ከግብረሰዶማውያኑ ጀርባ  (አርአያ ተስፋማሪያም)

አርአያ ተስፋማሪያም

ከጥቂት አመት በፊት በኢትዮጵያ በተለይ አዲስ አበባ የሚገኙ ግብረሰዶማውያን ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ በሸራተን ሆቴል የሃይማኖት አባቶች ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት በስፍራው ተገኝተዋል። ፕሮግራሙ ሊጀመር 15 ደቂቃ ሲቀረው በድንገት የደህንነት ሰዎች ይገቡና ጋዜጠኞች እንዲወጡ ያደርጋሉ። ቀጥሎ ለሃይማኖት መሪዎቹ « ይህን መግለጫ መስጠት አትችሉም» ተባሉ። « ማነው ከልካዩ?..» ሲሉ ጠየቁ፤ ጭራሽ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው። የተቃውሞ መግለጫው በዚህ መልኩ ተደናቀፈ። በመቀጠል ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ተጠየቀ። የሸራተኑን መግለጫ ያደናቀፈው ባለስልጣን ጣልቃ ገብቶ ሰልፉን አስከለከለ። ይህን ሁሉ ያደረጉት የወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚ/ር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም መሆናቸውን የቅርብ ምንጮች ያረጋግጣሉ። በቅርቡ አሜሪካ መጥተው የነበሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ በአፍሪካ ከጤና ጋር በተያያዘ አንድ ተቋም በሃላፊነት እንዲመሩ ተፈልገዋል። ከያዙት ስልጣን ፓርቲያቸው እንዲለቃቸውና አሜሪካኖቹ ወደሚፈለጉት ቦታ ዶክተሩን ለመውሰድ እቅድ መኖሩን አንዲት ከፍተኛ ሃላፊን በመጥቀስ ምንጮች ገልፀዋል።

ዶ/ር ቴዎድሮስ ስለዚህ ጉዳይ ይነጋገሩ አይነጋገሩ የታወቀ ነገር የለም። ዶክተሩ የተመረጡት « በኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚ/ር ሆነው ብዙ ነገር ሰርተዋል፤ ለምሳሌ ኤ.ች.አይ.ቪ/ ኤድስ፣ የወሊድ ቁጥጥር፣ የጤና ተቋማት ግንባታ..» ወዘተ በሚል ይጠቅሳሉ። ነገሩ ወዲህ ነው..የሚሉ ወገኖች ባለስልጣኑ የተፈለጉት « ለግብረሰዶማውያን መብት ዘብ በመቆም አሜሪካ በዚህ ዙሪያ ለምታራምደው አቋም ዶ/ር ቴዎድሮስ በተደጋጋሚ አጋርነታቸውን በማሳየታቸውና በተጨማሪ ስለግብረሰዶማውያን መብት ደግፈው ስለሚፅፉ ነው» ይላሉ። የሚያሳዝነው ዶ/ር ቴዎድሮስ « የማሰር ሱስ የለብንም..» ከማለት አልፈው የታሰሩትን ሙስሊሞች ከጓንታናሞ ጋር ለማያያዝ መሞከራቸውና ቀጥሎ ለማስተባበል መሯሯጣቸው ነው። እውነት ለመብት የቆሙ ቢሆን ኖሮ ከአምላክ ድንጋጌና ተፈጥሮ ላፈነገጡ ሳይሆን ካለሃጢያታቸው በእስር እየተሰቃዩ ለሚገኙ ወገኖች መሆን ነበረበት።