ትናንት ምሽት በቤተመንግስት ወታደሮቹ የፈጸሙት ተግባር “አደገኛ እና የደኅንነቱን ድከምት ያሳየ” ነበር ተባለ

ትናንት ቁጥራቸው ወደ 250 የሚጠጋ ወታደሮች የመብት ጥያቄ አንስተው ወደ ቤተመንግስት ከነታጠቁት መሳሪያዎች መሄዳቸውና የተፈጸመውም ድርጊት “አደገኛ እና የመንግስት ደኅንነቱን ድከምት ያሳየ” ነበር ተባለ::
(ቢቢሲ)
ቢቢሲ በስልክ ያነጋገራቸው አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ክስተቱን ‘የወታደራዊ ደኅንነቱን ድክመት ያሳየና አደገኛ’ ሲሉ ገልጸውታል።
እኚህ መኮንን እነዚህ ወጣቶች ያነሱት ጥያቄ ከሞላ ጎደል የጠቅላላ ወታደሩን ጥያቄ ሊወክል ይችላል ካሉ በኋላ የሄዱበት መንገድ ግን ከወታደራዊ ጥብቅ ዲሲፕሊ እና ሕግ ያፈነገጠ እንደሆነ አብራርተዋል።
ዩኒፎርም በለበሱ ወታደሮች እንዲህ ዓይነት አስገዳጅ ስብሰባ የመጥራት ጉዳይ የማይታመንና አስደንጋጭ ነው ይላሉ መኮንኑ። “የትናንቱ ክስተት የሚነግረን ነገር ወታደራዊ የመረጃ ክፍል ሥራውን በአግባቡ እንዳልሠራ ነው።”
እኚህ መኮንን ችግሩ በጥቅሉ የወታደራዊ ደኅንነት የመረጃ ክፍል መሆኑን ሲጠቅሱ ክስተቱ ያደገበትን ሂደት በመዘርዘር ነው።
በአሠራር ደረጃ ወታደሮች ለግዳጅ ሲንቀሳቀሱም ኾነ ወደ ካምፓቸው ሲመለሱ የሚሄዱበት መስመር በዘፈቀደ የሚመረጥ እንዳልሆነ ከጠቆሙ በኋላ የወታደር ኮንቮዮች መነሻና መድረሻ፣ ሰዓታቸውም ኾነ እንቅስቃሴያቸው በአዛዦች በኩል ተከታታይ የመረጃ ልውውጥ የሚደረግብት እንደሆነ ያወሳሉ።
ወታደሮቹ ላይ የዲሲፕሊን እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባ ነበር ወይ ተብለው የተጠየቁት መኮንኑ ከዚያ በፊት ማቆም ይገባ ነገር እንጂ “ከገቡ በኋላ ነገሮችን በነሱ ደረጃና ስሜት ወርዶ ማስተናገድ ምንም አማራጭ አልነበረውም” ብለዋል።
ያን ስሜታቸውን በመረዳትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገሩን ለጊዜውም ቢሆን በብልሀት ፈተውታል። “የግል ብቃታቸውና ጥበባቸው ረድቷቸዋል” ይላሉ።
እኚሁ ከፍተኛ መኮንን እንደሚገምቱት በወጣት ወታደሮቹ የዋህነት ውስጥ ተጠቅሞ ሴራ የጎነጎነ አካል አለ። እንዲህ እንዲያምኑ ያስገደዳቸው ደግሞ በወታደሩ ውስጥ ያለ ጥብቅ የዕዝ ሰንሰለት ነው።
ወታደሮቹ ዝም ብለው ድንገት በስሜት ተነሳስተው ወደ ቤተ መንግሥት ሊመጡ የሚችሉበት ዕድል ሊኖር አይችልም ብለው ያምናሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአዲስ አበባና ኦሮሚያ የተቀናጀው የጋራ ልማት ፕላንና ያልተቀናጁ ጥያቄዎች

ወታደራዊ ደኅንነቱ ከዚህ በኋላ ይህ ነገር እንዴት ሊሆን ቻለ? ከጀርባው እነማን ነበሩ? ወደፊት ተመሳሳይ ስሜቶች ቢያቆጠቁጡ እንዴት ማቆም ይቻላል? የትኞቹ የወታደር ክፍሎች ለዚህ የተመቹና “ስሱ” ናቸው የሚለው ላይ ትልቅ ሥራ እንደሚጠብቀው አስገንዝበዋል።
“ይህ ነገር ለነገ የሚባል አይደለም። ፋታ የሚሰጥም አይደለም።” ይላሉ ከፍተኛ መኮንኑ።
“ከለውጡ በፊት እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢፈጠር ምን ዓይነት ወታደራዊ የዲሲፕሊን እርምጃ ሊወሰድ ይችል ነበር?” ሲል ቢቢሲ ጥያቄ ያነሳላቸው እኚህ መኮንን “መጀመርያውኑም የሚሞከርም የሚታሰብም አይሆንም ነበር” ብለዋል።
“ወታደሩ አካባቢ ያለው ችግር እነርሱ ከገለጹትም በላይ ነው። ከግዳጅ አፈጻጸም፣ ከትምህርትና ሥልጠና፣ ከውጭ ተልዕኮ እንዲሁም ከማንነት ጋር ተያይዞ የተጎዳ ሠራዊት ነው” ካሉ በኋላ “ቀደም ባለው አሠራር በግምገማ ወቅት ጥያቄዎች ይነሳሉ፤ የሚመለሱበት መንገድ ግን አዝጋሚ ነበር” ብለዋል።
መኮንኑ እንደሚያምኑት አሁን የለውጡ መንፈስ ተከትሎ ወጣት ወታደሮቹ ዲሞክራሲውን የሚረዱበት መጠንና መንገድ ስለሚለያይ ለዚህ ተግባር አብቅቷቸዋል።
“ወታደርን ወታደር የሚያደርገው ሥነ ሥርዓቱ ነው። አንዴ ሠራዊት ውስጥ ከገባህ ወደድክም ጠላህም የሚያስጠይቅ ነገር ሁሉ ያስጠይቅሀል። ይህ ተግባር እንደዋዛ የተወሰደው አሁን የሽግግር ስሜት ላይ በመሆናችንና ሆደ ሰፊ ለመሆን እየተሞከረ ስለሆነ ነው። አሁን ያለውን መልካም ስሜት እንዳያደበዝዘው ሲባል ጥብቅ እርምጃዎች ላይወሰዱ ቢችሉም ነገሮች በዚህ መንገድ ይቀጥላሉ ማለት ግን አይቻልም።” ብለዋል።
ስማቸውን መግለጽ የማይሹት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኑ እንደሚያምኑት ይህ የትናንቱ ክስተት ለወታደራዊ ደኅንነቱ የማንቂያ ደውል ነው።

Share