ከ6 ነጋዴዎች ጎማ አስነግዳችኋለሁ በሚል ብር ተቀብሎ ተሰውሯል የተባለው አርቲስት ሚኪያስ መሐመድን ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ ጥረት ተጀመረ | የደረቅ ቼክ ማስረጃውን ይዘናል

(ዘ-ሐበሻ)  ከ6 ሰዎች ገንዘብ ተቀብሎ ስንቅ የሌለው ቼክ በመስጠት ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ዕዳ አለበት ተበሎ የተከሰሰው አርቲስት ሚኪያስ መሀመድ(ባለታክሲው) ከተደበቀበት ለማስመጣት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተሰማ:: የዘ-ሐበሻ ምንጮች እንደገለፁልን አርቲስቱ በቼክ ማጭበርበር በጷግሜ ወር ውስጥ በአዲስ አበባ ቦሌ ፖሊስ መምሪያ ታስሮ የነበረ ቢሆንም ከከሳሽ ጋር በሽማግሌ በተደረገ ድርድር ተለቆ ሊፈታ ችሏል፡፡ በቦሌ ደህንነቶች የተለቀቀውም የሕወሓት መንግስት ደጋፊ በመሆኑና በየሕወሓት በአል ላይ በመገኘት ለስርዓቱ ታማኝ መሆኑን በማሳየቱ መሆኑም ምንጮች ይናገራሉ::

ከእስር ከተፈታ በኋላም እጁ ላይ የነበረውን የአሜሪካ ቪዛ በመጠቀም ወደ አሜሪካ  ካሊፎኒያ ግዛት ገብቶ ተደብቋል ተብሎ ገንዘባችን ተወሰደብን በሚሉ ወገኖች እየተወገዘ ይገኛል::

በአርቲስት ሚኪያስ መሀመድ ገንዘባቸውን ከተበሉ ሰዎች መካከል ድምፃዊ ታደለ ሮባ አንዱ ሲሆን፤ ታደለ አርቲስቱን ለመፈለግ ከሰሞኑ ወደአሜሪካ ማቅናቱ ታውቋል፡፡

ድምፃዊ ታደለ ለአርቲስቱ የሰጠው 1.7 ሚሊዮን ብር እንደነበርም ለማወቅ ችለናል፡፡ አርቲስት ሚኪያስ መሀመድ ገንዘባችንን ወስዶ ባዶ ቼክ ሰጥቶናል ያሉ ወደ 6 ያህል ሰዎች አቤቱታ እያሰሙ ሲሆን ከነዚህም መካከል የኪንግ ሲልቨር ባለቤት እንደሚገኝበት ታውቋል:: ጉዳያቸው በሽምግልና ተይዞ ይገኛል፡፡ በዚህ ሽምግልና ውስጥም አቶ ኤፍሬም የተባሉ ግለሰብ፤ አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬና ዮናስ ቬጋስ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡ በተለይም ዮናስ ቬጋስ በተጣለበት ሽምግልና አርቲስቱን ይዞ ወደኢትዮጵያ የማምጣት አላማ ሰንቆ ወደአሜሪካ እንደሄደም ምንጮቻችን ነግረውናል፡፡

 

ሚኪያስ መሐመድ አጭበረበበት የተባለው ደረቅ ቼክ

ስልኩን የዘጋውና በቫይበርም ቢሆን ከዮናስ ቬጋስ ውጭ ለማንም መልስ የማይሰጠው አርቲስት ሚኪያስ መሀመድ አሁን ለሽማግሌዎቹም ትልቅ ራስ ምታት ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ዮናስ ቬጋስ አሜሪካ ከገባ በኋላ አርቲስቱ የእሱንም ስልክ መመለስ(በቫይበር) አቁሟል፡፡ አርቲስት ሚኪያስ መሀመድ ከበርካታ ግለሰቦችና ታዋቂ ሰዎች ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ይዞ ወደአሜሪካ ለመሰወር የቻለው የጎማና የሲሚንቶ ንግድ በጋራ እንስራ በማለት ነበር፡፡ ይህ ከላይ ያቀረብነው ቼክ አርቲስት ሚኪያስ መሀመድ ከሰጣቸው ባዶ ቼኮች አንዱ ሲሆን የከሰሱትና አሳስረውት የነበሩትም እኚሁ ግለሰብ ናቸው፡፡ እኚህ አቶ ሰይፍ ዳሳ የተባሉት ግለሰብ በላስ ቬጋስ ሎተሪ ደርሷቸው ወደኢትዮጵያ በመጡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከአርቲስት ሚኪያስ መሀመድ ጋር ተገናኝተው 2 ሚሊዮን ብር ለጎማ ኢንቨስትመንት በሚል የሰጡ ነበሩ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኤታማጆሩ የጥላቻ መግለጫ ላይ የተሸከመው ማዕረግ ለምን ከበደው?

 

ከአርቲስት ሮማን በፈቃዱ ሁለት ልጆችን የወለደው አርቲስት ሚኪያስ መሀመድ አሁን በኢቢኤስ እየተላለፈ ባለው ‹‹ዳና›› ድራማ ወሳኝ ገጸ ባህርይ ያለው መሆኑ ይታወቃል፡፡ የ‹‹ዳና›› ድራማ ምንጮቻችን እንደገለፁልን አርቲስቱ በጥቅምት ወር ውስጥ እንደሚመለስ በመናገሩ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ከአገር መጥፋቱ ስለተረጋገጠ ደራሲዎቹ እሱ የሌለበት ሌላ ታሪክ ለመፃፍ ተገደዋል፡፡

 

አርቲስት ሚኪያስን አሜሪካን ሃገር ይዞታል በተባለው በስልክ ቁጥሩ ደውለን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም:: እንዳገኘነው የርሱንም ምላሽ ይዘን እንቀርባለን::

ተጨማሪ ወሬዎችን እየተከታተልን እናቀርባለን፡፡

Share