በኬንያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ስጋት ላይ መሆናቸውን ተናገሩ

በኬንያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከመጠለያ ጋር በተገናኘ ስጋት ላይ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡ የኬንያ መንግስት የስደተኞች መጠለያ የሆኑ ካምፖችን በመዝጋት ላይ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታም በቀጣይ ህይወታቸው ላይ ትልቅ ስጋት እንደሚደቅን ስደተኞቹ ተናግረዋል፡፡ የኬንያ መንግስት ከዚህ ቀደም ዳዳብ የተባለውን እና በኬንያ ትልቁ የስደተኞች መጠለያ የሆነውን ካምፕ ለመዝጋት እንደሚፈልግ ሲገልጽ ነበር፡፡

በተጠቀሰው የስደተኞች ጣብያ ይገኙ የነበሩ የሶማሊያ ስደተኞች ወደሀገራቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ሲሆን፣ አሁን በጣብያው ያሉት ስደተኞች ቁጥር፣ በፊት ከነበረው የስደተኞች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህንንም ተከትሎ በዳዳብ ዙሪያ ያሉ የስደተኛ መጠለያ ካምፖች መዘጋት ጀምረዋል- እንደ መረጃዎች ገለጻ፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ሌሎች በዳዳብ ዙሪያ ያሉ ሌሎች የስደተኛ መጠለያዎችን እንደሚዘጋ የኬንያ መንግስት አስታውቋል፡፡

ይህ ሁኔታም በቀጣይ ህይወታቸው ላይ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል የሚናገሩት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፣ መጠለያ አልባ ሊሆኑ እንደሚችሉ በማሰብ ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ችግሩ በዚህ ብቻ እንደማያበቃ የሚናገሩት ስደተኞቹ፣ በመጠለያ ካምፖች አካባቢ እርዳታ ለመስጠት የሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ተቋማት ቁጥርም በዛው ልክ እየተመናመነ እንደሚሔድ ገልጸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከባድ ፈተና ሊጋርጥባቸው እንደሚችልም አክለው ተናግረዋል፡፡ በኬንያ ሁለት ዓይነት ስደተኞች ሲኖሩ፣ አንደኞቹ በከተማ የሚኖሩ ስደተኞች ሲሆኑ፣ ሌላኞቹ ደግሞ በመጠለያ ካምፖች የሚኖሩት ስደተኞች ናቸው፡፡

BBN News November 17, 2017

 

ተጨማሪ ያንብቡ:  EHSNA 3rd Annual Festival 2013
Share