April 18, 2013
29 mins read

የአፍሪካ አምባገነን መሪዎችና የብዕር ጀግኖቿ ጦርነት

በፍቅር ለይኩን ~ (fikirbefikir@gmail.com)

ብዕር …፣ ብዕር …፣ የብዕር ኃይል ምንጊዜም ያሸንፋል!!
(ናይጄሪያዊው የብዕር ጀግና ኬን ሳሮዊዋ)

የቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት ተመሠረተበትን የ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ለማክበር በተለይ የኅብረቱ ዋና መቀመጫና ለአፍሪካ አንድነትም ሆነ ለኅብረቱ እውን መሆን በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ብርቱ ጥረት ግንባር ቀደም ሚና በተጫወተችው በኢትዮጵያ፣ በመዲናችን አዲስ አበባ በደማቅ ሁኔታ ለማክበር መጠነ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተቋቋመና አብዛኞቹ አፍሪካ አገራትም ነፃነታቸውን ከተጎናጸፉ በኋላ አፍሪካውያን በልባቸው ትልቅ ተስፋንና ራእይን ሰንቀው ነበር፡፡ አፍሪካ በጥቁር አፈሯ የአብራኳ ክፋዮች፣ በልጆቿ መሪነት ወደተሻለ ፖለቲካዊ አስተዳደርና መረጋጋት፣ ማኅበራዊ ተሐድሶ፣ ኢኮኖሚያዊ እምርታና እድገት ትገሠግሣለች ተብሎ ነበር በብዙዎች ዘንድ የተገመተው፣ የታሰበው፣ የታቀደውም፡፡
ግና ለአፍሪካ ይመጣል ተብሎ የታሰበው፣ ያ ብሩህ ዘመን የተገመተውንና የተጓጓለትን ያህል ብዙም ተስፋ ሰጪና ብሩህ አልነበረም፡፡ እዚህም እዛም የፈነዱት የብዙ አፍሪካውያን ሕይወት የቀጠፉ የእርስ በርስ ግጭቶች፣ ስደትና መፈናቀል፣ በወታደሮችና በጦር ኃይል የታገዘ ደም አፋሳሽ የሆኑ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች፣ ሙስናና ዝርፊያ አኅጉሪቱን ባልተጠበቀ ፍጥነት ወደ ምድራዊ ገሃነምነት ነበር የቀየሯት፡፡
በዚህ አጭር መጣጥፌ በብዙ ተስፋ ስለተደረገው የትላንትናው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት በአፍሪካ አገራት ውስጥ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በሌሎችም ዘርፎች ስላስመዘገበው ስኬቶች፣ ስላጋጠሙት እንቅፋቶችና ውድቀቶች ለመተንተን አይደለም አነሣሴ፡፡
ይሁን እንጂ የዚህ ጽሑፌ ዋና ትኩረት የኅብረቱን 50ኛው የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ለማክበር ሽር ጉድ እያሉ ባሉት አፍሪካውያን አገሮች ውስጥ የምድሪቱ የብዕር ጀግኖች በየአገራቸው የተነሡትን አምባገነኖችን፣ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን፣ ሙስናን፣ የአስተዳር ብልሹነትን፣ መሪዎቻቸው የተዘፈቁበትን የሞራል ዝቅጠትንና ውድቀትን… ወዘተ በማጋለጣቸው የተነሣ በየጊዜው የተነሡ አፍሪካውያኑ አምባገነኖች የብዕር ጀግኖቻቸውን ያሳደዱበትን፣ ያጋዙበትንና እንዲያም ሲል ሞት ያወጁባቸውን የአፍሪካ የምንጊዜም ምርጥ የብዕር ጀግኖች ስለሆኑ ኃያላኖች ታሪክ ጥቂት ላካፍላችኹ ወድጄ ነው፡፡
ዛሬም ድረስ የየአገሮቻቸውን አምባገነኖች ለማረም የተነሡትን የከበሩ ምሁራኖችን፣ ጸሐፊዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የጥበብና ብዕር ሰዎችን ጉሮሮ ለመፍጥረቅ እንደወትሮው ኃይል የማያንሳቸው አፍሪካና አፍሪካውያን አምባገነኖች በየጓዳው በተጽእኖ በትርና በአድርባይነት መርዝ ዛሬም ድረስ ስንቱን የኪነ ጥበብ ሊቅ በግፍ ረግጠው እየገዙ እንዳለ ሊታሰበን ይገባል፡፡ ለአብነትም ያህል በአገራችን በቀደመው ትውልድ ዘመን እነ አቤ ጉበኛና እነ በዓሉ ግርማ የመሳሰሉ ኃያላኖች በብዕራቸው አማካይነት ስለ እውነትና ስለ ፍትሕ በመጮኻቸው ነበር የእብሪተኞችና የአምባገነኖች ሰለባ ለመሆን የተዳረጉት፡፡
በእኛው ዘመንም በዓለም አቀፍ ደረጃ የብዙ ሽልማቶች ባለቤት የሆነው እንደ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ እንዲሁም ከሰሞኑ እንኳን የመንግሥታቱ ድርጅት ዩኔስኮ ለነፃ ፕሬስና ሐሳብን በነፃነት ለመግለጥ እውን መሆን አምርራ በብዕሯ የታገለች ምርጥ፣ ጀግና ሴት፣ የብዕር አርበኛ ተብላ የተሸለመችው ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙና ሌሎችም በገዛ አገራቸውና መንግሥታቸው ‹‹አሸባሪ›› በሚል ሰበብ በወኅኒ እንዲወረወሩ ያደረጋቸው እምቢ ለእውነት፣ እምቢ ለፍትሕ፣ እምቢ ለነፃነት ባለችው ኃያል ብዕራቸው የተነሣ መሆኑን ማንም ይስተዋል ብዬ አልገምትም፡፡
መቼም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ማኅበሮች በታሪክ ‹‹አሸባሪዎችንና ሽብርተኞችን›› ሲሸልሙ፣ ሲሾሙና ሲያከብሩ አይተንም፣ ሰምተንም አናውቅም፡፡ ለመሆኑ መንግሥት ይህን እውነት በአደባባይ እያየና እየሰማ ምን እያሰበ፣ ምንስ መከራከሪያ እያዘጋጀ ይኾን?! ለመሆኑ ‹‹አሸባሪነትስ›› በመንግሥታችን መዝገበ-ቃላት ውስጥ ያለው ፍቺስ ምን ማለት ይኾን?!
ባለፉት ዓመታትም ወጣቱ ከያኒ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በጥበብ ሥራው የዛሬው የትላንቱን ለመቀጣትና ለመበቀል ከሆነ ራእዩና ፍላጎቱ ለኢትዮጵያ የታለመው ሰላም፣ ብልጽግና፣ እድገትና ዲሞክራሲ አድራሻው ወዴየት ነው?! ቂም በቀል ይቅር፣ ለአንድ እናት ምድራችን በማንዴላ የእርቅ መንፈስ እጅ ለእጅ እንያያዝ፣ እንደጋገፍ፡፡ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በዘር መለያየታችን ይቅር፣ ኢትዮጵያችን ሁላችንም የጋራ ቤት፣ የጋራ እናታችን ናት፡፡ ሰንደቀ ዓላማችን፣ ቋንቋችን ፍቅርና ፍቅር ብቻ ይሁን!!
አለበለዚያ ግን የዛሬው መንግሥት በተራው በትላንቱ ላይ በጥላቻ ጥርሱን የሚነክስ ከሆነና የበቀል ሰይፉን የሚያነሣ ከሆነ ‹‹አዲስ ንጉሥ እንጂ መቼ ለውጥ መጣ?!›› ብሎ በማዜሙ የተነሣ ከእውነት፣ ከፍቅር፣ ከፍትሕና ከእርቅ መንፈስ ጋር የተፋቱ ብኩኖችና እብሪተኞች በወጣቱ ከያኒ ላይ ጥርሳቸውን ክፉኛ ነክሰውበት ሲያጥላሉትና ሲያወግዙት ለመስማት የተገደድንበት አጋጣሚ ቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ በግሌ የማስታውሰው በኦሎምፒያ አካባቢ ተሰቅሎ የነበረው የወጣቱ ከያኒ ‹‹ጃህ ያሰተሰርያል!›› የሚለው የጥበብ ሥራው ፖስተር ከላይ እስከ ታች ነጭ ቀለም ተረጭቶ ያየኹበትን ትእይንት አሁን ድረስ ሳስታውስ አምባገነኖችና እብሪተኞች በልባቸው ያረገዙትን ክፋታቸውንና በቀላቸውን ለመተግበር ምን ያህል ርቀት ሊጓዙ እንደሚችሉ ነው በሐዘንና በጸጸት ውስጥ ሆኜ እንዳስብ ያደረገኝ፡፡
አፍሪካውያኑ አምባገነኖች በዚህ አካሄዳቸው አገራቸውን የዕድገት፣ የዲሞክራሲ፣ የነፃነትና፣ የፍትሕ ምች እንዲያጠናግረው የፈቀዱ ማን አለብን ባዮች ዓይኖቻቸውን ሳያርገበግቡ ምን መጠበቅ እንዳለባቸው አሳምረው ያውቁታል፡፡ ለእውነት፣ ለሰብአዊ መብቶች፣ ለፍትሕና ለሕዝብ ብሶት የቆሙ የጥበብ ድምፆችንና ሐቀኛ ብዕሮችን በዋሉበትና ባደሩበት እያደፈጡ ሲያሴሩና ጥበብን አልከስክሰው በእውነት ላይ ለመማገጥ የታቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ እናም ሊደፋፈሩ የሚገባቸውን ጀግኖቻቸውን ያዋክባሉ፣ ያሳድዳሉ፣ ያግዛሉ፣ ይገድላሉ፣ ያስገድላሉ፡፡
ድንግል አፍሪካ፣ በተፈጥሮ ሀብቷ አቻና አምሳያ የሌላት አፍሪካ… የማርና ወተት መፍለቂያ ምድር እማማ አፍሪካ፣ አውሮፓውያኑ የአፍሪካ በዕዳን ወራሪዎች ካደረሱባት ግፍና መከራ ያልተናነሰ ከማኅፀንዋ የወጡ፣ ጡትዋን ጠብተው ያደጉ ልጆቿ፣ ነፍጥ ማንገታቸው ልባቸውን በእብሪት የወጠረው ወታደራዊ መሪዎቿ ይህ ነው ማይባል የግፍና የመከራ ዘመንን አስቆጥረዋታል፡፡ ለዛሬ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት በነበሩት በጄኔራል ሳኒ አባቻ ዘመነ መንግሥት ለእስራትና ለሞት ስለተዳረገው ስለ ኃያሉና ጀግናው ብዕረኛ፣ ደራሲ ኬን ሳራዊዋ ታሪክ በጥቂቱ ላካፍላችኹ ወደድኹ፡፡
የናይጄሪያዊው ጁንታ መንግሥት የስቅላት ገመድ በአንገቱ ገብቶ በሕይወቱ ላይ ስለተፈረደበት የነፃነት ታጋይ፣ የጥበብ ፊታውራሪ፣ የሕዝብ ልጅ፣ የናይጄሪያውያኑ የኢጎኒ ጎሳ ተወላጅ፣ የሕዝቡ የቁርጥ ቀን ልጅ ስለሆነው ደራሲ፣ ገጣሚ፣ ሐያሲ፣ ነጋዴ፣ የፖለቲካ ሰው፣ ሃይማኖት ሰባኪ ኬን ሳሮዊዋ፡፡
የፈላጭ ቆራጩ የሳኒ አባቻ መንግሥት የደህንነትና የፀጥታ ክፍል ኃላፊዎች ኬን ሳሮዊዋ እትብት ከተቀበረበት ቀዬ ነዳጅ ቀድተው እንዳሻቸው መሆን እንደማይችሉ የተረዱት ናይጄሪያውያኑ አምባገነኖች ይህን በሕዝቡ ፍቅር የተነደፈውን ሐቀኛ ሰው ከማጥፋት ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ እናም ይህን የሕዝብ አለኝታ ከምድራቸው ሊያጠፉት መከሩበት፤ መክረውበትም አልቀረ ያን የሕዝባቸውን የንጋት ኮከብ ገና በአፍላ ዘመኑ ብርሃኑን ጨክነው አጨለሙት፣ አጠፉት፡፡
አምባገነኖቹ ሳሮዊዋን በቁጥጥር ስር ለማዋል ያቀናበሩለት የውንጀላ ሴራም እንዲህ የሚል ነበር፡፡ በዋና ከተማይቱ አቡጃ ትልቁ አደባባይ በጠራራ ፀሐይ በተጠመደ ፈንጅ የታፈሩና የተከበሩ የሚባሉ በሳኒ አባቻ ፊት ሞገስ ያገኙ ሦስት አዛውንቶች በድንገት ተገደሉ፡፡ የእነዚህ አዛውንቶች ግድያ ከኬን ሳሮዊዋ ጋር ሚያገናኘው ምንም ነገር አልነበረም፡፡ በወቅቱ በተደረገው ማጣራትም ግድያው የተፈፀመውም ሆነ አደጋው የተጣለው ወታደራዊውን ጁንታ በሚቃወሙ ወጣቶች መሆኑ ተገልፆ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ወታደራዊው አምባገነን መንግሥት ድርጊቱን በቀጥታ ከሳሮዊዋ ጋር በማያያዝ ለሳኒ አባቻ መንግሥት የእግር እሳት የሆነው የነፃነት ታጋዩ ኬን ሳሮዊዋ በዚህም አለ በዚያ በሐሰትም ቢሆን ተወንጅሎ ከሚወዳት አገሩና ሕዝቡ መወገድ ነበረበት፡፡ እናም ናይጄሪያዎቹ አምባገነኖች ይኽን ውሳኔ አስቀድመው አቅደውና ወስነው የዚህን ጀግና የብዕር ሰው ሞት/እረፍት ለማፋጠን ተቻኮሉ፡፡
ናይጄሪያዊው ደራሲና ብዕርተኛ ኬን ሳሮዊዋ በወቅቱ ሰለ አምባገነኖቹ ወታደራዊ መሪዎች እርምጃ እንዲህ ነበር ያለው፡- ‹‹እነዚህ ሰዎች ነፍሰ ገዳዮች ሆነው ሳሉ እኔን በከንቱ ለመወንጀል ይጥራሉ፤ በበኩሌ የመሠረቱብኝን ክስ እንኳን ለመስማት አልፈልግም፡፡ ችሎቱ በሚካሄድበት ወቅት ማለፊያ የሆነውን መጽሐፌን አንስቼ አነባለኹ፡፡ እነዚህ ሰው በላ ጭራቆች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ ፍትሕንና እውነትን የተጠየፉ አምባገነኖች፣ በሚያዩት ሁኔታ እርካታ አግኝተው እንዲፈነጥዙ ዕድል አልሰጣቸውም፡፡››
ጀሽዋ ሐመር የተባለ ጋዜጠኛ ኬን ሳሮዊዋ ያለአግባብ ተወንጅሎ ወኅኒ ከተጣለ በኋላ አግኝቶ ለማነጋገር ብዙ ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ የናይጄሪያ ፖሊሶች ጋዜጠኛውን አታክተውና አሰላችተው ለመሸኘት ያደረጉት ጥረት ግን በሰውዬው አይበገሬነትና ብሎም በሳሮዊዋ ጠባቂ ትብብር ከሸፈና በስተመጨረሻ ሊያገኘው ቻለ፡፡ ጋዜጠኛው ጀሽዋ ሳሮዊዋን ባገኘው ጊዜ ብረት ባነገቱ ወታደሮች ተከቦ ነበር፡፡
ሳሮዊዋ አልጋው ላይ ጋደም ብሎ ፒፓውን እያጨሰ ነበር፡፡ እንዳየኝ ይላል ጋዜጠኛ ጀሽዋ እንዳየኝ ተነሣና ጨበጠኝና ለመሆኑ ከቀናት በፊት የላኩልህ ደብዳቤዬ ደረሰኽ ሲልም ጠየቀኝ፡፡ እኔም ደብዳቤው እንደደረሰኝ አንገቴን በማወዛወዝ ገለጽኩለት፡፡ አብረን በቆየንበት ጊዜ ሳሮዊዋ የአገሩ አምባገነን መንግሥት መሪዎች ፍርደ ገምድሎች፣ ጨካኞችና የሰው ደም የጠማቸው ሆነው ሳለ በከንቱ ሲወነጅሉት የቱን ያህል ልቡ እንደተጸየፋቸው አጫወተኝ፡፡ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ኬን በሠራው ሥራ ሁሉ ፍፁም ጸጸት እንደሌለበትና የአሸናፊነት ስሜት እንደሚሰማውም ነገረኝ፡፡
በዚህ ጨዋታችን መካከልም የእስረኞቹ መኪና መጣ፡፡ ሳሮዊዋ መኪናው ላይ ከሚጫኑት ዋንኛውና አንዱ ተረሻኝ ነበር፡፡ መኪናው ላይ ከወጣ በኋላ የተለየኝ በአውራ ጣቱ አሸናፊነት/የድል ምልክት እያሳኝ በፈገግታ እንደታጀበ ነበር ይላል ጋዜጠኛው ጆሽዋ፡፡ ኬን ሳሮዊዋ በሕይወቱ ጀምበር ማዘቅዘቂያ የመጨረሻ ሰዓት ላይ ጋዜጠኛው ወዳጁን በዚህ መልኩ ከተለየው በኋላ ሳሮዊዋና ሁለት ሌሎች እስረኞች ጥብቅ በሆነ የጥበቃ አጀብ ወደሚሰቀሉበት ፖርት ሐርኮት እስር ቤት ተወሰዱ፡፡
ከመገደያቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ንስሐ ይቀበሉ ዘንድ አንድ እንግሊዛዊ ካህን ወደ ወኅኒ ቤቱ መጡ፡፡ በስፍራው የነበረ አንድ የዓይን ምስክር እንደገለጸው ሁለቱ እስረኞች ያለ ቅጥ እየተንሰቀሰቁ ሲያለቅሱ ሳሮዊዋ ተመልክቶ ጠጋ በማለት ለእናት ምድራቸው ናይጄሪያና ናይጄሪያውያን መሥዋዕት በመሆናቸው ሊኮሩ እንደሚገባቸው በመንገር በድፍረት የሞትን ጽዋ ይጠጡ ዘንድ ነበር ያበረታታቸው፡፡
የሞት ፍርዳቸው በሚጸናበት ረፋድ ጠዋት ላይ ኬን ሳሮዊዋ አዘውትሮ ከከንፈሩ የማይነጥላትን ፒፓውን ለአባቱ እንዲሰጡለት ገዳዮቹን ተማጸነ፡፡ ጥያቄውን የተቀበለው ሰው ግን አልነበረም፡፡ ወዲያው የአምባገነኖቹ ቅጥረኛ የሆኑት ወታደሮች የእስረኞችን ዓይን በጥቁር ጨረቅ ሸፍነው ወደ መስቀያው ስፈራ እያጣደፉ ወሰዷቸው፡፡ ኬን ሳሮዊዋ የመጀመሪያው ተሰቃይ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በሚገርም ሁኔታ በኬን ሳሮዊዋ አንገት ውስጥ የተጠለቀው ገመድ ለአራት ጊዜያት ያህልም ቢበጠስም በአምስተኛው ግን እነዛ ጨካኞችና እብሪተኞች ሕይወቱን በስቅላት ከነፍሱ ነጠሏት፡፡
ግዑዙ ገመድ እንኳን እምቢ ለፍትሕ፣ እምቢ ለእውነት ብሎ በኬን ጎን በቆመበት፣ በመሰከረበትና ባመጸበት በዛች ቅጽበት አምባገነኖቹ ልባቸውም ሆነ ዓይናቸው ታውሮ ይኼን እውነት ለመገንዘብ ሕሊናቸውም አእምሮቸውም ጨለመባቸዋልና ሊምሩት አልወደዱም፡፡ ወታደሮቹ ለጊዜውም ቢሆን ከዚህ እኩይ ድርጊታቸው፣ በክፉው፣ ሸካራና ጠማማ ጎዳና ላይ ከመገሥገሥ የሚያግዳቸው ምንም ምድራዊ ኃይል እንደሌለ ነበር ለናይጄሪያ ሕዝብና ለመላው ዓለም ለማሳየት የሞከሩት፡፡
ታጋይ፣ ደራሲ፣ ጸሐፊ … የሆነው ኬን ሳሮዊዋ በናይጄሪያ ደቡብ ምስራቅ ጠረፍ በኒጀር ወንዝ ዳርቻ የሚኖር የኢጎኒ ብሔር ተወላጅ ነበር፡፡ በ54 ዓመት ዕድሜው በግፍ በገመድ ተንጠልጥሎ ለሕልፈት የበቃው ሳሮዊዋ በተለያዩት ጊዜያት በጋዜጦች ላይ ባቀረባቸው መጣጥፎች፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ የሰላ ትችቶቹ፣ በቴሌቪዥን ዝግጅቶቹና ዘገባዎቹ በድፍን ናይጄሪያ ከፍተኛ ተወዳጅነትንና ዝናን ለማትረፍ የቻለ ስመ ገናና ጸሐፊና ገጣሚ ነበር፡፡
‹‹ሶልጀር ቦይ›› የተሰኘ ወጥ የፈጠራ ሥራው ከአገሩ አልፎ ከበሬታን ያተረፈለትና ተነባቢ ሥራው ለመሆን በቅቶለታልም፡፡ ሳሮዊዋ በኑሮው የተደላደለ ቱጃር ለመሰኘት የሚችል፣ የግሉ የሆነ ፕሬስ መሥርቶ በመንቀሳቀስ ላይ የነበረና ይህ ጎደለው የማይባል ሰው የሚባል ዓይነት ቢሆንም እንኳን ናይጄሪያና ናይጄሪያውያን ዕጣ ፈንታ በአምባገነኖቹና በጨካኙ ወታደራዊ ኃይሎች እጅ መውደቁ እረፍት ስለነሣው አምባገነኖችን በብዕሩ አምርሮ ለመዋጋት ተነሣ ጀግና የብዕር ሰው ነበር፡፡
ታጋዩና ደራሲው ኬን ከትውልድ ቀዬው በገፍ የሚቀዳው ጥቁር ወርቅ (የነዳጅ ዘይት) የናይጄሪያ 90 በመቶ የገቢ ምንጭ ከመሆኑም በላይ ለሙስናና ለምዝበራ ለተዘፈቁት ወታደራዊ ገዢዎች መንደላቀቂያነት ሲውል ታዝቧል፡፡ ሕዝቡ ይህ ነው በማይባል ድህነትና ጉስቁልና ውስጥ ተዘፍቀው አምባገነኖቹ እንዲህ መቀማጠላቸው የሕሊና እረፍት የነሣው ሳሮዊዋ ይህን ግፍ ለመበቀል ነበር ብዕሩን በድፍረት ያነሣው፡፡ በዚህም አምባገነኖቹንና ሙሰኞቹን ናይጄሪያውያንን ክፉኛ ነበር ያሰጨነቃቸው፡፡
ደራሲና ታጋይ ኬን ሳሮዊዋ ሙያውን አክባሪና በሙያው ተደሳች እንደነበር ለእንግሊዛዊው ደራሲ ዊሊያም ማድዬ በጻፈው ደብዳቤ እንዲህ በማለት ነበር ማንነቱንና ሥራውን የገለጸው፡-
በእጅጉ የማከብረውንና የምወደውን የኢጎኒ ሕዝብ እነዚያ አበሳውንና ፍዳውን በሚያስቆጥሩት ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎችን እንዲጋፈጣቸው ለማድረግ የሥነ ጽሑፍ ስጦታዬን እንደ ታላቅ መሳሪያ ለመጠቀም በመቻሌ በሕይወቴ ውስጥ ትልቁ ነገር ሆኖ ይመዘገባል፡፡ ብዕሬን ለወገኖቼ አርነት ማዋሌን ያህል ሚያስደስተኝ ነገር የለም፡፡ ለወገኔ የእኔ ድምፅ፣ የእኔ ጩኸት በጣሙን ወሳኝና አስፈላጊ ነበር፡፡
በእጅጉ የሚደንቅ ነው!! ፖለቲከኛ ሆኜ እንዲህ ያለ ነገር ማድረግ አልቻልኩም፣ በንግዱ ዓለም ተሰማርቼ በነበር ወቅትም አልሳካልኝ ያለ ነገር ነበር፡፡ ብዕር አንስቼ ከወረቀት ጋር ማዋኻድ ስጀምር ግን ከባዱ ነገር ቀላል ሆነ፡፡ አልሳካ፣ ድምፁም አልሰማ ያለው ነፃነትና የፍትሕ ድምፅም ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ በምድሬ በናይጄሪያ ተሰምቶ አምባገነኖቹንና እብሪተኞችን መግቢያና መውጫ አሳጣቸው፣ እረፍትም ነሣቸው፡፡
ብዕር …፣ ብዕር …፣ የብዕር ኃይል ምንጊዜም ያሸንፋል፡፡ ለእኔ ከዚህ በላይ ደስታ የለም፡፡ በዚህ ወቅት የፈለገው ነገር ቢመጣም በቆራጥነት ለመጋፈጥ ተዘጋጅቼያለኹ፡፡ እንደሚመስለኝ በዚህ ሰዓት ታላቅ የሆነ የሞራል ድል የተጎናጸፍኩት እኔ ነኝ፡፡ በጠላትነት የተነሡብኝ አምባገነኖች፣ ጠላቶቼ ከዘላለማዊ እፍረትና ጸጸት ከማያመልጡበት የሲኦል ቅርቃር ውስጥ እንደገቡ ሆነው ነው የሚሰማኝ፡፡ ነበር ያለው ያ ጀግና የብዕር ሰው!!
በእያንዳንዱ ናይጄሪያዊ ሕዝብ፣ የአርነት ታጋዮችና በዓለም ሕዝቦች ሁሉ ዘንድ ብሎም የኪነ ጥበብ ወዳጆችና አፍቃሪዎች ልብ ውስጥ ኬን ሳሮዊዋ ዛሬም ነገም ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ አባቻና መሰል አምባገነኖች ግን በአረመኔያዊ ግብራቸው ታሪክ በትዝብት ሲያስታውሳቸው ይኖራሉ፡፡
በመጨረሻም በአገራችን ታላቅ የሆነ ብዕራዊ ተጋድሎ ያደረጉትን እነ ጸጋዬ ገ/መድኅንን፣ እነ አቤ ጉበኛን፣ እነ በዓሉ ግርማን አርአያ አድርገው ዛሬም ስለ እውነት፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ነፃነት … በጨዋ፣ በታረመና ባላመነዘረ ብዕራቸው ተጋድሎ እያደረጉ ላሉ ኢትዮጵውያን ሁሉ ያለኝን አድናቆትና ክብር ለመግለጽ እወዳለኹ፡፡
በአቤ ጉበኛና በበዓሉ ግርማ መንፈስ፣ ሌሎችም በዚህ ዘመን የእነርሱን ብዕር ቁርጠኝነትና ወኔ የተቀላቀሉ ኃያላንና ጀግኖች ብዕረኞች ለተገፉ ወገኖቻቸው፣ ለሰው ልጆች መብት፣ ለፍትሕና ለእውነት በመቆም በተባ ብዕራቸው ላደረጉትና እያደረጉት ላለው ታላቅ ተጋድሎ ሊዘከሩ የሚገባቸው የምን ጊዜም የኢትዮጵያ የብዕር ጀግኖቻችን ናቸውና ልናከብራቸው፣ ልንዘክራቸው ይገባናል ለማለት እወዳለኹ፡፡
ሰላም! ሻሎም!

Previous Story

ለቅጥረኛ ወያኔ ትግሬዎችና ሆድ አደር ተባባሪዎች

Next Story

የኢሕአግ ሰራዊት በዋልድባ ወታደራዊ ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop