December 23, 2024
12 mins read

አዲስ አበባ እና ሀረር ከተማ በኦርሚያ ስር እንዲሆኑ ጥያቄ ቀረበ

GfbPJ4iW4AAURYy

ኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ በሚገኘው የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ተሳታፊዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ ባለቤትነት፣ በክልሎች የወሰን አከላለል፣ በፌዴራል የሥራ ቋንቋና ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ትኩረት ያደረጉ አጀንዳዎችን ለኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቀረቡ፡፡

የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ታኅሳስ 7 ቀን የጀመረውና ዛሬ ታኅሳስ 13 ቀን 2017 ዓ.ም. በተጠናቀቀው በኦሮሚያ ክልል ገልማ አባ ገዳ አዳራሽ ባካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብ መድረክ፣ ተሳታፊዎች ለኢትዮጵያ ዜጎች ያለመግባባትና ያለመተማመን ምክንያት ሆነዋል ያሏቸውን፣ እንዲሁም የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ናቸው ብለው የለዩዋቸውን አጀንዳዎች ማቅረባቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎችን የወከሉ ተሳታፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከአርሲ ዞን ሞሊሳ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞችን በመወከል  በመድረኩ የተሳተፉት መምህር ብርሃኑ ቡሬሶ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በክልሎች ያለው የድንበር አከላል ለግጭት መንስዔ በመሆን ዜጎችን ለሞትና ለመፈናቀል የዳረገ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት የተሠሩት  የወሰን  ማካለል ሥራዎች ፍትሐዊነት የጎደላቸውና የኦሮሚያን መሬቶች ለሌሎች አሳልፈው የሰጡ ናቸው፡፡ ይህ በመሆኑም ኦሮሞ ለዓመታት ከተለያዩ የአገሪቱ ብሔሮች ጋር እንዲጋጭ ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡

‹‹በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነት እንዲመጣ፣ መተማመን እንዲኖርና መግባባት እንዲፈጠር ጥያቄዎቻቸው ሊመለሱ ይገባል፡፡ በመሆኑም መሠረት ኦሮሞን ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር እያገጩትና እያጋደሉት የሚገኙት የወሰን ጉዳዮች በአፋጣኝ መፍትሔ ማግኘት አለባቸው፡፡ ኦሮሚያን ከሌሎች ብሔሮች ጋር ግጭት ውስጥ ከከተቱት ወሰኖች መካከል ሞያሌና ሐረር ከተሞች ሙሉ በሙሉ ወደ ኦሮሚያ እንዲካለሉ አጀንዳ አቅርበዋል፡፡ ሞያሌ በአሁኑ ወቅት የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች ባንዲራዎች የሚውለበለቡባት ከተማ በመሆኗ፣ ይህ ቀርቶ በኦሮሚያ መተዳደር እንደሚገባትና ሐረርም የምዕራብ ሐረርጌ ዋና ከተማ መሆን አለባት፤›› ሲሉም አክለዋል።

አቶ ብርሃኑ አዲስ አበባ ቀደም ባሉት ጊዜያት የኦሮሞ መሆኗን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ስለሆነም አዲስ አበባ በፌዴራል መንግሥት መተዳደሯ ቀርቶ በኦሮሚያ ሥር እንድትተዳደርና የሕዝቡም ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ አጀንዳ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹የኦሮሚያ ሕዝብና ወክዬ የመጣሁትም የማኅበረሰብ ክፍል ሌላው ያልተፈታለትና ምላሽ ያላገኘበት ነገር የቋንቋ ጉዳይ ነው፤›› የሚሉት ግለሰቡ፣ ‹‹አፋን ኦሮሞ በስፋትና በተናጋሪ ብዛት  ከፍ ያለ ቁጥር ያለውና  ምሥራቅ አፍሪካ ጭምር በስፋት የሚነገር በመሆኑ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆን አጀንዳ አቅርበናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ በአገሪቱ ሕዝቦች ዘንድ መግባባት የለም፡፡ ይህ በመሆኑም የግጭት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ስለሆነም ችግሩን ለመቅረፍ በሚቻልበትና የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተስማሙበትና ሁሉንም ዜጋ በአንድ የሚወክል ባንዲራ እንዲኖር አጀንዳ አቅርበናል፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ብርሃኑ ማብራሪያ፣ በመድረኩ ሕገ መንግሥቱ ስለሚሻሻልባቸው ሁኔታዎች ሐሳቦች የተንፀባረቁ ቢሆንም፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 መውጣት የለበትም የሚል አጀንዳ አቅርበዋል፡፡

‹‹አንቀጹ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጥቅማቸው እስከተከበረላቸው ድረስ አብረው ለመቀጠል የሚያስችላቸው ሐሳብ የያዘ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ዓውድ ወጥቶ አንዱ ብሔር ሌላውን ጨቁኖና ተጭኖ የሚኖር ከሆነ ለመገንጠል ዋስትና የሚሰጥ በመሆኑ ከሕገ መንግሥቱ መውጣት የለበትም፤›› ብለዋል፡፡

አሁን በአገሪቱ ለሚታዩ ግጭቶች፣ አለመግባባቶች፣ ሞትና ለዜጎች መፈናቀል  ምክንያት ሆነዋል ባሏቸው ጉዳዮች አጀንዳ ማቅረባቸውን የተናገሩት አቶ ብርሃኑ፣ የኦሮሞ ሕዝብ የዘመናት ጥያቄዎችና በአገረ መንግሥት ግንባታው ላይ ሊኖረው ስለሚገባው ድርሻ በዋናነት የተነሱና ለኮሚሽኑ የቀረቡ አጀንዳዎች መሆናቸውን አክለዋል፡፡

ዜጎች እርስ በርስ እንዳይግባቡና እንዳይተማመኑ በማድረግ ወደ ግጭት እንዲገቡ የሚያደርጓቸው ነጥቦች በምክክር ሊፈቱ ይገባል ያሉት ከምሥራቅ ወለጋ ዞን ሲምቡ ሶሬ ወረዳ የማኅበረሰብ ተወካይ የሆኑት አቶ ቦጋለ ማሞ ናቸው፡፡

አቶ ቦጋለ እንደገለጹት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገሪቱ ሕዝቦች አብሮ የመኖር እሴት ተሸርሽሮ በየሥፍራው ግጭት፣ ሞትና መፈናቀል በየዕለቱ የሚታይና የሚሰማ ክስተት ነው፡፡ ለዚህም ዋና ምክንያት የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄዎች ሊመለሱ ባለመቻላቸውና ቅሬታዎቻቸው  በንግግር፣ በውይይትና በመግባባት በጊዜ ባለመፈታታቸው ነው፡፡

ስለሆነም እሳቸውን የወከላቸው ማኅበረሰብ በአገር ደረጃ ያልተግባባቸውንና ያልተማመንኩባቸው ብሎ ለይቶ የሰጣቸውን አጀንዳ ይዘው ወደ መድረኩ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከአጀንዳዎቻው መካከል አንዱ የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ ነው፡፡ አዲስ አበባ ቀደም ባሉት ዘመናት የኦሮሞ ርስት መሆኗን የሚያመላክቱ ሰነዶች አሉ ይላሉ፡፡ ይህ በመሆኑም ከተማዋ ለባለመብቱ ለኦሮሞ ሕዝብ መሆን እንደሚገባትና ከፌዴራል አስተዳደር በመውጣት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መተዳደር አለባት የሚል አጀንዳ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

ኦሮሚፋ ቋንቋ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆን፣ በባንዲራ ዙሪያ ሁሉም የአገሪቱ ሕዝቦች ይሁንታን ያገኘና ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተቀበሉትና ይወክለኛል የሚሉት እንዲኖር አጀንዳ ማቅረባቸውንም ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ቦጋለ፣ በድንበር ዙሪያ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር ዓመታትን የዘለቀ ጥያቄ አላትም፡፡ በዚህ ላይ ከኤርትራና ከሱዳን ጋር ያላት የወሰን ይገባኛል ጥያቄ በአፋጣኝ እንዲፈታ፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ያለው የወሰን ግጭት እንዲቆም፣ ወሰኖቹ በሚካለሉበት ሁኔታ ላይ አጀንዳ መቅረቡን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በሕዝብ ውሳኔ ወደ ኦሮሚያ የተመለሱና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ እንደ ‹‹ያሶ›› ዓይነት አካባቢዎች በሕጋዊ መንገድ ወደ ኦሮሚያ እንዲጠቃለሉ አጀንዳ መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡

ከሕገ መንግሥቱ ክፍል አንቀጽ 39 በምንም ዓይነት ሁኔታ መውጣት የለበትም ብለዋል፡፡ ለዚህም ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡ ሕገ መንግሥቱ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መተማመኛ ሰነድ እንደ መሆኑ፣ በሕዝቦች መካከል አብሮ ለመኖር የሚያስችል ስምምነት ከጠፋ አንቀጹ መለያየትና መገንጠልን ይፈቅዳል ይላሉ፡፡ በመሆኑም በሕገ መንግሥቱ የአንቀጹ መቀመጥ ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዋስትና ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በመካሄድ ላይ በሚገኘውና እስከ እሑድ ታኅሳስ 13 ቀን 2017 ዓ.ም. በሚቆየው አገራዊ የምክክር መድረክ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የአጀንዳ ማሰባሰብና ለአገራዊ የምክክር ጉባዔ  የተወካዮች መረጣ፣ ታኅሳስ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. ተጠናቋል፡፡ በመጪዎቹ ቀናት የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የባለድርሻ አካላት ምክክር እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል።

Reporter

Go toTop

Don't Miss

‹‹በትግራይ ግጭት የተካሄደው የምርመራ ሪፖርት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት አግኝቷል›› – ዶክተር ዳንኤል በቀለ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን
Addis Ababa

በአዲስ አበባ ሕዝብን ሲቀሰቅሱ የነበሩ 5 ሰዎች ታሰሩ

“እኔ በአዋጅ ሳይሆን በትዕዛዝ ነው የምመራው፤ እሰር የሚል ትዕዛ ደርሶኝ