የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመቀሌ ውሀ አገልግሎት አቅርቦት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድ ከቻይና ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ የተገደረገውን የብድር ስምምነት ተቀበለ

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራው የሚኒስትሮች ም/ቤት ዛሬ ህዳር 14 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብስባው ለመቀሌ ውሀ አገልግሎት አቅርቦት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድ ከቻይና ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ የተገደረገውን የብድር ስምምነቱን ተቀብሎ ለማጽደቅ ወደ ፓርላማው መራው::

ለመቀሌ ውሀ አገልግሎት አቅርቦት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. እና በቻይና ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ መካከል የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተወያየው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በብድር የተገኘው ገንዘብ በመካከለኛ ጊዜ የሚከፈል፣ የወጪ ጫናው ቀላልና ከአገራችን የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ም/ቤቱ የብድር ስምምነቱን ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት አስታውቋል::

በአቶ ደመቀ መኮንን የተመራው ይኸው የም/ቤቱ ስብሰባ ስለምግብ እና መድሃኒት አስተዳደር በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተወያየ ሲሆን ደህንነቱ ባልተጠበቀ ምግብ ምክንያት በሕብረተሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጤና ጉዳት መከላከል እና መቆጣጠር፤ ደህንነቱ፣ ፈዋሽነቱና ጥራቱ ባልተረጋገጠ መድሃኒት እንዲሁም ደህንነቱ እና ውጤታማነቱ ባልተረጋገጠ የህክምና መሳሪያ ምክንያት በሰው ላይ የሚደርስን የጤና ችግር መከላከል እና መቆጣጠር በማስፈለጉ የጤና ሚኒስቴር ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
በሌላ በኩልም በኢትዮጵያ የምግብ እጥረትና የሥርዓተ ምግብ መዛባት የረዥም ጊዜ ተግዳሮቶች ሆነው የቆዩ ሲሆን መንስኤዎቹም ስር የሰደደ የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ፣ ዝቅተኛና ከሚጠበቀው በታች የሆነ የእናቶችና የህጻናት ክብካቤና አመጋገብ ስርአት፣ ከፍተኛ የሆነ የግልና የአካባቢ ንጽህና ጉድለት እና ልማዳዊና ባህላዊ የአመጋገብ ስርአቶች የመሳሰሉት ችግሮችን ለመቅረፍ የጤና ሚኒስቴር ብሔራዊ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ፖሊሲ አዘጋጅቶ፣ፖሊሲው በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገጉ የተወሰኑ ክልከላዎች ተነሱ

ምክር ቤቱ በተጭርማሪም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. መንግሥት እና በእስራኤል፣ በፈረንሳይ፣ በሞሮኮ መንግሥታት መካከል የተደረጉትን የአየር አገልግሎት ስምምነትን ለማጽደቅ የቀረቡት ረቂቅ አዋጆች እና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. መንግስት እና በሞሮኮ መንግሥት መካከል የተደረገውን የኢንቨስትመንት ጥበቃ እና የግብርና ዘርፍ ትብብር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ይጸድቁ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንዲተላለፉ ም/ቤቱ መወሰኑን ከጠቅላይ ሚ/ር ጽህፈት ቤት የደረሰን መረጃ ጠቁሟል::
https://www.youtube.com/watch?v=ibs_Mi6_X_s

Share