ዘ-ሐበሻ እና የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ በሚኒሶታ በሳዑዲ ለተጎዱ ወገኖች ያሰባሰቡት ገንዘብ ለIOM ተሰጠ

(ዘ-ሐበሻ) ሳዑዲ አረቢያ ሕገወጥ ያለቻቸውን ዜጎችን ከሃገሯ እንዲወጡ ማዘዟን ተከትሎ የሳዑዲ ፖሊሶች በፈጸሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በመበሳጨትና የተገደሉትንም ለማሰብ በሚኒሶታ ዘ-ሐበሻ እና የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ በመተባበር ባዘጋጁት የሻማ ማብራት ምሽት ላይ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮአሜሪካውያን ያዋጡት ገንዘብ ለዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ተሰጠ።

በኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ በኩል የተላከውን ይኬንኑ ቼክ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ተወካዮች መረከባቸውን የሚገልጽ ደብዳቤም ልከዋል።

እሁድ ኖቬምበር 17/2014 ብሎሚንግተን በሚገኘው ራዲሰን ሆቴል በተደረገው የሻማ ማብራት ሥነሥርዓት ላይ $3,050.00 ዶላር (60 ሺህ 390 ብር) የተሰበሰበ ሲሆን ይህኑኑ ገንዘብ በኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ ገንዘብ ያዥ አቶ አንተነህ ተፈራ በኩል በተጻፈ ቼክ ለ IOM እንዲላክ ተደርጓል።
ፌብሩዋሪ 11 ቀን 2014 ከIOM ፕሬዚዳንት ሉካ ዳል ኦሊጎ በተፃፈ ደብዳቤም ገንዘቡን መረከባቸውን የሚገልጽ ለኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ ተልኳል።
ፕሬዚዳንት ሉካ በደብዳቤያቸው ተቋማቸው እስካሁን ድረስ ከሳዑዲ የተመለሱ ከ160 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን እየረዳ እንደሚገኝ አስታውቀው በሚኒሶታ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ይህን ጥረት ለመደገፍ ያሳየው ትብብር የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ በሚኒሶታ የራሱን ህንጻ ለመግዛት የሚያደርገውን ጥረት በመቀጠል 2ኛውን የገቢ ማሰባሰብ ዝግጅት ማርች 29/2014 እንደሚያካሄድ አስታወቀ። በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት የሚኒሶታ ታዋቂ ዲጄዎች እና አርቲስቶች እንደሚሳተፉ አቶ መስፍን ነጊያ ለዘ-ሐበሻ አስታውቀዋል።
ከዚህ ቀደም ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ቃል ከተገባው 50 ሺህ ዶላር ውስጥ ግማሽ ያህሉ ገቢ መደረጉን የገለጹት አቶ መስፍን ቃል የገቡ ሰዎች ክፍያውን በፍጥነት እንዲፈጽሙ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ አባላት ቁጥር በአንድ ዓመት ውስት ከ11 ወደ 300 በላይ ማደጉን የጠቆሙት አቶ መስፍን እየሠራን ያለው ሥራ ብዙዎቹን እያስደሰተ መሆኑን ከምንሰማቸው አስተያየቶች እንረዳለን ብለዋል።
ኮምዪኒቲው እንደተለመወደ ዘንድሮም የአድዋ ድል በዓልን በተከራየው የቢሮው አዳራሽ ውስጥ ማርች 1/2014 እንደሚያከበር አስታውቆ ሁሉም የአድዋ ድል ታሪክ ኮሪዎች በስፍራው እንዲገኙ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ማርች 1 በሚከበረው የአድዋ ድል በዓል ላይ ጥናታዊ ፊልሞች፣ የኢትዮጵያ ህፃናት የሙዚቃና የውዝዋዜ ሥራዎች፣ ግብዣ በተደረገላቸው እንግዶች ውይይት እንደሚደረግና ዝግጅቱን ከሰዓት በኋላ ከ2 ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ አቶ መስፍን ጨምረው ለዘ-ሐበሻ ገልጸዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቁማሯን እንዴት ሊበሏት እንዳሰቡ እንመልከት - አራጋው ሲሳይ
Share