Sport: 4-1-3-1-1 ወይም 3-2-3-2 ወይም 3-3-3-1 1-1-3-1-1 ወይም 1-4-3-2 የማንችስተር ዩናይትድ ታክቲካዊ አማራጮች

ከቀደሙት ዓመታት የማንችስተር ዩናይትድ ባህርይ በተቃራኒ በውድድር ዘመኑ ለሁለተኛ ጊዜ በካርዲፍ ሲቲው ጨዋታ በጭማሪ ደቂቃዎች ጎል ተቆጥሮባቸው ነጥብ መጣላቸው ይበልጥ ደጋፊዎችን ግራ አጋብቷቸዋል፡፡ በእርግጥ ለካርዲፍ ሁለተኛ ጎል ተወቃሹ ፓትሪክ ኤቭራ ነው፡፡ ፈረንሳዊው ፉልባክ የጎል አስቆጣሪውን እንቅስቃሴ በንቃት ከመከታተል ቸል ማለቱ ቡድኑን ሁለት ነጥብ አስከፍሏል፡፡ ይሁን እንጂ እውነተኛው ችግር ከዚህም ይልቅ ስር የሰደደ ነው፡፡
ማንችስተር ዩናይትድ በሰር አሌክስ ፈርጉሰንም ጊዜ ቢሆን የስኬቱ ቁልፍ በትንንሽ ክለቦች ነጥብ አለማባከኑ ነበር፡፡ ክለቡ ከትልልቆቹ ተፎካካሪዎቹ ጋር ሲገናኝ መልካም ውጤት ባላስመዘገበባቸው ዓመታትም ቢሆን በተደጋጋሚ ሻምፒዮን ሲሆን ታይቷል፡፡ በተለይ እንደ ካርዲፍ ያሉትን ቡድኖች ለመርታት በቀላሉ የክንፍ ጨዋታው ይጠቀም ነበር፡፡

የቡድኑ የአሁን ችግር ፖል ስኮልስ እና ማይክል ካሪክ ሜዳ ላይ ሲኖሩ ብዙም የሚስተዋል አልነበረም፡፡ ሁለቱ እንግሊዛዊያን በመሀል ሜዳው ወደ ኋላ አፍግፈው የጨዋታውን ሂደት መቆጣጠር እንዲሁም ተፅዕኖ መፍጠር ይችላሉ፡፡ ስኮልስ ባለፈው ክረምት ለሁለተኛ ጊዜ ጫማውን ከሰቀለ እና ካሪክ ደግሞ በቅርቡ ጉዳት ካስተናገደ ወዲህ ግን ዩናይትድ መከራውን እያየ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በይበልጥ በዌልስ ክለብ አጨዋወት ተጋልጧል፡፡
የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኖቹ ጨዋታውን በ4-2-3-1 ፎርሜሽን በጀመረበት የካርዲፍ ግጥሚያ ቡድኑ ሮቢን ቫን ፔርሲን ሳይሆን ሀቪዬር ሄርናንዴዝን ከፊት ማሰለፉ የቡድኑን ውህደት ረብሾታል፡፡ ለወትሮውም በመሀል ክፍል ችግር የነበረበት ዩናይትድ በካርዲፍ የፕሬሲንግ አጨዋወት ውጥረት ውስጥ ገብቶ በተደጋጋሚ ኳስ እየተነጠቀ ተጨዋቾቹም ለመከላከል ሲሯሯጡ ተስተውለዋል፡፡ በዚህም ግጥሚያ የዩናይትድ ትለቅ ችግር በውድድር ዘመኑ ሙሉ እንደታየው በመሀል ክፍል መበለጡ ነው፡፡ ቡድኑ ጠንከር ያለ እና በዳይመንድ ፎርም ቅርፅ አማካይ ክፍል በሚቀርቡ ተጋጣሚዎች ይበልጥ ችግሩ ተጋልጦ ይወጣል፡፡ ይህንን ለማስተዋል በቂ ጊዜ ያገኙት ሞዬስ አሁን ያሏቸውን ተጨዋቾች እና የሚከተሉትን አጨዋወት ለማጣጣም መነሳት ያለባቸው ይመስላል፡፡
ሞዬስ በመሀል ክፍል ማርዋን ፌላይኒን ከመጨመራቸው በስተቀር በመልበሻ ክፍል የሚያገኛቸው ተጨዋቾች በፈርጉሰን ጊዜ የነበሩት ናቸው፡፡ የአሁኑ ቡድን በኳስ ቁጥጥር ረገድ መታማቱ አያስገርምም፡፡ የፈርጉሰንም ቡድን ኳስን ለረጅም ጊዜ ይዞ ማቆየት አይችልም ነበር፡፡ የአሁኑ ቡድን ግን የመጨረሻ ኳሶችን ለአጥቂዎች ለማቅረብ እና ለመጨረስ ብዙ ሲቸገር እየታየ ነው፡፡ ሞዬስ ይህንን ችግር እንዴት ሊቀርፉ ይችላሉ? መፍትሄው በሚጠቀሙት የፎርሜሽን አይነት ላይ የተመሰረተ ይመስላል፡፡

4-1-3-1-1
ይህ ፎርሜሽን ከዳይመነድ ፎርሜሽን ጋር ይመሳሰላል፡፡ የአራቱ ተከላካዮች ሚና ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች ሲሆኑ በግራ እና በቀኝ የማጥቃትን ስራ ደርበው የሚሰሩ ፉልባኮች ይኖራሉ፡፡ ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች በመሀል ክፍል ጥንቃቄ የተሞላበት የመከላከል ጨዋታቸውን ሲቀጥሉ የመስመር ተከላካዮቹ ደግሞ ከክንፍ ተጨዋቾቹ ጋር እየተናበቡ ወደፊት ይሮጣሉ፡፡ የአጨዋወቱ ትልቅ ጥቅም ለተጨዋቾቹ Man Marking (ሰው በሰው የመቆጣጠር) እና Zonal Marking (ቀጠናን እየጠበቁ የመጫወት) እድል መፍጠሩ ነው፡፡ ይህንን ደግሞ በአርሰናሉ ጨዋታ ዩናይትዶች በጥሩ ሁኔታ ሲተገብሩት አይተናል፡፡
ማንችስተር ዩናይትድ የአርሰን ቬንገርን ቡድን ጨዋታ አበላሽቶ 1-0 ሲያሸንፍ በመሀል ሜዳ ሳንቲ ካዞርላ እና ሜሱት ኦዚልን ከጥቅም ውጪ ማድረግ ነበረበት፡፡ በዕለቱ በቀኝ ክንፍ የተሰለፈው አንቶኒዮ ቫሌንሺያ ለማጥቃት ከክሪስ ስሞሊንግ ጋር ቦታ እየተለዋወጠ ተጫውቷል፡፡ ይሁን እንጂ በዚያ ግጥሚያ ከዩናይትድ ተጨዋቾች እንቅስቃሴ ቀልብ የሚስበው ያለ ኳስ የሚያሳየው የቦታ አያያዝ ነበር፡፡ አርሰናል ኳስ ሲይዝ እና ሲያጠቃ ቫሌንሺያ ሌላ ነገሩን ሁሉ ትቶ ኦዚል፣ ካዞርላ እና ሚኬል አሮቱታን እየተጠጋ ያስጨንቃቸው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ በተደጋጋሚ የአርሰናሎች አማካዮች ኳስ ወደ ኋላ ለማቀበል ይገደዱ ነበር፡፡
በቀኝ መስመር ሲያጠቃ የነበረው ስሞሊንግ እና የተከላካይ አማካይ ሚና የነበረው ፊል ጆንስ አርሰናል ኳስ ሲነጥቅ ወደ ቦታቸው ለመመለስ በቂ ጊዜ እንዲያገኙ የቫሌንሺያ ስራ ወሳኝ ነበር፡፡ ጆንስ እና ተከላካዮቹ በትክክለኛ ቦታቸው ላይ መገኘታቸውን ሲያረጋግጥ ብቻ ኢኳዶራዊው ወደ ቀኝ ክፍል ቦታ ተመልሶ ጓደኞቹ ኳስ ነጥቀው የመልሶ ማጥቃት ጨዋታው እስኪጀመር ራሱን ያዘጋጃል፡፡ የቫሌንሺያ ተጨማሪ ሚና አርሰናል የተለመደውን ጠንካራ የመልሶ ማጥቃቱን እና ፈጣን ቅብብሉን እንዳይተገብር አግዶታል፡፡
በመሀል ሜዳ የተከላካይ አማካይ ስራ የተከላካይ ክፍሉን ከአማካዩ እና ብሎም ከአጥቂ መስመር ጋር የማገናኘት ኃላፊነት ይጨምራል፡፡ ካሪክ ለዚህ ቦታ ምርጥ ነው፡፡ እንግሊዛዊው ረጃጅም ኳሶችን በማቀበል እና በማከፋፈል ጎበዝ ሲሆን ብዙ ጊዜም ኳስ አይነጠቅም፡፡ የአሁን የቡድኑ ችግርም ይኸው ነው፡፡ ዩናይትድ የካሪክ ተተኪ የለውም፡፡
ከተከላካይ አማካዩ ፊት ለፊት ሶት ሜድፊልደሮች ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህ ተጨዋቾች ውስጥ ሁለቱ የክፍን ተጨዋቾች ሲሆኑ አንደኛው በመሀል የሚጫወት ነው፡፡ በቀኝ ክፍል ሚና ሉዊስ ናኒ እና ቫሌንሺያ ቢፈራረቁበትም ላቲን አሜሪካዊው ልጅ በመከላከል አጨዋወቱ ጥንካሬ ቅድሚያውን እያገኘ ነው፡፡ በግራ በኩል አድናን ያኑዛይ ቦታውን በአስተማማኝ መልኩ ቢሸፍንም እድሜው እያንዳንዱ ጨዋታ እንዲጫወት የሚያስችለው አይደለም፡፡ ሌላኛው የቦታው አማራጭ ሺንጂ ካጋዋ ተፈጥሯዊ የቦታው ተጨዋች ባለመሆኑ አንዳንድ ጊዜ ጥሩ ሌላ ጊዜ መጥፎ ብቃት እያሳየ ይሰለፍበታል፡፡
ጃፓናዊው በግራ ክፍል የሚያገኛቸውን ኳሶች ለመጠቀም ወደ መሀል ሜዳ ሰብሮ መግባት ያወትራል፡፡ አጋጣሚው ከተመቻቸለትም እስከ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ዘልቆ አደጋ ይፈጥራል፡፡ ሆኖም ብዙዎቹ የተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮች ይህንን አጫወቱን ስለሚያውቁ አስቀድመው ኳሷን በጉልበት ይነጥቁታል፡፡
እውነተኛ የግራ ክፍል ተጨዋች የሚያስብሉትን ባህሪዎች የያዘው አሽሊ ያንግ በተከታታይ የወረደ ብቃት ካሳየ እና ሁለት ጊዜ አስመስሎ የመውደቅ ከተወቀሰ በኋላ በሞዬስ እምነት አጥቷል፡፡ እንዲያውም በቅርቡ ክለቡን መልቀቁ እንደማይቀር ይገመታል፡፡ በክንፍ በኩል ሌላኛው ጥሩ አማራጭ ዳኒ ዌልቤክ ነው፡፡ እንግሊዛዊው የአጥቂ መስመር ተጨዋች ቢሆንም እድሉ ሲሰጠው በሚገባ አልተጠቀመበትም፡፡ በተለይ በጎል ማስቆጠር በኩል ያለበት የተጋነነ ድክመት ከግንዛቤ ሲገባ በሌሎቹ ጠንካራ ጎኖቹ የክንፍ ተጨዋች መሆን እንደሚችል መናገር ይቻላል፡፡ የዌልቤክ ፍጥነት የትኛውንም የተከላካይ ክፍል የመረበሽ አቅም አለው፡፡
ከአጥቂ በስተጀርባ ያለውን ቦታ ዌይኒ ሩኒ የራሱ አድርጎታል፡፡ እንግሊዛዊው በቦታው በተለይ ከሮቢን ቫን ፔርሲ ጋር የፈጠረው ጥምረት እና አይታው ድንቅ የሚባል ነው፡፡ የእንግሊዛዊው ታታሪነት እና ሁልጊዜም ኳስ ለመቀበል ራሱን ዝግጁ ማድረጉ ለቦታው የተመቸ አድርጎታል፡፡ ሆኖም ሞዬስ ዌይን ለጉዳት ከመዳረጉ ወይም ከመድከሙ በፊት እረፍት ሊሰጡት እንደሚገባ የሚመክሩ አልጠፉም፡፡ ሞዬስ ይህንን ቢያደርጉ ሁለት ጥቅም ያገኛሉ፡፡ አንደኛ ሩኒን በወሳኙ የውድድር ወቅት በሙሉ ብቃት ያገኙታል፡፡ በሌላ በኩል የእንግሊዛዊው ማረፍ ለጓጋዋ በተመራጭ ቦታው የመጫወት ዕድል ያስገኝለታል፡፡
በአጥቂ መስመር የቫን ፔርሲን ቦታ የሚቀናቀን የለም፡፡ ሆላንዳዊው ያለምንም ጥያቄ የማንችስተር ዩናይትድ ምርጡ አጥቂ ነው፡፡ ቺቻሪቶ ብዙ የመጫወት ዕድል ባያገኝም ቅር ሊሰኝ የሚገባ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ሜክሲኳዊው የአንድ አይነት አጨዋወት ምርጥ ጎል ጨራሽ ነው፡፡ በመከላከልም ሆነ የመሀል ክፍሉን በማንቃት የማይታወቀው ቺቻሪቶ ጎሎቹን ለማግባት የክንፍ ክሮሶችን የሚጠብቅ አይነት አጥቂ ነው፡፡ ስለዚህ በቋሚነት ከመጀመር ይልቅ ተቀይሮ ሲገባ ይበልጥ ውጤታማ ነው፡፡ ምናልባት ምርጥ ተቀያሪነቱን ተቀብሎ በሞዬስ ስር መቆየት እና የፈርጊ እና ኦሌጎናር ሶልሻዬርን ታሪክ መድገም ወይም ማንችስተር ዩናይትድን መሰናበት ይኖርበታል፡፡
3-2-3-2 ወይም 3-3-3-1
የእነዚህ ፎርሜሽኖች መሰረታዊ ልዩነት ቡድኑ በሁለት የመሀል ተከላካዮች ፈንታ ሶስት መጠቀም ከመቻሉ ጋር ይያያዛል፡፡ ከተጫዋቾች መኖር ወይም አለመኖር ጋር የሚያያዝ ከሆነ ዩናይትድ በቂ የመሀል ተከላካዮች አሉት፡፡ አምበሉ ኒማኒያ ቪዲች፣ ሪዮ ፈርንዲናንድ፣ ጆኒ ኢቫንስ፣ ፊል ጆንስ እና ክሪስ ስሞሊንግ ተፈጥሯዊ የመሀል ተከላካዮች ናቸው፡፡ ምናልባት ሶስት የመሀል ተከላካዮችን ለመጠቀም ቢፈልግ ዩናይትድ ከቪዲች እና ከሪዮ አንዱን፣ ኢቫንስን፣ ጆንስ እና ስሞሊንግን ወይም ከሁለት አንዳቸውን የማጣመር ዕድል አለው፡፡
ከእነዚህ ሶስት ተከላካዮች በጥቂቱ ወደ ፊት ተጠግተው የሚጫወቱ ሁለት ፉልባኮች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ፉልባኮች በማጥቃቱም በርትተው የሚሳተፉ እንዲሁም የመሀል ክፍሉን እና የተከላካይ መስመሩን ሽፋን እየሰጡ ድጋፍ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በሜዳ ላይ ቦታ አያያዛቸውም ከኋላቸው ላለው የመሀል ተከላካይ ወደ ፊት የመሄድ አማራጭ ለመፍጠር ወደ መስመር ይበልጥ ይጠጋሉ፡፡ በቀኝ መስመር ይህንን ሚና ለመውሰድ ቫሌንሲያም ሆነ ራፋኤል በሚገባ የተመቹ ናቸው፡፡ በግራ በኩልም ከኤቭራ ሌላ አሌክሳንደር በትነር እንዲሁም ፋቢዮ ይኖራሉ፡፡
በሆልዲንግ አማካይ ቦታ ካሪክ ቀዳሚ ተመራጩ ነው፡፡ ሆኖም ቀደም ሲል እንደጠቀሰው እንግሊዛዊው ለሚናው ሁነኛ ተተኪ የለውም፡፡ ምናልባት ሞዬስ ብቃቱ ብዙ የሚያሳማውን ፌላይኒ በቦታው እየሞከሩ ያሉት ቀስ በቀስ ለቦታው ጥሩ አማራች ወደ መሆን እንዲያድግላቸው አስበው ሊሆን ይችላል፡፡ ጆንስም በዚህ ሚና ሲጫወት የተጋጣሚን አጨዋወት በመስበር እና በቶሎ የማጥቃቱን ጨዋታ በማስጀመር ጥሩ የሚባል ፍንጭ አሳይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ጆንስ አሁንም ብዙ ልምድ ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡ ዩናይትድ የዚህን ሚና ኃላፊነት ጠቅልሎ ቢሰጠው ምናልባት ሌሎች ከልምድ ማነስ የሚመጡ ዋጋ አስከፋይ ጥፋቶችን ሊሰራ ይችላል፡፡
ከተለካካይ አማካዩ ፊት ለፊት የሚገኙትን ሶስት አማካዮች እንመልከት፡፡ ቡድኑ በአንድ የፊት አጥቂ ብቻ የሚጫወት ከሆነ ሩኒ ከጀርባው የመሀሉን ቦታ ይይዛል፡፡ ሆኖም ሞዬስ ፎርሜሽኑን ወደ 3-2-3-2 እንዲለወጥ ከፈለጉ ሩኒን ከቫን ፔርሲ ጋር በአጥቂነት ሚና ሊያጣምሩት ይችላሉ፡፡ አሰልጣኙ ይህንን አጨዋወት ከተገበሩ የለውጡ ዋነኛ ተጠቃሚ ካጋዋ ይሆናል፡፡ ጃፓናዊው ከሁለቱ አጥቂዎች በስተጀርባ ተፈጥሯዊ እና ተመራጭ ቦታውን ይይዛል፡፡
በክንፍ በኩል የቀኑን ቦታ ለቫሌንሲያ ወይም እንደወቅታዊ ብቃቱ ለናኒ መስጠት ያዋጣል፡፡ የግራ ክንፍ ሚናን ደግሞ ያኑዛይ ወይም ዌልቤክ በሚገባ ሊሸፍኑት ይችላሉ፡፡ ዌልፍሬድ ዛህ በተጠባባቂ ቡድን የሚያሳየው ብቃት የሞዬስን ቀልብ መግዛት ከቻለ እርሱም ጥሩ የቦታው አማራጭ ይሆናል፡፡ በአጥቂ መስመር ቀደም ሲል ከተነሳው ነጥብ የተለየ አይኖርም፡፡ ቀደም ሲል ከተነሳው ነጥብ የተለየ አይኖርም ቫን ፔርሲ ከኦልድ ትራፎርድ ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ በፈርጉሰን ስር በተለያዩ አጨዋወቶች እና ከተለያዩ ተጨዋቾች ጋር ተጣምሮ ውጤታማ መሆን እንደሚችል አሳይቷል፡፡ ስለዚህ በ3-2-3-2 ወይም በ3-3-3-1 ለብቻውም ይሁን ከሌላ አጥቂ ጋር ቢጣመር ውጤታማ መሆን አይሳነውም፡፡ በተለይ በ3-2-3-2 ከዌይን ጋር መጣመር ከቻለ ሞዬስ እግረ መንገዳቸውን እንግሊዛዊውን በተፈጥሯዊ ቦታው ደስተኛ ሆኖ እንዲጫወት ማድረግ ይችላሉ፡፡ ባለፉት ወራት በቀድሞው የልጅነት አሰልጣኙ ስር ደስተኛ ሆኖ ድንቅ ብቃት እያሳየ የሚገኘው አጥቂ የፊት መስመር ሚናው ከተሰጠው ምናልባትም እስካሁን መፍትሄ ያላገኘውን የኮንትራት ማራዘም ጥያቄውን መልስ ያበጅለታል፡፡
1-1-3-1-1 ወይም 1-4-3-2
ይህ ፎርሜሽን በተለይ ዩናይትድን በመሀል ለሚያጠቁ ተጋጣሚዎች አስቸጋሪ ያደርጉታል፡፡ ለምሳሌ እንደ ቶተንሃም ሆትስፐርስ እና ባርሴሎና ያሉ ብዙውን ጥቃታቸውን በመሀል ለሚፈፅሙ ቡድኖች አጨዋወቱ ፈታኝ ነው፡፡ በዚህ አጨዋወት ከተለመደው በተቃራኒ አንድ ተጨዋች በጠራጊነት ሚና ከአራቱ ተከላካዮች በስተጀርባ ወደኋላ አፈግፍጎ ይጫወታል፡፡ በማንችስተር ዩናይትድ ጆንስ በመከላከሉም ሆነ ወደ ፊት እየሮጠ የማጥቃቱ ጨዋታ በማገዝ በኩል ውጤታማ ነው፡፡ ሆኖም በ1-4-3-1 ፎርሜሽ የተጫዋቹ ቦታ ከበረኛው ዴቪድ ደ ሂያ ፊት እና ከአራቱ ተከላካዮቹ በስተጀርባ ይሆናል፡፡ ይህንን ሚና ከተለመደው የጠራጊነት (ከአራቱ ተከላካዮች ፊት ለፊት የሚተገበር ሚና) የሚለየው ተጨዋቹ ከዚያ ቦታ እየተነሳ ሲያጠቃና ኳስን ይዞ ወደ ፊት ሲሄድ በተወሰነ መጠን ከተከላካዮቹ ጥበቃ ማግኘቱ ነው፡፡
በዚህ የጠራጊነት ሚና የሚጫወተው ተጨዋች ቡድኑ ሲጠቃ ከዋነኞቹ ተከላካዮች ሊያመልጥ የሚችልን ኳስ በሜዳው ስፋት እየተሯሯጠ ከአደጋ ክልል መራቁን ያረጋግጣል፡፡ በመከላከሉ ሂደት ኳስ ሲያገኝ ደግሞ እንዲሁ በደመነፍስ አድራሻ የሌለው ኳስ ከመለጋት ይልቅ የማጥቃቱን ጨዋታ ይጀምራል፡፡ ይህንን ሚና ለመጫወት በዩናይትድ የቡድን ስብስብ ከጆንስ የተሻለ ተጨዋች ማግኘት ያስቸግራል፡፡ በጥቂቱም ለዚህ የቀረበ የሚመስለው እና በፍጥነቱም ረገድ የሚመሰገነው ስሞሊንግ የሚሆን አካላዊ ብርታቱም ሆነ ልምዱ ከጀንስ ጋር የሚነፃፀር አይደለም፡፡
ጆንስ ከተከላካዮች ኋላ መጫወት የማይጠይቀውን ሚና እንዲወስድ የሚያስችሉት ሁለት አሳማኝ ነጥቦች መመልከት እንችላለን፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ጆንስ ከኳስ ጋር ሳይሆኑ ሲቀር የሚተገበሩ ስራዎች ላይ ጎበዝ ነው፡፡ እንግሊዛዊው በኳስ ቴክኒኩ ጥሩ ለሚባል የቡድን ጓደኛው ጥበቃ በማድረግ እና ችግር ሲፈጠር ኳሱን ተቀብሎ ለሌሎች ጓደኞቹ በማድረስ ውጤታማ ነው፡፡ ይህንን በሜዳው ቁመት እየተሯሯጠ ለመስራትም በቂ አካላዊ ብርታት አለው፡፡
በሌላ በኩል የቀድሞው የብላክበርን ተጨዋች በተከላካይ መስመር መገኘቱን ለማሳየት የሚረዳው ጉልበት እና አካላዊ ግዝፈት ተላብሷል፡፡ ጉልበቱን ተጠቅሞ የትኛወንም የተጋጣሚ ቡድን ተጨዋች ኳስ መቀበል እና የባላጋራውን ቡድን ጥቃት የመስበር አቅም አለው፡፡ በተለመደው የተከላካይ አማካይ ሚና ሲጫወትም ኳስ ይዞ ወደ ዩናይትድ የአደጋ ክልል የሚጠጋን የትኛውንም ተጫዋች አሯሩጦ ከተቻለ መንጠቅ እና አለበለዚያም እየታገለ ሌሎቹ የቡድኑ ተከላካዮች ቦታቸውን ይዘው በተጠንቀቅ እንዲጠብቁ ጊዜ መስጠት እንደሚችል አስይቷል፡፡ በዚህ ፎርሜሽ የኋላ መስመሩ ልዩነት የለውም፡፡ የአራቱን ተከላካዮች ቦታ ሁለት የመሀል ተከላካዮች እና ሁለት ፉልባኮች ይሸፍኑታል፡ እነዚህን ሚናዎች ለመሸፈንም በየቦው ሞዬስ በቂ አማራጮች አሏቸው፡፡ ከፊት ለፊታቸው የሚኖሩትን የሶስት አማካዮች ቦታዎች ሁለት የክንፍ ተጨዋቾች እና አንድ የመሀል አማካይ ይይዙታል፡፡
የዚህ አጨዋት ትልቁ ፈተና የሚኖራቸው ግን በአራቱ ተከላካዮች እና በጠራጊው ተጨዋች መካከል ያለው መናበብ ላይ ነው፡፡ ጆንስ በዚያ ሚና ከተከላካዮቹ ጋር ሳይናበብ አንድ የተሳሳተ እርምጃ ከወሰደ የሚያመጣው ጉዳት ከተጋጣሚ ቡድን ተጨዋቾች እንደ አንዱ ሊያስቆጥረው ይችላል፡፡ በተለይ የተከላካይ መስመር ተጨዋቾች ባልተገባ አቋቋም ወይም ከጨዋታ ውጪ መረብ ውስጥ ሊያስገቡ ቢሞክሩ ሁኔታውን ጆንስ ካልተገነዘበ ውጤቱ የከፋ ይሆናል፡፡
ተመሳሳይ ችግር የሚፈጠርበት ሌላኛው ምክንያት አራቱ ተከላካዮች ከፊታቸው ካሉት የቡድኑ አማካዮች ጋር ያላቸው የቦታ ርቀት መስፋቱን ተመልክተው ለማጥበብ ወደ ፊት ሲጠጉ ነው፡፡ ተከላካዮቹ ይህንን ማድረጋቸው አሳማኝ እና ምክንያታዊ ነው፡፡ እነርሱ የአማካዮ እንቅስቃሴ እያዩ ወደ ፊት እና ወደ ኋላ ካልተንቀሳቀሱ በመሀል የሚፈጠረው ክፍተት ቡድኑ ኳሱን ብቻ ሳይሆን ሜዳውንም እንዳይቆጣጠር ያደርገዋል፡፡ በተጨማሪም በተከላካዮች እና አማካዮች መካከል የሚተው ሰፊ ክፍተት ተጋጣሚ ቡድን ረጃጅም ኳሶችን እየተጠቀመ ተጨዋቾቹ ያለተቀናቃኝ ቦታውን እንዲመሰርቱ ያደርጋል፡፡
ይሁን እንጂ ፎርሜሽኑ በትክክል ከተተገበረ ተጋጣሚ ቡድን ኳስን መስርቶ ወደ አደጋ ክልል በመጣ ቁጥር እንዲነጠቅ እንዲሁም ቀዳዳዎች ሲያጣ ኳስን ወደ ኋላ እየመለሰ በተደጋጋሚ ጨዋታውን ከኋላ እንዲጀምር ያስገድደዋል፡፡ ዩናይትድ የኳስ ቁጥጥር ሳይወስድ ተጋጣሚውን እረፍት መንሳት እና ባገነው አጋጣሚ አደጋ መጣል ያስችለዋል፡፡
ማንችስተር ዩናይትድ እና ሞዬስ በጃንዋሪ ሁነኛ የመሀል ክፍል ተጨዋቾችን የሚገዙ ከሀነ ምናልባት በእነዚህ አዳዲስ ፎሜሽች መጨነቅ አይገባቸውም ይሆናል፡፡ ሆኖም እንደሚገመተው ልዩነት ፈጣሪ አማካዮችን በገበያው ማግኘት ካልቻሉ እንደ ፈርጉሰን በእጃቸው አጨዋወታቸው ቀውስ ውስጥ ባይጥላቸውም እንደቀድሞው አስፈሪ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ስኮትላንዳዊው በኦልድትራፎርድ የሚሰማቸውን ውጥረት ለመቀሰን ለጊዜውም ቢሆን ያላቸው አማራጭ ግን ባሉት ተጨዋቾች አጨዋወትን መቀየር ይመሰላል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የወያኔ ልዩ ፖሊስ በምስራቅ ሃረርጌ ዞን ንጹሃንን በጥይት ፈጀ
Share