December 23, 2024
5 mins read

ሕመማቸው ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል! በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ክርስቲያን እና አቶ ዮሐንስ “ህመማቸው እንደባሰባቸው” ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ

471269298 567942632655786 3154896902472520242 nበቃሊቲ ማረሚያ ቤት እስር ላይ የሚገኙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባሉ አቶ ዮሐንስ ቧያለው “ለከፍተኛ ሕመም” መዳረጋቸውን የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ቤተሰቦቻቸው እስረኞቹ ቀዶ ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ “የማያቋርጥ የደም መፍሰስ እንዳጋጠማቸው” ገልጸዋል።
ሁለቱ ፖለቲከኞች “በተደጋጋሚ አቤቱታ” ከሁለት ሳምንት በፊት ቀዶ ሕክምና ማድረጋቸውን ጠበቃቸው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ሁለቱ ግለሰቦቹ በሆስፒታል ይቆዩ ቢባልም “ያንን እምቢ ብለው በሰዓታት ልዩነት በማይመች መኪና ጭነው ወደ ማረሚያ ቤት መልሰዋቸዋል” ሲሉ የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ተናግረዋል።
አንድ የአቶ ክርስቲያን የቅርብ ቤተሰብ “ቁስሉም አልደረቀም እና ደግሞ ደም እየፈሰሳቸው ነው። ሐኪሞቹም ተናግረዋል፤ ደም መፍሰስ ሊያጋጥም እንደሚችል እና ይህ ሲያጋጥምም እንድታመጧቸው ብለው ነበር” ብለዋል።

ነገር ግን ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ወደ ሆስፒታል አለመወሰዳቸውን ገልጸዋል።
ሕክምናውን ተከትሎ ለሚከሰተው የደም መፍሰስ ማስታገሻ እንደተሰጣቸው ያስታወሱት የቤተሰብ አባላቱ “የተሰጣቸው የማስታገሻ መድኃኒትም አልቆባቸዋል። ሕመሙን ለማስታገስ ቶሎ ቶሎ እየወሰዱት ስለነበር” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአቶ ዮሐንስ ቤተሰብ አባል፤ “ትላንት ማስታገሻ ይዘን ስንሄድ መግባት አትችሉም ተባልን፤ ለምንድን ነው ስንል? ሊቀየሩ ነው አሉን። እስከ ትናንት ግን እነሱ አይሄዱም ብለውን ነበር። ትናንት በድንገት ተነስተው ሊወጡ ስለሆነ ምንም ምግብ ማስገባት አትችሉም መድኃኒትም አይገባም ብለው ከለከሉን” ብልዋል።
የአቶ ክርስቲያንም የቤተሰብ አባል በተመሳሳይ “ትላንትና ምግብም ማስታገሻም ይዘን ስንሄድ የሚያስገባን ስለሌለ ተመለስን” ሲሉ ተናግረዋል።
የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ሰኞ ታህሳስ 7/ 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ “ታራሚዎችን ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ገላን አካባቢ ወደ ሚገኘው እና በተለምዶ አባ ሳሙኤል ተብሎ ወደሚጠራው ማረሚያ ቤት እንደሚያዘዋውር አስታውቆ ነበር።
ይህን ተከትሎም “በአዲስ አበባ ቃሊቲ ማረሚያ ማዕከል ይሰጥ የነበረውን የታራሚ ቤተሰብ ጥየቃም ሆነ የቢሮ ስራ አገልግሎት ከታህሳስ 8 እስከ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ተቋርጦ የሚቆይ” መሆኑን ጠቁሟል።

ኮሚሽኑ በዚሁ መግለጫው ካለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጀምሮ የተቋረጠው አገልግሎት ከዛሬ ታህሳስ 14 እንደገና እንደሚጀምር በመግለጫው ገልጾ ነበር።
ነገር ግን የአቶ ክርስቲያን እና አቶ ዮሐንስ ቤተሰቦች ዛሬም ምግብ ማስገባት እና እስረኞቹን መጠየቅ እንዳልቻሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ጉዳዩን በተመለከተ የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገረመው አያሌው ጋር ያደረገው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ምላሽ ባለማግኘቱ አስተያየታቸውን ማካተት አልቻለም።

ዐቃቤ ህግ አቶ ዮሐንስ ቧያሌው እና አቶ ክርስቲያን ታደለ ላይ ክስ የመሰረተው ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ነበር። ከሁለት የምክር ቤት አባላት በተጨማሪ ሌሎች 50 ግለሰቦች እና ፖለቲከኞችም በአቶ ዮሐንስ ቧያሌው ስም በሚጠራው የክስ መዝገብ ተካትተዋል።

Ethio Youth Movement የወጣቶች ንቅናቄ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop