ልክ የዛሬ 17 ዓመት ሚያዝያ 30 ቀን 1989 ዓ.ም አቶ አሰፋ ማሩ ወደ ቤቱ ሊገባ ሲል በወያኔ ተረሽኖ ሕይወቱ አለፈ

በስደት ከሚገኙ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት የተሰጠ መግለጫ

የኢመማ ጀግኖች ሰማእታትን እናስብ።

የዛሬ 17 ዓመት ሚያዚያ 30 ቀን 1989 ዓ.ም አቶ አስፋ ማሩ ከቤቱ በሰላም ወጥቶ ወደ ሥራ በመሔድ ላይ እያለ በአዲስ አበባ ሐምሌ19 የሕዝብ መነፈሸ አካባቢ በጠራራ ጸሐይ በወያኔ/ኢህአዴግ ነፍሰ ገዳይ ፖሊሶች የጥይት እሩምታ ሰለባ የሆነ ጀግና ኢትዮጵያዊ ነው።

አቶ አሰፋ ማሩ በጊዜው በወሎ ክፍለሀገር በላስታ አውራጃ መቄት ወረዳ በ1951ዓ.ም ተወለደ። በመምህርነት ሙያ ከማገልገሉም ባሻገር በሙያ ማህበሩ የአመራር አባል በመሆንም የመምህራንን መብትና ጥቅም ለማስከበር ፣ የትምህርቱን ጥራት ለማስጠበቅ በሚደረገው ትግል በግምባር ቀደምትነት ከሚታገሉት አንዱ ሆኖ ሕይወቱ በግፈኞች እስካለፈበት ዕለት በጽናት ቆሞ ቆይቷል። በወቅቱ በነበረው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤም በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት የላቀ ድርሻ አበርክቷል።

በዚህ በኩል ኢመማ ለሙያው ክብር ፣ለትምህርት ጥራትና በእኩልነት መዳረስ፣ በነፃ ለመደራጃት፣ ለሰብአዊ መብቶች መጠበቅ ፣ ለፍትሕና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን በአጠቃላይ ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት ታግለው እያታገሉ መሰዋዕትነት የከፈሉ በርካታ ጀግኖችን አፍርቷል። አቶ ሺመልስ ዘውዴ በወያኔ/ኢህአዴግ ፖሊስ ጣቢያ ለአንድ ወር ያህል ታስሮ በነበረበት ጊዜ ለከፋ ብርድ ሕመም በመጋለጡ፣ ሕክምና ባለመግኘቱና በደረሰበት እንግልት ከእስር ከተፈታ በኋላ ወዲያውኑ ሕይወቱ አልፏል። አቶ ከበደ ደስታ በኢመማ ሥር የአባት መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት የነበሩትም ታሰረው ሕይወታቸው እስር ቤት እንዳሉ አልፏል። እቶ አወቀ ሙሉጌታ የኢመማ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና በጥንካሬው የምናደንቀው የኢመማን ጽ/ቤት ለተላጣፊ ለአለመስጠት የሙጥኝ እንዳለ አሟሟቱ በግልፅ ሳይታወቅ በመጋቢት ወር 1999ዓ.ም መንገድ ላይ ሞቶ ተገኝቷል። አቶ ሰርዶ ቶላ፣አቶ
ፈቃዱ ፍርዴና ሌሎችም ኢመማ ካፈራቸውና በዕምነነታቸው ጸንተው ካለፉት ጀግኖች ቀዳሚዎች ናቸው። በቅርቡ በሕዳር ወር 2004ዓ.ም ደግሞ ፍትሕ በሌለበት አገር መኖር ባዶ ሕይወት ነው በማለት ራሱን በጋዝ አንድዶ መስዋዕት የሆነው መምህር የኔ ሰው ገብሬ ቆራጥነቱ ሕዝቡን ያስደመመ ሆኖ አልፏል።መምህራን በተለይ ማህበረሰቡ በአጠቃላይ ለእነዚህ ለኢመማ ጀግኖች ክብርና ሞገስ እንደሚያጎናጽፏቸው እናምናለን። የተሰውለትን ቅዱስ ዓላማ ከግቡ ለማድረስ ከሁላችንም አገራዊና ሕዝባዊ ግዴታ ይጠበቃል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እናንተ ደጀን በመሆን ከጀርባችን ሁኑልን እንጂ ወታደራዊ ጥበቡን ለእኛ ተውልን!! ጄነራል አበባው ታደሰ

አገራችን የወንበዴዎች መፈንጫ ሆነ እንዳትቀር፣ ሕልውናዋ አደጋ ላይ እንዳይወድቅና በዘርና በቡድን እየተጎተትን መበታተን እንዳይደርስ ፣ ዜጎች ሁሉ የነዚህን ጀግኖች የመስዋዕትነት አርአያ በመከተል ይህን አገር አጥፊ ቡድን ለማስወገድ በጋራ እንዲነሱና እንዲታገሉ በሰደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል ። ቀጥሎ ያለውን አጭር ግጥም ለኢመማ ጀግኖች መታሰቢያ እንዲሆን አቅርበናል።

ቢሞትም ሕያው ነው!!

ለራሴ የማይል -ወገን አስቀድሞ፣
መስዋዕት የሚሆን ግፈኛን ተፋልሞ፣
ለተተኪው ትውልድ የሚያስብ አርቆ፣
ከንቱ ውዳሴና የግል ጥቅምን ንቆ፣
በዕምነቱ ከፀና ሞትንም ሊቀበል፣
ሕያው ነው ተግባሩ እሱ ሞተ አንበል።
አፋሽ አጎንባሹ አየን ተበራክቶ፣
ከግፈኛ አብሮ ሊያድር ሆዱን ሞልቶ፣
እንዲህ ባለው ጊዜ እንዲህ ባለው ወቅት፣
ጀግና ሰው ያበቅላል-ያፈራል መሬት፣
ለወገኑ ቤዛ የሆነ ጀግና ሰው ፣
ታሪክ ይዘክራል ቢሞትም ሕያው ነው።

ያለመሰዋዕትነት ነፃነት አይገኝም!!
በጋራ ታግለን ሕዝባዊ ሥርዓት እንገንባ!!

Share