አጋዚ በኦሮሚያ ክልል አራት ሰዎችን መግደሉ ተነገረ

ቢቢኤን 

የአጋዚ ወታደሮች በኦሮሚያ ክልል አራት ሰዎችን መግደላቸው ተነገረ፡፡ ግድያው የተፈጸመው በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ውስጥ ሲሆን፤ ከሟቾች በተጨማሪ አምስት ሰዎች በወታደሮች ጥይት ተመትተው መቁሰላቸውን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ ትላንት እሁድ ሚያዝያ 7 ቀን 2010 በቡሌ ሆራ ከተማ ጉጂ ዞን ውስጥ የተገደለው አንድ ሰው መሆኑን የጠቆሙት የመረጃው ምንጮች፤ በዚሁ ከተማ ሶስት ሰዎች መቁሰላቸውንም ከመረጃዎቹ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በቡሌ ሆራ በጥይት የተመቱ ሰዎችን ህይወት ለማትረፍ ተጎጂዎችን ወደ ሆስፒታል ለመውሰድ ጥረት ሲደረግ፤ ጥቃቱን የፈጸሙት ወታደሮች ሲከላከሉ ነበር ተብሏል፡፡

እንደ መረጃዎቹ ገለጻ፣ በኦሮሚያ ክልል ገርባ ከተማ ሁለት ሰዎች በአጋዚ ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን፤ ቡሌ ሆራ በተባለው የክልሉ ከተማ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አባል የሆነ አንድ ግለሰብ በእነዚሁ ወታደሮች ተመትቶ ተገድሏል፡፡ በአጠቃላይ በተጠቀሱት የኦሮሚያ ከተሞች አራት ሰዎች ተገድለው አምስት ሰዎች መቁሰላቸውን የገለጹት መረጃዎች፤ ከአምስቱ ቁስለኞች ውስጥ ሁለቱ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አባላት መሆናቸውንም የመረጃው ምንጮች ይፋ አድርገዋል፡፡ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ-ህወሓት ልዩ ኃይል የሆነው አጋዚ፣ አሁንም በኦሮሚያ ክልል የሚፈጽመው አሰቃቂ ግድያ ተጠናክሮ ስለመቀጠሉ በተጠቀሱት ከተሞች የተፈጸመው ግድያ አስረጂ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎችን እየመራ የሚገኘው ራሱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያ አስፈጻሚ እያለ የሚጠራው ኮማንድ ፖስት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የካቲት 23 ቀን 2010 በገዥው ፓርላማ ከጸደቀ በኋላ፣ በኮማንድ ፖስቱ ቀጥተኛ ትዕዛዝ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ንጹኃን ዜጎች እየተጨፈጨፉ የሚገኙ ሲሆን፤ የሚፈጸመው ጭፍጨፋም አሁንም ተጠናክሮ በመቀጠል ላይ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በአሁን ሰዓት በሀገሪቱ የአደባባይ ተቃውሞዎች ለጊዜው መቆማቸው የሚታወቅ ቢሆንም፤ በህዝባዊ ተቃውሞ ሰበብ የሚፈጸመው የዜጎች ግድያ ግን አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል ሲሉ ሁኔታውን በቁጭት ይገልጻሉ-አስተያየት ሰጪዎች፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ማን  ምን እንዲል  እንጠበቅ ?  - ማላጂ   

በተቃውሞ ሰበብም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ድምጻቸውን በሰላማዊ መንገድ የሚያሰሙ ዜጎች ላይ ግድያ መፈጸም ነውር መሆኑን የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ በሀገሪቱ ምንም ዓይነት የአደባባይ ተቃውሞ በሌለበት በአሁን ሰዓት እንኳን ግድያዎች ሊቆሙ እንዳልቻሉ በመጠቆም፤ የኮማንድ ፖስቱን የኃይል እርምጃ በጽኑ ኮንነዋል፡፡ አገዛዙ በአንድ በኩል ‹‹የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት ተከትሎ አዲስ የለውጥ መንገድ እየተከተለ›› መሆኑን ቢገልጽም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ንጹኃንን መጨፍጨፉን መቀጠሉ፣ እርስ በእርሱ የሚጋጭ እንደሆነም እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡

ዶ/ር አብይ አህመድ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ፣ ‹‹የሀገሪቱን ችግር በሰለጠነ መንገድ እንፈታለን›› በማለት ደጋግመው ቢናገሩም፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በንጹኃን ዜጎች ላይ የሚፈጸመውን ግድያ በተመለከተ ግን ምንም ዓይነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል ሲሉ የገለጹ ታዛቢዎች በበኩላቸው፤ ‹‹በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ በአንጻራዊነት የተጣለው ጭላንጭል ተስፋ እየተሟጠጠ ይገኛል›› በማለትም ታዛቢዎቹ ተናግረዋል፡፡ የንጹኃን ግድያ ተጠናክሮ መቀጠሉ፣ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢመጣም ባይመጣም፣ ገዥው ፓርቲ የሚሻሻል ባህሪ እንደሌለው ያመላክታል ሲሉም ታዛቢዎቹ ደምድመዋል፡፡

Share