April 27, 2015
4 mins read

በባህር ዳር መስቀል አደባባይ እና የህዝብ ተቋማት መፍረሳቸው ተረጋገጠ

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

ባለፈው ታህሳስ 2007 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሀይማኖት ተከታዮች ሀይማኖታዊ በዓላትን የሚያከብሩበት (በተለይ ጥምቅትና መስቀል በዓላትን) ስፍራ መስቀል አደባባይ በከፊል እና የተለያዩ የህዝብ ተቋማት ‹‹ለመንገድ ልማት›› በሚል ሊፈርሱ ይችላሉ መባሉን ተከትሎ የከተማዋ ህዝብ ለተቃውሞ ወጥቶ ዜጎች በመንግስት ታጣቂዎች መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ እነዚህ ህዝብ የሞተላቸው ተቋማትና የሐይማኖት ቦታ ከሰሞኑ መፍረሳቸው እርግጥ መሆኑን የነገረ ኢትዮጵያ ዘጋቢ በቦታው ተገኝቶ በመመልከት አረጋግጧል፡፡

(የባህር ዳር ከተማ)
በባህር ዳር መስቀል አደባባይ እና የህዝብ ተቋማት መፍረሳቸው ተረጋገጠ 1

በከተማዋ ከአዝዋ ሆቴል እስከ ግዮን ሆቴል በሚወስደው መስመር የሚገኙት የባህር ዳር የህዝብ ቤተ-መጽሐፍት ሙሉ ለሙሉ፣ የባንክ ስራ የሚሰራበት እድሜ ጠገብ ህንጻ ሙሉ ለሙሉ፣ እና የህዝቡ ተቃውሞ ዋና ምክንያት የሆነው መስቀል አደባባይ በከፊል ፈርሰዋል፡፡ የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት እና ሙሉዓለም የባህል ማዕከል ደግሞ አጥሮቻቸው እንዲፈርሱ ሆኗል፡፡

የነገረ ኢትዮጵያ ዘጋቢ በስፍራው ተገኝቶ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚገልጹት ከተማ አስተዳደሩ እነዚህን የህዝብ ተቋማት ሲያፈርስ ዙሪያ ገባውን በፌደራልና በክልሉ ፖሊስ አጥሮና የሚቆረጡ ዛፎችንና ሌሎች ፍርስራሾችን በፖሊስ መኪና ብቻ እያጓጓዘ ነው፡፡ ይህም አስተዳደሩ ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት ውስጥ ሆኖ ተቋማቱን ማፍረሱን ያመለክታል ይላሉ ነዋሪዎቹ፡፡
ታህሳስ ወር ላይ ተቀስቅሶ በነበረው የህዝብ ተቃውሞ ወቅት የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ አቶ ላቀ አያሌው ‹‹ህዝብ ያልፈለገውና በተቃውሞ ድምጽ ያሰማበት ፕሮጀክት ተፈጻሚ አይሆንም፤ ስለዚህ ካልፈለጋችሁ ይቀራል›› በሚል ህዝቡን ለማረጋጋት መሞከራቸው የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ግን ህዝቡ ይሁንታ ሳይሰጣቸው ወደማፍረስ መግባታቸው ተመልክቷል፡፡

አስተዳደሩ ህዝቡን በኃይል እያስፈራራ ነው የሚሉት የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የፌደራል ፖሊስ መስቀል አደባባይ ጎን በሚገኘው ሁለገብ የወጣቶች ማዕከል ውስጥ ከትሞ በተጠንቀቅ መቀመጡን ለንግግራቸው እንደ ዋቢ ያነሳሉ፡፡ ይህን የነዋሪዎችን ጥቆማ በማስመልከት ወደ ወጣት ማዕከሉ ያመራው የነገረ ኢትዮጵያ ዘጋቢም የፌደራል ፖሊስ አባላት በማዕከሉ በብዛት እንደሚገኙ ማረጋገጥ ችሏል፡፡

Previous Story

(ለትውስታ) አቡበከር አህመድ ከመታሰሩ በፊት ከራድዮ ፋና ጋር ያደረገው ቃለምልልስ – [ሊደመጥ የሚገባና አዲሱን የወያኔ ሴራ የሚያጋልጥ]

Next Story

በሚኒሶታው መድሃኔዓለም ቤ/ክ በሊቢያ በስቃይ ላሉ ኢትዮጵያውያን መርጃ በአንድ ቀን ከ20 ሺህ ዶላር በላይ ተሰበሰበ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop