ለአንዱ ብሄር ያገዙ መስለዉ አንዱን ብሄር የሚሳደቡ ሰዎች ሲገጥሙን ልንገነዘባቸዉ የሚገቡ ጥቂት ነጥቦች  – ሸንቁጥ አየለ

በኢትዮጵያዉያን ማህበረሰቦች መሃከል ጥላቻን የሚያባዙ : …የሚረጩ: የሚያሰራጩ ግለሰቦች ብዙ ይመስሉናል:: ብንቆጥራቸዉና ብንመረምራቸዉ ግን እጅግ በጣም ጥቂት ናቸዉ:: በተለያዬ ግለሰብና ድርጅት ስም ዞረዉ ተዙዋዙረዉ የሚያወናብዱን እነዚሁ ጥቂት ሰዎች ናቸዉ::

በተለይም ግጭት በስፖርት ሜዳዎች : በተማሪዎች መካከል ሲፈጠር: በዩኒቨርሲቲዎች ግጭት ሲነሳ እንዲሁም አንዱ ብሄር ከአንዱ አካባቢ ሲባረር እነዚህ ጥቂት ግለሰቦች ስማቸዉን እየቀያዬሩ በመቶና በመቶ አምሳ ስም አንዴ አንዱ ብሄር ሲሳደቡ ሌላ ጊዜ ዞረዉ ደግሞ ሌላዉን ሲያንጉዋጥጡ አንዳንድ የዋህ ሰዎች ዘለዉ እክርክሩ መሃል ዘዉ በማለት ጥላቻን ለልባቸዉ ሸምተዉ በሌላዉ ማህበረሰብ ላይም ክፉ ክፉ ንግግሮችን ተናግሮ ዘወር ይላል:: እነዚህ ሁሉ ግን ስራቸዉ እና መነሻቸዉ ቢጠና በአንድም ወይም በሌላ መልክ ቢጠኑ መድረሻቸዉና ምንጫቸዉ ይችዉ ደም መጣጯ የወባ ትንኝ ወያኔ ነች:: ከወያኔም ከዘለለ የዘር ፖለቲካን ለወያኔ ቀጥቅጦ የጋታት ሻቢያ::

ማስተዋል ለምትችሉ ወገኖች ጥንቃቄ እንድታደርጉ መምከር የግድ ያስፈልግ መሰለኝ:: ስለ ጥቂት ግለሰቦች ብዙሃኑን አትሳደቡ:: ስለ ጥቂት ቁጡና ስሜታቸዉን መግታት የማይችሉ ሰዎችም ሁኔታዎችን አታጋግሉ:: መሞገት ከቻላችሁ እነዚያን ግለሰቦች አጥብቃችሁ መሞገት ነዉ::

ለአንዱ ብሄር ያገዙ መስለዉ አንዱን ብሄር የሚሳደቡ ሰዎች ሲገጥሙን ልንገነዘባቸዉ የሚገቡ ጥቂት ነጥቦች :-

1. የትኛዉንም ብዙሃን በጅምላ የሚሳደብ ወገን አደገኛ የጥላቻ ተልዕኮ ስላለዉ እሱ የሚያስነሳቸዉ ክርክሮች ዉስጥ ከመግባት መታቀብ

2. ለአንድኛዉ ማህበረሰብ ያገዘ መስሎ አንዱን ማህበረሰብ እስከ ደመና ከፍ ከፍ ማድረግ ሲጀምር እዉን ይሄ ነገር ትክክል ነዉ ? ደግሞስ ተገቢ ነዉ ? ብሎ መጠየቅ:: እንዲሁም የተነሱት ነጥቦችን ከምታቁት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ማገናዘብ ተገቢ ነዉ:: ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ ሁሉ ምርጥና መልካም ገጽታዉ ከፍ ብሎ የሚዉለበለብለት ህዝብ ስለሆነ ተጨባጭ እዉነታዉን አለመርሳት::

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሰሜኑን የኢትዮጵያ ክፍል ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኘው የደብረ ብረሃን አዲስ አበባ መንገድ የሚያቋርጡ ተጓዞች፣ ሸኖን አልፈው እንዳይሄዱና ወደመጡበት እንዲመለሱ ሲገደዱ በስፍራው የነበረው ሪፖርተራችን ተመልክቷል

3. አንድ ሰዉ ብዙ ከተሳደበና ከጮህ ወይ ፈሪ ነዉ ወይም በጥላቻ የታወረ ደንቆሮ ነዉ:: ስለሆነም ፈሪን እና በጥላቻ የታወረን ወገን ለማዘል በእርሱ ጎራ አለመሰለፍ

4. ሁል ጊዜ ከስሜት ይልቅ ትዉልድን ማሰብ:: ተዉልዱ ሁሉ የተመቻቸ ፍቅር የሚፈስባት ኢትዮጵያን እንጅ በጥላቻ የተወጠረች ሀገር አይፈልግምና ፍቅርና የጋራ እሴቶች ላይ ማተኮር

5. ጥላቻን እና ልዩነትን የሚያራግቡትን ቸል ብሎ ማለፍ:: ከተከራከሩም በተጠይቅና በእዉቀት መከራከር:: አለዚያ ግን ዝም ማለት::

6.ልዩነት ከሚባሉት አንድና ሁለት ነገሮች በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ያጋራ አንድነቶች በኢትዮጵያዉያን መሃከል እንዳሉ ማስተዋል እና እነዚያ ላይ ማተኮር

7. ስልጣን ማግኘት የሚቻለዉ ይሄኛዉን ወይም ያኛዉን ብሄረሰብ በማንጉዋጠጥና ጥላቻን በመዝራት ሳይሆን ዘመኑ የሚጠይቀዉን የትግል ስልት ((በትጥቅ ትግልም ቢሆን: በህቡዕም ቢሆን: አምባገነኑን ሀይል ላይ በልዩ ልዩ መንገድ አሻጥርም በመስራትም ቢሆን: በድርድርም ቢሆን በሰላማዊ መንገድም ቢሆን ወይም በሌላ ስልትም ቢሆን) ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል ብቻ መሆኑን በሚገባ መገንዘብ እና ለስልጣን የምትታገሉ ሀይሎች የትግል ስልታችሁን ጥላቻን መሰረት ያደረገ እንዳይሆን መጠንቀቅ:: በጥላቻ ላይ ተመስርቶ የሚገኝ ስልጣን ቢገኝ እንኩዋን ሰበቡና መዘዙ የበረከት ስለሚሆን ወደ ብሄረሰብ ማጥላላትና ማንጉዋጠጥ አጥር ዉስጥ ላለመግባት መጠንቀቅ

8. የብሄር ጥላቻ አንድን ወገ ሳይሆን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ይዞት ገደል እንደሚገባ መገንዘብና በጥላቻ ጉዳዮች ላይ ላለመሳተፍ ስሜትን መግዛት

9. ስለ ኢትዮጵያዊ የጋራ እሴት እና ፍቅር የሚሰብኩ ወገኖችን ማበረታታት እና ይበልጥ ማጀገን::

10. ለአንዱ ብሄር ያገዙ መስለዉ አንዱን ብሄር የሚሳደቡ ሰዎች ሲገጥሙን ስላላቸዉ የሰበአዊ መብት: የፖለቲካ እና የዲሞክራሲ ግንዛቤ በመጠዬቅ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸዉ በእዉቀት ማስረዳት ካስፈለገም ከጥላቻ እርቆ መከራከር::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰማያዊ ፓርቲ በመብራት ኃይል አዳራሽና በምኒልክ ት/ቤት ሕዝባዊ ስብሰባ እንዳላደርግ በቢሮክራሲያዊ መንገድ ተከለከልኩ አለ

11. የኢትዮጵያዊነት እሴትና አቁዋምን ከጥላቻና ከስድብ ርቆ በግልጽ በድፍረትና በፍቅር ማራመድ ::

12. ሌላዉ በደንብ ሊሰመርበት የሚገባዉ ጉዳይ ግን በስግብግብነት አገሪቱን ወጥሮ የያዘዉ አንባገነን ብሎም ዘረኛ ሀይል አንዴ የአንዱን ብሄር ካባ እና ስም እየለበሰ ሌላ ጊዜም ሌላዉን ብሄር ወካይ በመሆን በብሄረሰቦች መሃከል ስድብና ጥላቻ እንዲስፋፋ ከፍተኛ ገንዘብ እየረጨ 25 አመታት ሙሉ ዙፋን ላይ እንደቆዬ አይዘንጋ::ስለዚህ ይሄን ርኩስ ሀይል ለመግጠም የሚነሳ ሀይል ሁሉ የዚህን ሀይል ባህሪያት መጀመሪያ ጠንቅቆ ማወቅና እሱ በሚዘረጋዉ የጥላቻ ወጥመድ ዉስጥ ላለመዉደቅ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉ በሌሎች ብሄሮች ላይ አሉታዊ ቃላትን ከመወርወር ለመቆጥብ ያግዛል::የኢትዮጵያ ችግር በምንም መልኩ ከህዝቧ ወይም ከማህበረሰቦቿ በጅምላ ጋር የተያያዘ ሳይሆን ከወያኔ ጋር የተያያዘ ብቻ ነዉ:: ወያኔን ላቦራቶሪ ዉስጥ እንደምታገኛት ደም መጣች የወባ ትንኝ ነጥለህ ዉሰዳት::መደሃኒትም ስታዘጋጅ ለዚህች ደም መጣጭ የወባ ትንኝ ብቻ ይሁን::ካለዚያ ወባ ትንኝ አጠፋለሁ ብለህ አጠቃላይ ማህበረሰብን የሚያጠፋ መድሃኒት ወደ ህዝቡ ልትረጭ ትችላለህ::

Share