ወራሪውን የጣሊያን ጦር ለመመከት አርበኞች ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰባሰቡባት ስፍራ – “አንዲትግራር”

(ኢፕድ) “አንዲትግራር” በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሞጃና ወደራ ወረዳ እንግዳ ዋሻ አንቀላፊኝ ሜዳ በተባለች ስፍራ ላይ ኢትዮጵያውያን በአንድ ተሰባስበው ወራሪውን የጣሊያን ጦር ለመዋጋት የጦር ስትራቴጂ ቀይሰው የመጀመሪያው የአርበኞች ማህበር የመሰረቱባት ታሪካዊ ስፍራ ነው።

ወደ አንዲትግራር ለማቅናት ከደብረሲና ተነስተው እስከ ታሪካዊው ስፍራ ለመድረስ የአካባቢው ፒስታ መሰል አቧራማ ወጣ ገባ መንገድ ማቆራረጥ የግድ ይላል። አካባቢው ተፈጥሯዊ መስህብ ያለው በመሆኑ ወጣ ገባና ጠጠረማ መንገዱን አንዳያስቡ ያደርጋል።

አንዲትግራር በአካባቢው የሚገኝ እድሜ ጠገብ ባለ ብዙ ቅርንጫፎች የግራር ዛፍ ሲሆን ስፍራው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር የተመሰረተባት ቦታ እንደሆነ የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።

 

ጥር 1 ቀን1931 ዓ.ም በባላንባራስ ባሻህ ኃይሌ ሰብሳቢነት ‹‹አንዲትግራር›› ስር ተገናኝተው አርበኞች ተወያዩ፡፡ ራስ አበበ አረጋይ፣ልጅ ግዛው ኃይሌ፣ ደጃዝማች ተሰማ እርገጤ፣ ፊታውራሪ ታደሰ በላይነህ፣ ልጅ ከፈለው ወልደፃዲቅ፣ አቶ ፀሃይ እንቁ ፃዲቅ፣ አቶ ፀኃይ እንቁ ስላሴ፣ ራስ መስፍን ሽመልስ እና ሌሎችም የጦር አለቆች ጦራቸውን በመያዝ በግራሩ ስር መሰበሰባቸውን የአካባቢው አባቶች ይናገራሉ፡፡

የወረዳው ባህልና ቱሪዝም መረጃ እንደሚያመለክተው በአካባቢው አንዲት ግራር እንጂ ሌሎች ዛፎች አልነበሩም። ግራሯ 200 ዓመት እድሜን ያስቆጠረች ስትሆን የአካባቢው ማህበረሰብ የሽምግልና፣ የስብሰባ እና የሌሎችም ማህበራዊ ክንውኖች ማስፈጸሚያ ቦታ ነበረች።

ከኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር ምስረታ በኋላም ቦታዋ አንዲትግራር በሚል በየአመቱ ጥር አንድ ቀን ታስቦ ይውላል። ይሁንና ታሪኩ በአግባቡ ወጣቱ ጋር ባለመድረሱ እና ለውጭ አገራትን ባለመተዋወቁ ብዙ ጎብኚ አያውቀውም።

በጌትነት ተስፋማርያም
ፎቶሀዱሽአብርሃ

ተጨማሪ ያንብቡ:  በበዓላት በሚኖረዉ ከፍተኛ የሀይል ፍላጎት የተነሳ ሊያጋጥም የሚችለውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ለማስቀረት በቂ ዝግጅት ማድረጉን ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ

1 Comment

  1. This place is where Menze Amaras originally discovered the skills of holding logical conversation listening skills, that lasted for generations used to make the law of the country that is in works till date.

Comments are closed.

Share