የሲድኒ ኢትዮጵያዊያን የተሳካ የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ ( ከአቢይ አፈወርቅ )

አዲሱ አምባሳደር ሀፍረት ገጠማቸው

በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አረጋ ሀይሉ ትላንት (ቅዳሜ ፌብሯሪ 22 ቀን) የሲድኒ ነዋሪ ኢትዮጵያዊያንን በልማት ዙሪያ ለማነጋገር የያዙት ፕሮግራም በአሳፋሪ ሁኔታ ተደመደመ።
ይህ በሜሪላንድ ሲቲ ካውንስል የተካሄደው ስብሰባ አምባሳደሩንና የስብሰባውን አስተባባሪዎች ጨምሮ በድምሩ 20 ሰዎች እንኳ ያልተገኙበት ሲሆን በርካታ ቁርጠኛ ኢትዮጵያዊያን ግን ለሰዓታት በአዳራሹ በር ላይ ቆመው ደማቅ የተቃውሞ ድምጽ ሲያሰሙ ውለዋል። ቪዲዮ ክሊፑን ለመመልከት
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲያስፖራውን ለመከፋፈል ከዓመታት በፊት ያወጣውና በሲድኒም የአገዛዙ ወኪሎች ለረጅም ጊዜ የደከሙበት ዕቅድ ‹ውጤት አስገኝቷል› በሚል ያለአግባብ የተመኩት አምባሳደር አረጋ መላው የሲድኒ ነዋሪ እንዲገኝላቸው መወትወት የጀመሩት ከ2 ሳምንታት አስቀድሞ ነበር። ይሁንና የወገኖቻቸው ሰቆቃ እንደ የእግር እሳት የሚያንገበግባቸው የሲድኒ ነዋሪ ኢትዮጵያዊያን ግን ሳምንቱን ሙሉ ‹የስብሰባው አጀንዳ የዲሞክራሲ መታፈንና የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ መሆን ይገባዋል› በሚል እርስ በርስ በስልክ የጸሁፍ መልዕክቶችና በሶሺያል ሚዲያዎች ኃሳብ ሲለዋወጡ ነበር የቆዩት። በዚህም የነዋሪው የቁጣ ልክ ከፍተኛ መሆኑ ድንጋጤ ውስጥ የከተታቸው አምባሳደር አረጋ ከስብሰባው አንድ ቀን አስቀድመው ለፖሊስ በመደወል ሀሳባቸውን መቀየራቸውንና በግል አዘጋጆቹ ከሚመርጧቸው ሰዎች በቀር ማንም ወደ አዳራሹ እንዳይገባባቸው ለመጠየቅ ተገደዋል።

ገና በመጀመሪያ ጉዟቸው በፈጸሙት የስሌት ስህተት ለሀፍረት የተዳረጉት አዲሱ አምባሳደር በይፋ የጋበዟቸውን ሰዎች ለማየት እንኳን ባለመድፈራቸው ከስብሰባው አንድ ሰዓት ዘግይተው ወደአዳራሹ በጓሮ በር ገብተዋል። ሰልፈኛውም በሳቅና በወረፋ ተሳልቆባቸዋል።
በስሜት ንዳድ የጋሉት ኢትዮጵያዊያን ከአዳራሹ በር ላይ ቆመው በከፍተኛ ድምጽ መፈክሮችና አገራዊ መዝሙሮችን ያሰሙ ነበር። ባኳያው ደግሞ እየተንጠባጠቡ ወደ ስብሰባው በማምራት ላይ ከነበሩ አናሳ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎች መሀል አንዳንዶቹ የተቃውሞውን ጥንካሬ በመመልከት ከቅርብ ርቀት ፊታቸውን እያዞሩ ሲመለሱ ታይተዋል።
የአገዛዙ ወኪሎች ‹ለተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ይሸነፋሉ› በሚል የገመቷቸውን ኢትዮጵያዊያን በማባበልና በመደለል ለረጅም ጊዚያት የደከሙበት ይህ ዝግጅት፤ ነባር የህወሀት ደጋፊዎችን፣ አምባሳደሩንና የዝግጅቱን አስተናባሪዎች ጨምሮ 20 የሚሞሉ ሰዎችን እንኳ ማሰባሰብ ያለመቻሉ ለኤምባሲው ሀፍረትን፣ ለተቃዋሚዎች ደግሞ እርካታን ሊያጎናጽፍ በቅቷል።
በሚያስተዛዝብ ደረጃ አብዛኞቹ ታዳሚዎች ከተመሳሳይ ብሄር የፈለቁ ቢሆኑም ተቃዋሚዎቹ ግን እየደጋገሙ “እናንተ የትግራይን ብሄር አትወክሉም!” “የትግራይ ተወላጅ ወገኖቻችን የአገር ፍቅርን የሚያውቁ ኩሩዎች ናቸው። እናንተ ግን ሆዳሞች ናችሁ።” ሲሏቸው ተደምጠዋል። አስገራሚ የአቋም ለውጥ አድርጋ ‹ዓይንሽ ለዓፈር› የተባለችውን አርቲስት አይናለም ተስፋዬን ጨምሮ አራት ያህል የሌላ ብሄር ተወላጆችም ወደ አዳራሹ ሲገቡ ታይተዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ‹‹የትህነግ አባላት እንኳ ኢትዮጵያዊነትን በትግራይዋን መካከል እንኳን ልዩነቶችን የሚፈጥሩ ጠባቦች ናቸው - ለትህነግ ተመራጩ ዜጋ የአድዋ

ከስብሰባው ታዳሚዎች በቁጥር ከአራት እጥፍ በላይ የሚልቀውና አንገቱን ቀና አድርጎ በከፍተኛ የስሜት ንዳድ ድምጹን ሲያሰማ የቆየው ተቃዋሚ ከያዛቸው መፈክሮች መሀል ፦”ያለ ዲሞክራሲ ልማት የለም” “የጸረ ሽብር አዋጁ ሽብር ማራመጃ ነው።” “የመሬት መቀራመቱ ይቁም!” “በኢህአዲግ ፖሊሲ ሙሰኞች እንጂ አገር አይለማም” የሚሉና ሌሎችም ይገኙበታል። በግፍ እስር ላይ የሚገኙት ንጹሀን የህዝብ ልጆች እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋም በጋለ ስሜት ሲጠቀሱ ውለዋል።
ባስመዘገቡት ውጤት እርካታ የተሰማቸው የአገዛዙ ተቃዋሚ ኢትዮጵያዊያን የዕለቱን ተልዕኳቸውን አጠናቀው ወደ የቤታቸው ከመመላሳቸው በፊት በአገራቸው ጉዳይ ከመቼውም በላይ የተጠናከረ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባቸው ተወያይተዋል። መልካም ትብብርና ወንድማዊ ስሜት ያልተለያቸው የአውስትራሊያ ፖሊሶችም ልባዊ ምስጋና የቀረበላቸው ሲሆን እነሱም በአጸፋው ሰልፈኛው ሰልፉን በፍጹም ጨዋነት በማካሄዱ ምስጋና አቅርበውለታል። ይህን የተሳካ የተቃውሞ ሰልፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚያኮራ ቅንጅት ያስተናበሩት የሰልፉ አዘጋጆችም ተገቢው አክብሮት ተችሯቸዋል።
ኤንባሲው የበተነውን የጥሪ ደብዳቤ ከታች ይመልከቱ!

Share