June 20, 2014
7 mins read

በሃዋሳ 3 የአንድነት አመራርና አባላት ታሰሩ – “እስሩ ቅስቀሳውን አያስተጓጉለውም”

አንድነት ፓርቲ እሁድ ሰኔ 15 ቀን 2006 ዓ.ም “የሚሊዮኖች ድምፅ ለመሬት ባለቤትነት” በሚል መሪ ቃል በሃዋሳ ከተማ ለሚደረገው የተቃውሞ ሰልፍ በራሪ ወረቀት በማደልና ፖስተር በመለጠፍ ላይ የነበሩት የአንድነት ፓርቲ አመራርና አባላት ታሰሩ፡፡ ሲዳማ ዞን የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ሲዳ ኃይሌ እንዲሁም ከማዕከል ለሰልፉ እገዛ ለማድረግ ከሄዱ የፓርቲው አባላት መካከል አቶ ኃይሉ ግዛውና ወጣት ደረጄ ጣሰው ላይ ህገወጥ እስር መፈፀሙን ከስፍራው ለፍኖተ ነፃነት የደረሰው መረጃ አመላክቷል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ባለስልጣናት ሰልፉን ለማደናቀፍ የሚያደርጉት የተቀነባበረ እንቅስቃሴ ያልበገራቸው ሌሎቹ የቅስቀሳ ቡድኑ አባላት የተጠናከረ ቅስቀሳ ለማድረግ መዘጋጀታቸው ታውቋል፡፡

ምንጭ ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ

ራሳችንን ነጻ እናዉጣ ፤ ሰኔ 15 ቀን አዋሳ እንገናኝ

– አማኑኤል ዘሰላም

የደቡብ ክልል ዋና ከተማ ናት። በርካታ ብሄረሰቦች በፍቅር የሚኖሩባት ዉብ ከተማ። ሰኔ 15 ቀን 2006 ዓ.ም ደሴን፣ ባህር ዳርን፣ አዳማን፣ ጊዶሌን አዲስ አበባ እና ደብረ ማርቆስን በመቀላቀል ድምጿን ታሰማለች። አዋሳ !!!!
የሚሊዮኖች ድምጽ ለፍትሕና ለመሬት ባላቤትነት በሚል መርህ በሐዋሳ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተጠርቷል። ለሰልፉ የከተማዋ ባለስልጣናት እውቅና የሰጡ ሲሆን፣ የአንድነት አባላትን ደጋፊዎች ቅስቀሳ ጀምረዋል።
የሰላማዊ ትግል ቁልፍ ሥራ ትግሉን ወደ ሕዝቡ ማዉረድ ነው። የሚሊዮኖች እንቅስቃሴም እያደረገ ያለው ይሄንኑ ነው። ይሄን ሰልፍ ለማድረግ የታሰበው ከአንድ ወር በፊት የነበረ ቢሆንም የአገዛዙ ባለስልጣናት የተለያዩ ምክንያቶች እየሰጡ ሰልፉን እስከአሁን እንዲዘገይ አድርገዉት ቆይተዋል። በዞኑ የአንድነት አመራር አባላት ባሳዩት ትእግስትና ቁርጠኝነት ሰልፉ እዉቅ አግኝቶ ቅስቀሳ ተጀምሯል።
በሚቆጣጠራቸው የመገነኛ ብዙሃን ለሕዝብና ለአገር መልካም እንዳደረገ፣ ለሕግ የበላይነትና እንደቆመ፣ ሁሉንም በእኩል እንደሚያይ ኢሕአዴግ ይለፍፋል። «ኢሕአዴግ ለአዋሳ ሕዝብ ጥቅም የቆመና ሕዝቡን የሚያከብር ነው ወይ ? ባለስልጣናቱ ህዝቡን የሚያሰቃዩና የሚያንገላቱ ሳይሆን በቅንነት ሕዝብን ያገለግላሉ ወይ ? » የሚሉ ጥያቄዎች ቢነሱ መልሱ «አይደለም» የሚል እንደሆነ የአዋሳ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮያ ሕዝብ ያውቀዋል።
ኢሕአዴጎች የሚኩራሩበትና ግፍ ሲሰሩ ምንም የማይከብዳቸው «ሕዝቡ ፈሪ ነው ፤ ድምጹን ማሰማት አይደፍርም። ከኛ ፍቃና ትእዛዝ ዉጭ አይወጣም» የሚል እምነት ስላላቸው ነው። የአዋሳ ህዝብ ኢሕአዴጎች እንደሚያስቡት ሳይሆን፣ መብቱን፣ ነጻነቱን፣ ክብሩን አሳልፎ የማይሰጥ ህዝብ መሆኑን የሚያሳይበት ሰልፍ ተዘጋጅቷል። የኣዋሳ ህዝብ »እምቢ ለአምባገነንት፣ እምቢ ለዘረኝነት፣ እምቢ ለሙስና ፣ እምቢ ለፍትህ መጓደል፣ እምቢ ለኑሮ ዉድነት … » የሚልበት ሰልፍ የሚደረግበት ቀን እንሆ ደርሷል። ሰኔ 15 !!!!!
አገር ነጻ የምትሆነው፣ ክልሎች ነጻ ሲሆኑ ነው። ክልሎች ነጻ የሚሆኑት ወረዳዎች ነጻ ሲሆኑ ነው። ወረዳዎች ነጻ የሚሆኑት ቀበሌዎች ነጻ ሲሆኑ ነው። ቀበሌዎች ነጻ የሚሆኑት ቤተሰብ ነጻ ሲሆን ነው። ቤተሰብ ነጻ የሚሆነው እያንዳንዳችን በግልሰብ ደረጃ ነጻ ስንሆን ነው። በግላችን «ለመብቴ መቆም አለብኝ። እስለመቼ ባሪያ ሆኜ፣ አቅርቅሬ እኖራለሁ» በማለት ለራሳችን ፣ በግላችን ነጻነትን ስናወጅ ፣ ያኔ ከሌሎች ጋር ሆነ የነጻነትን ደዉል ለመደወል አይከብደንም።
እንግዲህ የነጻነትን መልእክት ለራሳችን እናስተላልፍ። ዛሬ እኛ በራሳችን አይምሮ ዉስጥ ፈቅደን ካስቀመጥነው ፍርሃትና የሕሊና መሽመድመድ ነጻ እንዉጣ። አዋሳ የምንኖር ሰኔ 15 ቀን የሚደረገዉን ሰልፍ እንቀላቀል። ከአዋሳ ዉጭ ያለን በአገር ዉስጥም ሆነ ከአገር ዉጭ የምንኖር ወገኖች በአዋሳ ያሉ ዘመድ፣ ወዳጆቻችንን በስልክ፣ በኢሜል፣ በቫይበር ፣ በቴክስት በማግኘት ሰልፉን እንዲቀላቀሉ እናበረታታ። በሶሻል ሜዲያ፣ በራዲዮኖችና ድህረ ገጾችም በፓልቶኮች ቅስቀሳዉን እናፋፍም። በገንዘብ ድጋፍ እናድርግ። በአካል ባንገኝም በመንፈስ ሰልፉን እንቀላቀል።
ይህ የአንድ ሰው፣ ወይንም የአንድ ፓርቲ ንቅናቄ አይደለም። ይህ የሚሊዮኖች ንቅናቄ ነው። ይህ የሕዝብ ትግል ነው። በመሆኑም የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ ያስፈልጋል። እያንዳንዳችን የድርሻችንን ለመወጣት እንዘጋጅ። ከሚሊዮኖች አንዱ እንሁን ። አዋሳ በአካልም ይሁን በመንፈስ እንገናኝ !

Tilahun Gugsa
Previous Story

” እዚህ አሜሪካ ብዙ ኢትዮጵያውያን በተለይም ህፃናቶችና ታዳጊ ወጣቶች ቤቶች ድራማን በመከታተላቸው በጣም ደስ ብሎኛል” – አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ

Next Story

በምስራቅ ጎጃም የመኢአድ አባል በካድሬዎች ድብደባ ሕይወታቸው አለፈ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop