናዊ የህይወት (የአኗኗርገፅታ የሚያንፀባርቀውን የሙያ ዘርፍ ሁሉ ከግልና ከቡድን ዝና ፈላጊነትና ልክ ከሌለው ጥቅም አግበስባሽነት የማያልፍ ያደርጉታል።

 እናም የወርቅ ማንኪያውን እና አካፋውን እየለየን በስሙ በመጥራት ትክክለኛውን ፍኖተ ነፃነትና ፍኖተ ፍትህ እናመቻች!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop