የሀይማኖት አባቶች ‹‹ለ27 ዓመት ያክል የተዘራ ዘር ለችግር ዳርጎናል›› አሉ

ዛሬ በባሕር ዳር የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የጋራ የምክክር መድረክ አካሂደው ነበር፡፡ ‹‹ሰላም ለሁላችን በሁላችን›› በሚል መሪ ሀሳብ የተከናወነው መድረክ በብጹዕወ ቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ ሼክ መሀመድ አሚን ጀማል፣ ብፁዕ ካርድናል ብርሀነ እየሱስ ሱራፌል ደምረው እና ፓስተር ፃድቁ አብዱ የተመራ ሲሆን የተለያዩ የሀይማኖት አባቶች የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እና የህብረተሰብ ክፍሎችም ተገኝተዋል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=aVUdalQQ5Mk&t=54s

በውይይቱ ሰላም በሁሉም የሀይማኖት መጽሀፍት በጉልህ መጠቀሱ እና አስፈላጊነቱ በጥልቅ መገለጹን ያስረዱት የሀይማኖት አባቶቹ ሰላም የሚኖረው መቻቻል እና መከባበር በህዝቦች ዘንድ ሲፈጠር መሆኑም አመላክተዋል፡፡ መጭውን የልደት በዓል በተመለከተም የሰላም ንጉስ እየሱስ ተወለደ እያልን ሰላምን አደፍራሾች መሆን የለብንም የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ሁሉም ዜጋ በየሀይማኖቱ ለሀገራችን ሰላም እንዲጾም እና እንዲጸልይ የሀይማኖት አባቶች አሳስበዋል፡፡ ሀይማኖቶች የሚሰብኩትን ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ መዋደድ፣ መከባበር እና ሌሎች እሴቶችን ህብረተሰቡ እንዲተገብርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉ ግለሰቦች ልዩ ልዩ ሀሳቦችን ሰንዝረዋል፡፡ ለአብነትም 27 ዓመት የተዘራው ዘር ፍሬ አፍርቶ ለችግር መዳረጉ ተጠቅሷል፡፡ ‹‹አሁን እያንዳንዱ ዜጋ የያዘው ዘር መልካም ይሁን ክፉ መለየት አለበት፡፡ በሀገራችን ለሚነሱ ግጭቶች መንስዔ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ በደሎች ናቸው›› ተብሏል፡፡ ሀሰተኛ የታሪክ ትርክቶች፣ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች፣ፍትሀዊ ተጠቃሚነት አለመኖር፣ስሜታዊነት እና በሀሰት የሚሰራጩ መረጃዎች የግጭት እና የሁከት መንስኤዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የሀይማኖት አባቶች በህዝቡ ላይ የተለያየ ግፍ ሲፈጸም ዝምታን መርጠው መቆየታቸውም እንደ ችግር ተነስቷል፡፡ አጥፊውን ቢቆጡ እና ቢገስጹ ሀገራችን ለዘመናት በመሰል ጎዳና አትጓዝም ነበር ተብሏል፡፡ የሀይማኖት አባቶች ከተሰሚነታቸው አንጻር ህዝቡን ሊያስተምሩ፣ ሊመክሩ፣ ሊቆጡ እና ሊገስጹ ያስፈልጋልም ነው የተባለው፡፡ ተረስቶ እና ተንቆ ለዓመታት የዘለቀው የሀይማኖት አባቶች እና የሽማግሌዎች ሚና ዳግም ሊያንሰራራ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ራንች የነበሩ ተፈናቃዮች የት ናቸው? ከ80ሽህ በላይ ህዝብን ወክለው የመጡ አማራዎች- አቶ መላኩ እምቢአለ፣ አቶ ታደለ ወርቅነህ እና አቶ አደም አስማማው

የቁርሾ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ሊያከትም እንደሚገባ እና ዋነኛ የግጭት ምንጭ እንደሆነም ተነግሯል፡፡ ጥያቄዎች ለረጅም ዘመናት ታፍነው መቆየታቸው የታወቀ ቢሆንም ህዝቡ የመንጋ ፍትህ እና አጓጉል የመብት ጥያቄዎችን ማቆም አለበት ነውም የተባለው፡፡ አጥፊውን ለመቅጣት አይጡን ከዳዋው መለየት ተገቢም ነው ተብሏል፡፡ የማህበራዊ ተቋማት የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ለማሳደግ እና ችግሮችን ለመፍታት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የጋራ ኮሚቴ በሀገራችን የሚስተዋሉ የፀጥታ እና አለመረጋጋት ችግሮችን ለመፍታት የተቋቋመ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በትግራይ፣ ደቡብ እና ኦሮሚያ ክልሎች መሰል መድረኮችን አካሂዷል፡፡ በቀጣይም ከከፍተኛ አመራሮች ጋር በመፍትሄ አቅጣጫዎች ዙሪያ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል ሲል አብመድ ዘግቧል፡፡

Share