በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ 5000 ሄክታር በሚጠጋ እርሻ ላይ ውድመት ደረሰ

(ፍኖተ ነፃነት) የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የኮምቦልቻ ከተማ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር በ07 ቀበሌ ልዩ ስሙ ትዩ አምባ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ላይ በቱርካውያን የባቡር መስመር ዝርጋታ ካምፓኒ የደረሰውን የአዝእርት ጭፍጨፋ በአካል በመሄድ የመስክ ግምገማና ምልከታ እንዲሁም ከአርሶ አደሮች ጋር ውይይት ማካሄዱን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመለከተ ፡፡

ለዝግጅት ክፍላችን በደረሰው መረጃ መሰረት ህዳር 21 ቀን 2007 ዓ.ም አምስት አባላትን ያካተተው በኮምቦልቻ የአንድነት ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቦታው ድረስ በመሄድ የመስክ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ የደረሰውን ጉዳት ገምግሟል፡፡ በዚህም መሰረት አምስት ሺህ ሄክታር በሚጠጋ የአርሶ አደሩ እርሻ ላይ ከፍተኛ የሆነ ውድመት መድረሱን ጉዳት የደረሰበት ማሳም በደረሱ የጤፍ፣ የስንዴ፤ የማሽላ እንዲሁም ሌሎች አዝእርቶች የተሸፈነ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በስፍራው ተገኝተው የደረሰውን ጉዳት ያስረዱት ከ100 በላይ አርሶ አደሮች “ያለኛ ስምምነት፤ ተገቢው ካሳ ሳይከፈለን እንዲሁም አዝእርታችንን እንኳን ሳናነሳ ላባችንን ያፈሰስንበትን ምርት በግሬደር ከአፈር ጋር ደባልቀውታል” ብለዋል፡፡

አቶ መሀመድ ሰይድ የተባሉ አርሶ አደር እንደገለፁት የአዝእርት ማጥፋት ድርጊቱ ሲፈፀም በቦታው የነበርኩ ቢሆንም በህግ አምላክ ልፋታችንን ገደል አታስገቡብን፤ ምርታችንን እንኳ እናንሳ ብንልም ከቱርካውያኑ ጋር የተመደቡ ፖሊሶች በሙስና በታገዱት ከንቲባ የተፈረመ ደብዳቤ በማሳየት ታዘናል፤ ልማት ለማደናቀፍ ከሆነ እናስራችኋለን፤ ምንም አታመጡም እንደተባሉ በምሬት አስረድተዋል፡፡ የተሰበሰቡት አርሶ አደሮች “አርሰን እንኳ መብላት ካልቻልን ከንግዲህ ሀገርም የለን፤ ሀገራችንን ያሳዩን፤ ከተፈጥሮ ጋር ታግለን፤ ያለማነውን አዝመራ መንግስት ካጠፋው፤ ነገ የማዳበሪያ እዳ ክፈሉ መባላችን ስለማይቀር ያለን እጣ ፈንታ ሀገር ጥሎ መሰደድ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጋዜጠኛ በፍቃዱ ሞረዳና ሳዲቅ አህመድ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ | በኦሮሚያ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ቁጣ ብሔራዊ መልክ አለመያዙ ምክንያቱ ምንድነው? - ያዳምጡት

በአካባቢው የሚገኝ ቀበሌ አስተዳዳሪ ለማነጋገር ባደረግነው ጥረት “እኛ ከበላይ ታዘን ነው፤ ፈፅሙ የተባልነውን ነው የፈፀምነው” በማለት መልሰዋል፡፡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የቱርካውያኑን ካምፓኒ እና የከተማ አስተዳደሩን ኃላፊዎች ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ አርሶ አደሮቹ ወዴት አቤት እንደምንል ባለማወቃችን እየተፈፀመብን ያለውን ግፍና መከራ ቁጭ ብለን ለማየት ተገደን ቆይተናል አሁን ግን ህዝቡን በማስተባበር ከአንድነት ፓርቲ ጋር በመሆን ተቃውሟችንን እናሰማለን፤ የደረሰብንን መንግስታዊ ግፍ ለመላው ኢትዮጵያዊ አሰሙልን በማለት በስፍራው ለተገኙ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች አሳስበዋል፡፡

በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ስር ካሉት የገጠር ቀበሌዎች (07 ቱሉ አዳሜ፤ 09 ትዩ አምባ፤ 010 መጠኔ እና 011 ጋሌሳ) የሚባሉ ቀበሌዎች ተካተው ይገኛሉ፡፡ እስካሁን ባገኘነው መረጃ መሰረት በእያንዳንዱ ቀበሌ በአማካይ 2000 (ሁለት ሺህ) አባወራ አርሶ አደሮች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ አራት የገጠር ቀበሌዎች በኢንቨስትመንት ሰበብ ከፍተኛ የሆነ የመሬት ቅርምት የሚካሄድባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡

Share