በምስራቅ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች በጅምላ እየታሰሩ ነው ተባለ • ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ነው

(ነገረ ኢትዮጵያ) በምስራቅ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች ‹‹የማዳበሪያ ዕዳ አልከፈላችሁም›› በሚል በገፍ እየታሰሩ መሆኑን ምንጮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ ወስዳችኋል የተባሉትን የማዳበሪያ እዳ እንዲከፍሉ እየተጠየቁ እንደሆነ የገለጹት ምንጮች በአንድ ቀበሌ ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች በጅምላ መታሰራቸውን ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሮች እነሱ ወስደውታል የተባለውን ብቻ ሳይሆን በሞት የተለዩትን ዘመዶችን ዕዳ ጭምር ካልከፈላችሁ ተብለው ለእስር እየተዳረጉ መሆኑም ተሰምቷል፡፡ የጅምላ እስሩ ከሰኔ 15/2007 ዓ.ም እንደተጀመረ የገለፁት የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ለሳምንት ያህል የታሰሩት አርሶ አደሮች ሰኔ 21/2007 ዓ.ም ቢለቀቁም ሌላ ዙር እስር በመጀመሩ በርካታ አርሶ አደሮች ለእስር ሰለባ ሆነዋል ብለዋል፡፡

ከእስር በተጨማሪ ‹‹ቤታችሁን እናፈርሳለን!›› የሚል ማስጠንቀቂያ እየደረሳቸው መሆኑን የገለፁት አርሶ አደሮቹ የሚፈፀምባቸው በደል ከምርጫው ጋር የተያያዘና ኢህአዴግን አይደግፍም በሚል ቂም በቀል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በምስራቅና ምዕራብ ጎጃም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ማሰርና ማዋከብ አሁንም የቀጠለ ሲሆን የእንገድላችኋለን ማስፈራሪያ የደረሳቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ቀያቸውን ጥለው ለስደት መዳረጋቸው ገልጸዋል፡፡ የቀበሌ ሚሊሻና ከወረዳው የተላኩ ቡችሌዎች በሚያደርሱባቸው ዛቻና ማስፈራሪያ ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ የገለጹት ቄስ ዋልተንጉስ የሳሙኤል አወቀን አይነት እጣ ፈንታ እንዳይገጥማቸው በመስጋት መሰደዳቸውን ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል፡፡ ኢህአዴግን ትቃወማለህ በሚል ከፍተኛ ዛቻ እንደደረሰባቸው የገለፁት ቄስ ዋልተንጉስ ‹‹ከፍተኛ ዛቻና ማስፈራሪያ ሲያደርሱብኝ ቆይተዋል፡፡ አሁንም ቤቴ ድረስ እየመጡ እየፈለጉኝ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ የሳሙኤል አወቀ አይነት እጣ ፈንታ እንዳይገጥመኝ በመስጋቴ ልጆቼን፣ ሀብትና ንብረቴን ጥዬ መጥቻለሁ›› ብለዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ተቃውሞው ተቀጣጠለ አዲስ አበባ ባህር ዳር ምሽቱን ህዝቡ ወጣ ቪዲዮ"አብይ ይውረድ"/መንግስት አመነ አሁን መግለጫ ሰጠ
Share