Sport: ሞ ፋራህ የቀማን 5 ወርቆች

ከቦጋለ አበበ
በዓለም አትሌቲክስ ታሪክ የአምስትና አስር ሺ ሜትር የሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ስማቸው ገናና ነው፡፡ በተለይም በጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴና ቀነኒሳ በቀለ ዘመን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የርቀቶቹ ቁንጮ ነበሩ፡፡
ኦሊምፒክን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች በሚዘጋጁ ውድድሮች በእነዚህ ርቀቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ወደ ውድድር ከመግባታቸው አስቀድሞ የወርቅ ሜዳሊያውን እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ የሚኮንበት ዘመን ነበር፡፡ ይህም የሆነው በርቀቶቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በማይዋዥቅ ብቃት በርካታ ውድድሮችን ማሸነፍ በመቻላቸው ነው፡፡
ከቅርቡ የኃይሌ ገብረስላሴ ታሪክ ብንጀምር እንኳን የተለያዩ አትሌቶች በርቀቶቹ ድንቅ ብቃት በማሳየት አምስትና አስር ሺ ሜትር ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ብቻ የተፈጠሩ ናቸው አስብለዋል፡፡
ከሌላ ፕላኔት እንደመጣ ተደርጎ የሚነገርለት ኃይሌ የአስር ሺ ሜትር የምንጊዜም ምርጥ አትሌት እንደሆነ እኛ ሳንሆን የውጭ ዜጎች ቃላት እስኪያጥራቸው ይነግሩናል፡፡ ኃይሌ በኦሊምፒክና በዓለም ሻምፒዮና በተለያዩ ጊዜያት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ለአገሩ በማስመዝገብ የማይረሳ ታሪክ አስመዝግቧል፡፡
ኃይሌ የውድድር ዘርፉን ወደ ማራቶን ካዞረ በኋላ ጎረቤታችን ኬንያ የተወሰኑ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ምናልባትም አንድ ወይንም ሁለት ነጥቃናለች፡፡ ከእዚያ በኋላ ግን በርቀቱ መልሰን ክብራችንን  አስጠብቀናል፡፡ በድንቅ የአጨራረስ ብቃቱ የሚታወቀው አትሌት ቀነኒሳ በቀለን ማግኘት ችለናል፡፡ ለረጅም ጊዜም በርቀቶቹ ስጋት ሳይገባን የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያዎችን እንደ ልብ መሰብሰብ ችለናል፡፡ አገራችን በርግጥም ተተኪ የማይነጥፍባት የብርቅዬ አትሌቶች መፍለቂያ መሆኗን አስመስክረናል።
ቀነኒሳ እንደማንኛውም አትሌት ብቃቱ እየቀነሰ ሲመጣ ሌላ ቀነኒሳ ይመጣል በሚል በተስፋ ብንጠብቅም ጠብ የሚል ነገር ጠፍቶ አሁን ላይ ደርሰናል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮችም በርቀቶቹ የበላይነት ሲወሰድብንና በርካታ የወርቅ ሜዳሊያዎች ስንነጠቅ እየተመለከትን እንገኛለን፡፡
በርቀቶቹ የተለያዩ ወጣት አትሌቶች በልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ የግል ውድድሮች በማሸነፍ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ቢያስመዘግቡም አገርን በሚያስጠሩ እንደ ኦሊምፒክና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባሉ ውድድሮች ልብ የሚደርስ ውጤት ማስመዝገብ ሲሳናቸው መመልከታችን እየተለመደ መጥቷል።
በኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮናዎች በአምስትና አስር ሺ ሜትሮች የወርቅ ሜዳሊያዎች እየናፈቁን ከመጡ ከሁለት ዓመት በላይ አልተቆጠረም፡፡ ነገር ግን በርቀቶቹ የተነጠቅነውን የወርቅ ሜዳሊያ ቁጥር ስናሰላ አምስት መድረሳቸው እውነትም በርቀቱ ያለንን ክብር ለሌሎች አገሮች እያስረከብን ነው ያስብላል፡፡
ቀደም ሲል የወርቅ ሜዳሊያዎችን የምንነጠቀው በጎረቤታችን ኬንያ ነበር፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን በትውልድ ሶማሌያዊ በዜግነት እንግሊዛዊው ሞሐመድ ፋራህ አማካኝነት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ምሥራቅ አፍሪካን አምስት ወርቆችን ነጥቃ እያጌጠችበት ትገኛለች፡፡
ሞፋራህ በአምስትና አስር ሺ ሜትር ኢትዮጵያን በተለይም ምሥራቅ አፍሪካን የወርቅ ሜዳሊያ ማሳጣት የጀመረው ከሁለት ዓመት በፊት በደቡብ ኮሪያ አስተናጋጅነት ዴጉ ከተማ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ነው፡፡
በዴጉው ሻምፒዮና ፋራህ ከምሥራቅ አፍሪካዎቹ የርቀቱ ተጠሪዎች ቁጥጥር ውጪ በመሆን በአምስት ሺ ሜትር መንጠቅ የጀመረው የወርቅ ሜዳሊያ ከዓመት በኋላ በተካሄደው የለንደን ኦሊምፒክም ቀጥሏል፡፡ ከሳምንት በፊት እስከተጠናቀቀው የዓለም ሻምፒዮናም ድረስ ዘልቋል፡፡
እንግሊዝ በአምስትና አስር ሺ ሜትሮች በታሪኳ ያላየችውን ወግ ያሳያት ሞፋራህ ከሁለት ዓመት በፊት በዴጉው ሻምፒዮና ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ጠራርጎ ለመውሰድ ጫፍ ደርሶ በአስር ሺ ሜትር ክስተት የነበረው ኢብራሒም ጄይላን ትውልደ ሶማሌያዊው ከአፉ ያደረሰውን የወርቅ ሜዳሊያ ነጥቆ ለኢትዮጵያ አስመዝግቧል፡፡
የአስር ሺ ሜትሩን የወርቅ ሜዳሊያ ለጥቂት የተነጠቀው ሞፋራህ በእዚያው የዴጉ ሻምፒዮና በአምስት ሺ ሜትር ቁጭቱን በመወጣት የወርቅ ሜዳሊያውን አንድ ማለት ጀምሯል፡፡
ይቀጥላል

ተጨማሪ ያንብቡ:  የድል ዜና! ጀነራሉ እና ኮረኔሉ ተማረኩ! ማርቆስ፣ ጂጋ፣ ሆዳንሽ!| የአማራ ድምጽ ዜና
Share