ከኖርዲክና ስካንዲኔቭያ ሃገሮች ዴሞክራሲ ምን እንማራለን? – በ.ከ.

በርካታ የፖለቲካ ምርምሮችንና ጥናቶችን ስንቃኝ የዴሞክራሲ” ሃሳብ ትልቁንና ማዕከላዊውን ሥፍራ መያዙን እንገነዘባለን። ዴሞክራሲ – ችግር (problem)፣ መፍትሄና (solution) ሂደት (process) ነች። በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ዴሞክራሲ የትምህርት ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ምርምርና ጥናት ከመሆን አልፋ ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ የዋለች ማደናገርያ ሆናለች። በዚህ ዘመን ብዙዎች ዴሞክራት ለመምሰል ይሞክራሉ። የሕዝብ ፍላጎትና ፈቃድ ደግሞ ዴሞክራሲን ሕጋዊ ማድረግ ነው። ይህን ፍላጎትና ፈቃድ በሥራ ላይ የሚያውለው ኃይል (power) በሥርዓት የመምራት ኃይል (the power to rule) የተቀናጀ የሕዝብ መንግሥት ነው።

ስካንዲኔቭያ የምንላቸው ሃገሮች ዴንማርክ፣ ኖርዌና ስዊድን ሲሁኑ ፊንላንድና፣ አይስላንድ፣ የፋሮ ደሴቶች Faroe Islands)፣ አላንድና ስቫልባርድ ደሴቶች (Aland Islands and Svalbard) እንዲሁም ጃን ማዬን (Jan Mayen)ሲጨመሩ ኖርዲክ ሃገሮች (Nordic Countries) ይባላሉ። የስካንዴኒቪያን ሃገሮች ዴሞክራሲ የሰዎችን ቀልብ ከሳበ ቆይቷል። ዴሞክራሲ ፅንሠሃሳብ ነች፣ ባይን አትታይም። ስለማትታየዋ ዲሞክራሲ ማውራት ደግሞ ቀላል ላይሆን ይችላል። ዴሞክራሲ እንዴት ነው የምትተገበረውእንዴትስ ነው ማህበራዊ ለውጥ ልታመጣ የቻለችውዲሞክራሲን አስመልክቶ ገለጻዎቹ በርካታ ከመሆናቸውም በላይ አንዳንዶቹ በትክክል ያልተነገሩና ያልተጻፉ (imprecise) ሌሎቹ ተለዋዋጭነቷን (continuously changing) የሚያስረዱ ናቸው። ዴሞክራሲ መቻቻል ነች። ዴሞክራሲን ከሥር መሠረቱ ለማወቅ የስካንዴኒቭያን ምሁራን የትናንሽ ሃገሮችን የአብሮነት ባህል ሳይቀር ያጠናሉ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ዴሞክራሲን አስመልክቶ ሶስት ትላልቅ መጽሃፍ ለዕትመት በቅተዋል። ሁለቱ በእንግሊዝኛ ነው የተጻፉት (Koch & Ross eds. 1949, Lauwerys ed. 1958)። በተጨማሪም የስካንዴኒቭያን ዴሞክራሲ፣ በተለይም ደግምፕ ከፅንሰሃሳብነት ወደ ቁሳካልነት ተለውጦ በርካታ ማህበራዊ ለውጦችን ማምጣት ስለቻለው ምጣኔኃብታዊው ዴሞክራሲ በበርካታ ጽሁፎች ለዕትመት በቅተዋል።

የስካንዴኔቪያውም ሆነ ባጠቃልይ የኖርዲክ ሃገሮች ዴሞክራሲ ከሌሎቹ የምዕራቡ ዓለም ዴሞክራሲ የተለዩ ባይሆንም በምጣኔኃብት እድገት በተመጣጣኝ የሃብት ክፍፍል ዙርያ የጎላ ለውጥ ማምጣታቸውን ማንም አይክድም። ዴሞክራሲያቸው በሂደት ላይ ስለሆኑ ክርክሮችና ሙግቶች ይበዛሉ። የስካንድኔቭያ ዴሞክራሲ አርዓያ (model) ነች ሲባል ፍፁም ነጥራ የወጣች” ነች ለማለት አይደለም። ይሁንና ግን የዴንማርክ፣ ኖርዌና ስዊድን ዴሞክራሲ ሌሎች እንደ ምሳሌ ሊወስዷቸው የሚገቡ በጎ ጎንኖች አሏቸው።

ዴሞክራሲ ምንድን ነችዴሞክራሲን ስናስብ ሶስት ነገሮች ከፊታችን ድቅን ይላሉ። እነሱም – ተወካይ (ወኪል) (representative)፣ ህገመንግሥታዊ (constitutional)፣ ፖለቲካዊ (political) የሚሉት ናቸው። የመራጩን ጉዳይ ሊያስፈጽም የሚችል ሃቀኛ፣ ትጉህና አደራ ተቀባይ ወኪል ከሌለ ዲሞክራሲን ማሰብ አይቻልም። ህገመንግስት ከሌለ ዲሞክራሲም የለም። ልበ ሠፊነት፣ ታጋሽነት፣ የመቻቻልና የመቀባበል ፖለቲካ ሳይሰፍን ዲሞክራሲ እያሉ ማውራት ውሃን ሲወቅጡ መዋል ነው። የሶስቱ አበይት ጉዳዮች ድምር የሆነችው ዴሞክራሲ ዋናው ተግባሯ ሕዝብን አስማምታ የሁሉም – ለሁሉም – አገልጋይ የሆነ መንግሥት” መመስረት ነው። ሮበርት ዳህል የተባለው የስካንዴኒቭያ ምሁርዴሞክራሲ ማለት ድርጅት ለመመስረት አልያም ለመቀላቀል የሚኖረው ነጻነት፣ ሃሳብን የመግለጽ መብት፣ የመምረጥ መመረጥ መብት፣ ሙያዊ ብቃቱ ካለ መንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ማገልገል መቻል፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ድጋፍና ድምጽ የመሰብሰብ መብት፣ መረጃ የማግኘት መብት፣ ነጻና ሚዛናዊ ምርጫ፣ የመንግሥት ፖሊሲዎች በምርጫውና በሌሎች ጠቃሚ ሃሳቦች ላይ ብቻ እንዲወሰኑ ማድረግ ናቸው” ይላል።

ዴሞክራሲ ሂደት ነች። ያለቀች፣ የነጠረች፣ በቂ” – የምትባል ዴሞክራሲ የለችም። አንድ ግለሰብ ተፈጥሮ ካደለችው ሙሉ ነጻነቱ ላይ ቆንጥሮ ለመረጠው የፖለቲካ ተቋም በአደራ ይሰጣል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ማዕከላዊውን የመንግሥት ኃይል ለመቆጣጠር በሃሳብ ይታገላሉ። ኃይላቸው የመረጧቸው ግለሰቦች ናቸው። በብዙሃን ምርጫ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች መንግሥት ይመሠርታሉ። የመንግሥት ተቋማት ፖለቲካዊ ውሳኔ ያደርጋሉ። መንግሥት አደራ ተቀባይና አገልጋይ እንጂ በዝባዥና ጉቦኛ አይደለም። በኖርዲክ ሃገሮች ውስጥ አንድ ግለሰብ ከሕጻንነቱ ጀምሮ ግብረገብንና የህግ የበላይነትን በቤቱ፣ በሕጻናት መዋያ፣ በትምህርት ቤት ሳለ ይማራል። ግለሰቦች የለበሱት ግብረገብነትና ሥነምግባር ሥልጣንን ለግል ፍላጎታቸው ማሟያ እንዳያደርጉ ኅሊናቸውን ይገዛል።

ማህበረሰብ ምን ያህል ነው ዴሞክራሲያዊ መሆን ያለበትማህበረሰቡ ፖለቲካውንና ምጣኔኃብቱን ለማያያዝ ዴሞክራሲን እንደ መርህ ይጠቀማል። ዴሞክራሲ አትጨበጥም፣ ቢሆንም ግን ልቅ ልትሆን አይገባም” ይላሉ የስካንዴኒቭያን ሃገር ሰዎች። ዴሞክራሲ በውዥንብርና ሃሰት ታምሳ ድንገት አስመሳይ ሰው እጅ ውስጥ ከገባች ማህበራዊ መብቶች ይደፈጠጣሉ” ብለው ይፈራሉ። ከአስመሳዮች የጠራችው የስካንዴኔቭያን ሃገሮች ዴሞክራሲ ጥንቃቄን አክላ ማህበረሰባዊና ኤኮኖምያዊ ጉዳዮችን እንደ ሰንሠለት አያይዛ የባህል፣ የትምህርትና የህግ ፖሊሲዎችን መስመር ታሲዛለች። መንግስት የሕዝቦች ነጻነት (liberty) እንዲረጋገጥ የግለሰቦች ነጻነትና መብት ላይ ጥበቃ ይደረጋል። አንድ ግለሰብ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በነጻነት ይሳተፋል። ይህም ማለት በሃገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ግለሰቡ ወሳኝ ሚና የመጫወት ብቃቱን በንቃት ካላንዳች ፍርሃት ያንጸባርቃል ማለት ነው። ተሳትፎ ካነሰ ጥቂቶች ደፋር (ተናጋሪ) –ብዙሃን ፈሪ (አዳማጭ)” ይሆኑና ፖለቲካ በማይገባው ሰው እጅ መዳፍ ውስጥ ትወድቃለች። ሰዎች ካላንዳች መሸማቀቅ፣ ይሉኝታና ማስመሰል የሚያደርጉት ንጹህ የፖለቲካ ተሳትፎ በዴሞክራሲ ስም የሚወሰልቱ አስመሳዮችንና ጭብጨባ ወዳድ ፖለቲከኞችን ገለል ያደርጋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጠቢቡ ሰለሞን የፈተናት ሴትና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፎክሩት እርጉሞች! - በበላይነህ አባተ

በኖርዲክና ስካንዴኒቭያን ሃገሮች ውስጥ መንግሥት ማለት ማህበራዊ ጥቅሞችን መልሶ ለመራጮቹ ግልሰቦች እኩል ለማከፋፈል ንጹህ የፖለቲካ ሥራ የሚከውን አካል ነው። ፖለቲካ በስካንዴኒቭያን ሃገሮች ውስጥ ሥልጣን ላይ መወጣጫ ስውር ገመድ አይደለችም። እርግጥ ገመዷን ካልያዙ የፖለቲካ ሥራን ማካሄድ አይቻልም። ግለሰቦች እኩል ክህሎትና እውቀት ሊኖራቸውም አይችልም። ሰዎች ተመሳሳይ የሆነ ሲቪል፣ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ኃብታዊና ማህበራዊ ግንዛቤ የላቸውም። የግለሰቡ ውስጣዊ ባህርይና የግንዛቤ ደረጃ እይታን ያለያያሉ። ፖለቲካ ችሎታን፣ ብስለትን፣ ትህትናን አርቆ አሳቢነትንና አስተዋይነትን ይጠይቃል። በኖርዲክና ስካንዴኒቭያ ሃገሮች ውስጥ እነዚህ ምግባሮች የሉተራን ፕሮቴስታንት ኃይማኖት አስተምርሆ ያስታጠቃቸው ዛሬ ባህል መስለው የሚታዩ በጎ ፍሬዎች ናቸው። የሆነ ሆኖ ግን አንድ ምሁር ፖለቲካውን ሲገልጹት ድምጽ ይቆጠራል ግብዓት ይወስናል” ብለዋል (votes count but resources decide)። ፖለቲካ መሠሪ ካልሆነች ባለሙያ ነች። መሠሪ ፖለቲካ የግል ጥቅምን ማፈሻ አካፋ ነች። ባለሙያ ፖለቲካ ችግሮችን ከሥር መሠረቱ ተረድታ መፍትሄ ታዘጋጃለች። ባለሙያ ፖለቲካ እንክርዳዱን እየወረወረች የሚጠቅመውን ባማረ ሳህን ታቀርባለች፣ አቅም ካነሳትም ሕዝቡን ታወያያለች።

በስካንዴኒቭያን ሃገሮች ውስጥ ዴሞክራሲ ምን ይዘት አላትየፖለቲካ ተሳትፎና የሰዎች እኩልነት (participation and equality) የስካንዴኒቭያው ዴሞክራሲ አንኳር ጉዳዮች ናቸው። ዴሞክራሲ እንዲሁ ተወልዳ እንዲሁ አታድግም፣ ከፊት ለፊቷ የሚመጡ በርካታ ጣጣዎችን እየቀረፈች ነው ዘመን የምትሻገረው። የውስጥ መቆራቆሶችና ትርምሶች የደሞክራሲ ቀበኞች ናቸው። የእንግሊዝና የአሜሪካ የፖለቲካ ዴሞክራሲ ውጣ ውረዶች ለስካንዴኒቭያኖች ተሞክሮ ናቸው። ከከበርቴውም ሆነ ከኅብረተሰብዓዊው የምጣኔ ኃብት ሥርዓት ጠቃሚ ጠቃሚውን መርጠው በሥራ ላይ ማዋላቸው ስካንዴኒቭያኖቹን የእኩልነት ማህበራዊዴሞክራሲ ፍሬ እንዲመገቡ አስችሏቸዋል። በማህበራዊዴሞክራሲ የሚታገዘው የምጣኔ ኃብትዴሞክራሲ ወደትረፈረፈ ምርትና ወደተሻለ የኃብት ክፍፍል እያሸጋገራቸው ነው።

የስካንዴኒቭያው ፖለቲካዊዴሞክራሲ ምንድነውየስካንዴኒቭያው ፖለቲካዊዴሞክራሲ ዋነኛ ዓላማው የፖለቲካ ባህሉን ማሳደግ ነው። ፖለቲካ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ወይንም ፓርላሜንት ውስጥ ህግ ሆኖ ይነደፋል። በመንግሥትነት የተሰየመው ይህን ህግ የሚያስፈጽመው ክንፍ (executive branch) ለፓርላሜንቱ ተጠሪ ነው። ይህ አካል ሥራውን በጥራት ካልሰራ የሕዝብ ተወካዩ ምክር ቤት ሊያስወግደው ይችላል (vote of non-confidence)። የህግ ተርጓሚ ተቋማት (judicial institutions) ለዴሞክራሲው ግንባታ ጉልህ ሚና ባይጫወቱም እንኳን ሲቪል መብቶችን ያስጠብቃሉ። ፖለቲካዊዴሞክራሲ ሕዝቡ የፖለቲካ ተሳታፊ እንዲሆን ታበረታታለች፣ ታነቃቃለች። በምርጫ ጊዜ ብቻ ተሳትፎን ማሳየት በቂ የፖለቲካ ባህልን አይገነባም። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ስዊድንና ኖርዌ ውስጥ በአብላጫ ድምጽ ያሸነፉ ነጠላ ፓርቲዎች ወንበሩን የመቆጣጠር ዕድል ተቀናጁ እንጂ በስካንዴኒቭያን ሃገሮች አብዛኛውን ጊዜ ፓርቲዎች በጥምረት ሥልጣን ስለሚይዙ ፉክክሩና ተሳትፎው ከፍ ያለ ነው። ሕዝቡ ማንኛውንም ግልጋሎት ከሙስናና አድሎ ውጭ ከሆኑት ዞኖችና ክፍለሃገሮች ያገኛል። የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤቶች ሥልጣኑን ሰብስበው አይዙም፣ በተዋረድ ለተቋቋሙት መስተዳድሮች (local and regional governments) ያከፋፍሉታል። በስካንዴኒቭያን ውስጥ ግብረገብና ፖለቲካ ጎን ለጎን ይሄዳሉ። መንግሥት በየተዋረዱ ያሉ መስተዳድሮችን በታማኝነት በቂ የራስ ገዝ ሥልጣን (autonomy) ያስጨብጣቸዋል። እነዚህ አካላት ሥራቸውን በታማኝነት ይወጣሉ፣ ሕዝቡም ያከብራቸዋል። ይህን የመሰለው ሙሉ የሥልጣን ውክልና (delegation of power)ፌደራላዊ ቅርጽ ከያዙ መንግሥታ ክንውኖች ለየት ይላል።

ማህበራዊዴሞክራሲ እንዴት ይገለጻልማህበራዊዴሞክራሲ በቅንነትና በመልካም ስነምግባር በሚከወን ሕዝባዊ ግልጋሎት ይገለጻል። ስነምግባሩ በማህበራዊ ቡድኖችና ግለሰቦች መካከል ያለውን የመደብና አካባቢያዊ ልዩነት(class and regional differences) ያሟሟል። የስካንዴኒቪያው ሰዎች ተመሳሳይ (homogeneity) የመሆናቸው ጸጋ ሰላምን አስገኝቶላቸዋል። ስካንዴኒቭያኖች በቤትም፣ በመሥሪያ ቤትም ሆነ በስብሰባ ቦታ ላይ ባህርያቸው ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው። መቻቻል የማህበራዊዴሞክራሲው ሁነኛ ነጸብራቆች ናቸው። ማህበራዊዴሞክራሲ ከፖለቲካውና ምጣኔኃብታዊው ዴሞክራሲ በቂ ውጤቶች እንዲፈልቁና መልካም ትስስሮች እንዲያድጉ ትጥራለች። ማህበራዊዴሞክራሲ ባጭሩ መግባባት፣ መተሳሰብና መቻቻል ናቸው። ከጥርጣሬና ከለበጣ ውጭ የሆነው መልካም አንድነታቸው ያገኙትን በሰላም እንዲካፈሉ አድርጓቸዋል። የማህበራዊዴሞክራሲያዊ እሴቶች የሆኑት እኩልነትና ትብብር(equality and solidarity) ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ይልቅ ትልቅ ግምት ይሰጣቸዋል። የእኩልነት” መርኅ የፖለቲካ ሥራ ብቻ ሆኖ ከተተወ በቶሎ አይተገበርም። እኩልነት” ማህበራዊ ተግባርም ነው። እኩልነትና አድሎየለሽ መልካም ቅርብርቦሽ (equality and equity) የስካንዴኒቭያው ሃገሮች ዓይነተኛ መግለጫ ነው። መልካም ባህርያት ለፖለቲካ ባህል እድገት አስተዋጾ አላቸው። የነቃ ተሳትፎ ከሌለ ዴሞክራሲ ትቀጭቻለች። ለዚህም ነው ተሳትፎና የሲቪል መብቶች መከበር ጎን ለጎን የህገመንግስት ጥበቃ የሚደረግላቸው። ዴሞክራሲ አሰስ ገሰሱን አትሰበስብም። ጥሩ ሃሳብ እንዳለ ሁሉ መጥፎ ሃሳብም አለ። ዴሞክራሲ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚወረወሩ ሃሳቦችን ታበጥራለች። ዴሞክራሲ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚንጸባረቀውን ማህበራዊ ሕይወት ትመዘናለች። ዴሞክራሲ – ግለሰቡ አንዳንዴ እንደግለሰብነቱ አንዳንዴ ደግሞ እንደ ማህበረሰብ አባልነቱ እርሷ የሰጠችውን ፍሬ ማጣጣሙንም ትገመግማለች። ከአራቱም አቅጣጫ የሚወረወረው ሃሳብ በጊዜና በሂደት እየተደመረ ለዴሞክራሲ እድገት አስተዋጾ ያደርጋሉ።

ስካንዲኔቭያ ውስጥ ዴሞክራሲ የፖለቲካ መሳርያ (political machine) አይደለችም፣ ይልቁንም ዴሞክራሲ ወደ ማህበራዊዴሞክራሲ (social democracy) የምታሸጋግር ግለሰቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው የሚጓዙባት የአብሮነት ድልድይ ነች። የማህበራዊዴሞክራሲ መገለጫዎች፣ እኩልነት (equality)፣ የቦታ፣ የማንነት፣ የሰው ልጅ እኩልነት (equality of status)፣ የመወዳደር፣ የማወቅ፣ የመሳተፍ፣ ወዘተ፣ እኩልነት (equality of opportunity)፣ እንዲሁም እከሌ እከሌ ሳይሉ እኩል የማስጀመር (equality of starting) ግቦች ናቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አገርና ነፃነት አደጋ ላይ ሲወድቁ ፋኖን የማይደግፍ ከነፃነት ባርነትን የመረጠ ባንዳ ተብሎ በተከታታይ ትውልድ ሲረገምና ሲኮነን ይኖራል!

የስካንዴኔቪያ ምጣኔኃብታዊ ዴሞክራሲ ምንድነውጂዮቫኒ ሳርቶሪ (Giovanni Sartor) የተባለው ምሁር ምጣኔኃብታዊ ዴሞክራሲ ማለት ተመጣጣኝ የኃብት ክፍፍልና በምጣኔ ኃብቱ ላይ እኩል የመወሰን መብትን(redistribution of welath and equalization of economic opportunities) መቀናጀት ነው” ይላል። ምጣኔ ኃብታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካዴሞክራሲው ሌላኛዋ ነጸብራቅ ነች። ፖለቲካ ምጣኔ ኃብቱን ካላሳደገ ባዶ ልፈፋ ነው። ጫና የማያበዛ መንግሥትና ተሳትፎ የሚያበዙ ትጉህ ግለሰቦች ሲገጣጠሙ ምርት ይትረፈረፋል። ፖለቲካና ምጣኔኃብት በቅንነት ከተያያዙ እድገት ያስገኛሉ። ፖለቲካው በጉቦና ሌብነት ከተመረዘ ምጣኔኃብት ይቀጭጫል ወይንም ይባክናል። መርዘኛ ፖለቲካ አመጽ ይጭራል።

ትላልቅ ቤተ ክርስትያኖች በግርማ ሞገስ ከፍ ብለው፣ ተውበው የሚታዩትን ያህል ዴሞክራሲም እንዲሁ ተደስተው ረክተው በሚታዩ ዜጎች ውስጥ ልትታይ ይገባል” ይላሉ የምዕራቡ ዓለም ሰዎች። ቤተ ክርስትያናት ግብረገብን አስተምረዋል። ዴሞክራሲም የግብረገብ ቅጅ ነች። ዴሞክራሲ የሕዝብ ራዕይ ነች፣ ባለ ራዕዩ ሕዝብም ዴሞክራሲን ይተገብራታል። ስካንዴኒቭያኖች ትልቁ ኃብታቸው የሆኑትን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔኃብታዊና ማህበራዊዴሞክራሲዎቻቸውን በእጅጉ ይንከባከባሉ። ዜጋው አዩኝ አላዩኝ ሳይል በትጋት ይሠራል፣ በትህትና ይነጋገራል። ከላዕላይ መዋቅር እስከ ታኅታይ መዋቅር በተዋረድ የሚያገለግሉት ሁሉ ከሕዝብ በታች መሆናቸውን በአቀራረባቸውና በትህትናቸው ይገልጹታል። በእርግጥ የስካንዴኒቭያው ዴሞክራሲ የተለየ አይደለም፣ እንደማንኛውም ሃገር በሕዝብ ተወካይ በምክር ቤቱ ነው የሚመራው። ስካንዴኒቭያኖቹን ልዩ የሚያደርጋቸው ምናልባት በፍቅር፣ ትብብርና ማህበራዊ ተሳትፎ የዳበረው ፖለቲካዊ ባህላቸው ሊሆን ይችላል። ባለጸጋና በሰው ልጆች መብትና እኩልነት የሚያምኑ ዜጎች (affluent and egalitarian) ለመሆን የበቁት ስካንዴኒቪያኖች የስኬታቸው ምስጢር ጽኑ የሆነው መተጋገዛቸውና መቻቻላቸው ነው። ማህበረሰቡ ገንዘቡንና ጉልበቱን እንደችሎታው አፍሶ ተቀራራቢ ጥቅም (benefit) ያገኛል። ዴሞክራሲያቸው እንደ ንጹህ ውሃ ከላይ ከመንግሥቱ መዋቅር እየፈሰሰች እታች ያሉትን ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ጉዳዮችን ታረሰርሳለች። ቅንነት፣ ደግነት፣ መቀባበል፣ መከባበር፣ ወዘተ፣ የመሳሰሉት የመልካም ባህርያት መገለጫዎች ስካንዲኔቭያ ውስጥ ፍትህ (justice) ከፍ እንድትል ምክንያት ሆነዋል።

ደስታን (happiness) ከፍ ለማድረግና ሙስናን (corruption) ለመቀነስ ብሎም አድሎ የለሽ ማህበራዊ ሕይወትን ማበልጸግ በስካንዴኒቭያ ሃገሮች ውስጥ በሂደት ያሉ ያልተገባደዱ የዴሞክራሲ ሥራዎች ናቸው። ደስታ ማህበራዊ ነች። የተራቡ፣ የታረዙ፣ መጠለያ የሌላቸው ሰዎች አጠገብ የሚኖሩ ባለጠጎች ተፈጥሯዊ ደስታ አይኖራቸውም። የጎረቤታቸው ቤት በላዩ ላይ እየፈረሰበት የሚያዩ ሠፈረተኞች ደስተኞች አይደሉም። ዘርፎ ባለገንዘብ የሆነ ሰው ፍርሃት እንጂ ደስታ በውስጡ የለም። ስካንዴኒቭያ ውስጥ አንዱ እየበላ አንዱ ጦሙን አያድርም። መንግሥት ለተቸገረ ግለሰብ ቤት፣ ልብስ መጠለያ ያቀርባል። ሥራ አጥ ድጎማ ያገኛል፣ ትምህርት፣ ሕክምና፣ የሕጻናት መዋያ፣ የአረጋውያን መኖርያ ነጻ ናቸው። መንግሥት ሁሉም የመኖርያ ቤት ባለቤት እንዲሆን ሥርዓት ዘርግቷል። እነዚህ ሁሉ የሕዝቡ አንድነትና ትብብር የወለዳቸው እሴቶች እንጂ ፖለቲካው ብቻውን የፈጠራቸው አይደሉም። መንግሥትም፣ የፖለቲካ ፓርቲም ይሁን የሠራተኞች ማህበራት አሁን የደረሱበት ማህበራዊ ደስታ ምንጩ ሃይማኖቱ ያዳበረው ትብብርና አንድነት ነው።

በዛም አነሰም ስካንዴኒቭያኖች መሠረታዊ ችግሮችን ቀርፈው ማህበራዊ ደስታ ለብሰዋል። ኖርዲኮች በዓለም የደስታ ሠንጠረዥ ላይ ከአንድ እስከ አስር ባለው ሥፍራ ላይ ይመደባሉ። በዘንድሮው – Happiest country in 2019 –ፊንላድ አንደኛ ስትሆን ዴንማርክ፣ ኖርዌ፣ አይስላንድ፣ ኔዘርላንድስዊዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ኒውዚላንድ፣ ካናዳና አውስትራሊያ በቅደም ተከተል እስከ አስረኛ ያለውን ቦታ ይዘዋል። Transparency International በየዓመቱ በሚያወጣው Corruption Perception Index የኖርዲክ አገሮች (Nordic Countries) መቶ በመቶ (100%) ሙስና አልባ ባይሆኑም ከሞላ ጎደል ሙስና የሌለባቸው (non-corruption) ወይም ፀረሙስና (anti-corruption)ሃገሮች በመባል እስከ አስር ያሉትን ቦታዎች በመያዝ ዓለምን ይመራሉ።

የኖርዲኳ ዴሞክራሲ ለሌሎች ታዳጊ ሃገሮች ተሞክሮ መሆን ትችላለችዴሞክራሲያቸው ታጋሽነትን፣ መቀባበልን፣ መቻቻልን፣ መግባባትን በማስተማሩ ረገድ ለአፍሪካ ምሳሌ ልትሆን ትችላለች። የፖለቲካ ተሳትፎን (political participation) ለማሳደግም ከዴሞክራሲያቸው ብዙ መልካም ነገሮችን መቅዳት ይቻላል። የፖለቲካ ተሳትፎ ማለት የሕዝብ ተወካይን መምረጥ (voting representative)፣ በውሳኔ ሕዝብ (referndum) ላይ መስተፍ፣ የፖለቲካ ድርጅትን መፍጠርና በህጋዊው ይሁን ህጋዊ ያልሆነ የተቃውሞ ሰልፍ (legal or illegal protest) ላይ እስከመሳተፍ ያሉትን ሁኔታዎች ያካትታል። ሁልጊዜ የተጠበቀ ውጤት (outcome) ባይመጣም ተሳትፎ ያደረገ ግለሰብ ቢያንስ ቢያንስ መንግሥት ፖሊሲውን እንዲመረምር ማስገደድ በመቻሉ ልቡ ተስፋን (hope) ይሞላል፣ እርካታን (satisfaction) ያዝላል። የፖለቲካ ተሳትፎ መንግስት የተሻለ ፖሊሲ እንዲመርጥና የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ ማስገደድ ማለት ነው። የተሻለ ውጤት ማለት – ደስታና እርካታን (happiness and satisfaction) ማፍለቅ ነው። የፖለቲካ ተሳትፎ ግንዛቤን ከመጨመሩ በላይ ግለሰቡ መብቱንና ግዴታውን (rights and duties) እንዲያውቅ ያደርገዋል።

ኖርዲኮቹን ባጠቃላይ ስካንዴኒቭያኖችን ደግሞ በተናጠል ስናስብ ዴሞክራሲ” ደስታና እርካታ ነች። አፍሪካን ስናስብ ደግሞ ዴሞክራሲ ገና በውል ያልተያዘች ጽንሠ ሃሳብ ነች። አፍሪካ የራሷ ችግር አለባት። ምግብ፣ የመጠጥ ውሃ፣ ልብስ፣ መጠለያ የሌለውንና በፖለቲካ ትርምሶችና መቆራቆዞች ሳብያ ተጎጂ፣ ተሰዳጅ፣ ተፈናቃይ የሆነን ሕዝብ የፖለቲካ ተሳታፊ ማድረጉ ቀላል አይደለም። ሕዝቡን ቀና ማድረጉና ፊት ለፊት ከተደነቀሩበት ችግር ማላቀቁ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል። ዴሞክራሲ – በስሟ ብዙ ተነግዷል፣ ተምረናል የሚሉ ሰዎች ችግር አብዥዎች እንጂ መፍትሄ አቅራቢዎች አልሆኑም። ጥቂት ያልሆኑ ልህቃን – መስዋዕት – ከመሆን ይልቅ – ተጠቃሚ – ለመሆን ስለሚንደረደሩ ነባራዊ ሁኔታዎችንና ሌሎች ግብዓቶችን ማዛመድና ማስተሳሰር ባለማቻላቸው አህጉሪቱን ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ ከተዋል። በአፍሪካ የሚገኙ በርካታ ልህቃን (elites) ሶስቱን ንጥረፖለቲካዎች ማለትም – ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን ማምጣት ያልቻሉ – ሶስት ዓይነት ዲግሪዎችን በከንቱ የተሸከሙ፣ በሕዝብ ገንዘብ የተማሩ የሕዝብ ዕዳ ናቸው። መፈናቀል፣ መሰደድ፣ መራብ፣ መጠማት፣ መገደል፣ መዘረፍ፣ እስር፣ ግርፊያ፣ በዘር መለያየት – የልህቃኑ የፖለቲካ ተሳትፎ(elites political participation) የወለዳቸው አሳፋሪ ተግዳሮቶች ናቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እንሆ፣ ዕቅድ “ሐ“ (Plan C) ተጀምሯ! ትንቢት ከነገር ይቀድማል! - ሲና ዘ ሙሴ 

አፍሪካ ሶስት ዓይነት ልህቅ” አላት። አንደኛው ዓይነት ልህቅ” በመንደር፣ በሠፈር፣ በመሸታ ቤቶች እየተዘዋወር የሰውን ስብዕና የሚንድ፣ ሃሚታንና ውሽንብርን የሚያስፋፋ፣ ጓደኛሞችን፣ ጓዶችን፣ ፍቅረኛሞችን፣ ወዘተ፣ ሶስተኛ ሰው ሆኖ የሚያጣላ፣ የሰውን ገመና ለማሽተት የሚራወጥ፣ በየቤቱ የተበላውን፣ የተወራውን ለማወቅ ጥያቄና ስለላ የሚያበዛ ተራ የመሸታ ቤት ልህቅ” ነው። ሁለተኛው ዓይነት ልህቅ” ትናንሽ እውቀቶችን ተሸኮሞ የሰውን አስተሳሰብ የሚያጣምም፣ ከሃቅ ይልቅ ሸፍጥን የሚወድ፣ አነጋገሩንና አለባበሱን አሳምሮ በተለይ ብርሌ ሲጨብጥ ተንታኝና አዋቂ መስሎ አወዛጋቢ ሃሳቦችን የሚተፋ ለሌሎች የመናገር ዕድል የማይሰጥ የአስተሳሰብና አስተዋይነት ገዳይ ልህቅ” ነው። ሶስተኛው ዓይነት ልህቅ” ፖለቲካውን ተሸሽጎ ዝንተ ዓመት የተገነባን አብሮነትን፣ መተጋገዝን፣ መቻቻልን የሚንድ ሰዎች በዘርና በጎሳ በተከፋፈሉለት መጠን አድፍጦ ጥቅማ ጥቅሞችን የሚቃርም፣ የሌሎችን ሃሳብ የማያዳምጥ፣ ምክንያታዊነትን ንዶ ጽንፈኝነትን የሚገነባ፣ በህዝቦች መሃከል ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ክፉ ልህቅ” ነው። ሶስቱም ዓይነት ልህቃን ምክንያታዊነትና አመክንዮ በሕዝቡ መሃል እንዳይሰራጩና የሰዎች የፖለቲካ አስተሳሰብና ባህል እንዳያድጉ ያደርጋሉ። በሃሰትና በክፋት የተለወሱ ትርክቶች ሁሉ ሃቅንና እውነትን አጠውላጊ ክፋቶች ናቸው። የደካማ ልህቃን ውጤቶች የሆኑት ክፋቶች እግር አውጥተው በማህበራዊ መገናኛዎች (face book, Twitter, etc) ሲረጩ መልካምነትን፣ አስተዋይነትን፣ መቻቻልን፣ መተጋገዝን፣ መግባባትን፣ ወዘተ፣ እንደ አንጨቆረር (black hole) ውጠው ያስቀራሉ።

በአፍሪካ ውስጥ ከላይ ከተመለከትናቸው ዓይነት ልህቃን (elite) ይልቅ ተቻችሎ አብሮ የሚኖረው ሕዝብ ብርቱና ዘመን ተሻጋሪ ነው። እንደ ተኩላ የሚያቅበዘብዘው የፖለቲካ ስግብግብነት (political greediness) ከድንፋታ (anger)ጋር ተዛምዶ የገዛ ወገኑ ላይ ክፉና አስፈሪ አውሬ (evil dragon) ሆኗል። ስግብግብነት ድንቁርናን ያብሳሉ፣ በባዶ ትርክት ያንደፋድፋሉ፣ ግጭት ይፈጥራሉ። ልህቃን ስግብግብ፣ ቁጠኛ፣ ተኩላ፣ ክፉ አውሬ ሲሆኑ የሚያሸንፋቸው ተፈጥሮ ባደለው የመቻቻል ዴሞክራሲ የሚኖረው አስተዋዩ መልካም ሕዝብ ነው።

አፍሪካውያን ዴሞክራሲያችንን ከማህበራዊው የመቻቻሉ ዴሞክራሲ ልንጀምር ይግባል። መልካም የሆኑ ልህቃን የግብረገብ ፍሬ የሆኑትን መቻቻል፤ መቀባበል፣መከባበርን ለብሰው የሕዝቡ አብሮነት ባህል ላይ ቢሰሩ የፖለቲካ ተሳትፎ ያድጋል። ልህቃን የፖለቲካ ፓርቲ ከመመስረቱ በፊት ልበ ሠፊ፣ ታጋሽ፣ ትሁት፣ አርቆ አሳቢ መሆኑን ሊመረምር ይገባል። አስተዋይነት በሂደት ታድጋለች። ይበልጥ አስተዋይ የፖለቲካ መሪ በእርሱ ምክንያት ሕዝብ እንዳይጎዳ አስቀድሞ ይጠነቀቃል። ሁላችንም ቂም በቀል ቀብረን ወደፊት ልንጓዝ ይገባል።

በሃገራችን ውስጥ በርካታ ቤተ ክርስትያኖች፣ መስጊዶች፣ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ይታያሉ። የአማኙና የተማረው ሰው ብዛት ካልተማረውና ከማያምነው ሰው ብዛት ይበልጣል። የኃይማኖት አስተማሪዎች፣ ቀዳሾች፣ አገልጋዮች፣ ዘማሪዎች ብዙ ናቸው። የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች፣ የዜና ሥርጭቶች እንደ አሸን ፈልተዋል። የምዕራቡን ዓለም ዴሞክራሲ የቀመሱ በርካታ ስደተኞች ተመልሰዋል። እነሆ ታድያ ግብረገብና ሥነምግባር እንደ ኦክስጂን እስትንፋሶቻችን በሆኑ ነበር። ቤተክርስትያኖች፣ መስጊዶች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመልካም ምሁራን፣ የጀግኖች፣ የበሰሉ ልህቃን፣ የደጋግና የሕዝብ ተቆርቋሪ ሰዎች መፈጠርያ ካልሆኑ ችግር አለ ማለት ነው። በስድሳዎቹና ከዚያ በፊት በነበሩት ዓመታት ጀግንነት፣ ምሁርነትና አዋቂነት መልክ ነበረው። በኢሕአፓም፣ በመኢሶንም፣ በሌሎችም ድርጅቶች ሁሉ በፖለቲካ የሚሳተፈው ላመነበት ይሞታል እንጂ ጥቅማ ጥምቅሞችን አያባርርም ነበር። በኃይማኖተኛው፣ በአስተማሪውና በመንግሥት አገልጋዩ ውስጥ ግብረገብና ሥነሥርዓት ይንጸባረቁ ነበር። ልያት ልታይ ማለት ነውር ነበር። ስድስተኛንና ስምንተኛ ክፍልን ሚኒስትሪ ማለፍ ጉድ የተባለበት ዘመን አልፎ ዛሬ ማስትሬትና ዶክትሬት ይቸበቸባሉ።

ግብረገብና ሥነምግባር ለምን ተናዱችግሩን መርምሮ መፍትሄ ማምጣት የኃይማኖት አስተማሪዎች፣ የምሁራንና የሃቀኛ ልህቃን ኃላፊነት እንጂ የመንግሥት ብቻ አይደለም።

የኦሮሞ ገዳ ባህላዊና ማህበራዊ ዴሞክራሲ እምቅ ኃብት እንዲሁም ጥንታዊ ሳባዊ እውቀትና ጥበብን ያዘልን – ኢትዮጵያውያን – እንደ አውሮፓው ትላልቅ ካቴድራሎች ከፍ ብሎ የሚታይ ውብ ዴሞክራሲ ለአፍሪካችን ለማበርከት ምን ያንሰናልታላላቅ ሃይማኖቶች ክርስትናንና እስልምናን (ሥነምግባርንና ግብረገብንቀድመን የተቀበልን ሕዝብ፣ አትንኩኝ ባይ ነጻነቱን አፍቃሪ ሕዝብ፣ እንደምን የአፍሪካ ዴሞክራሲ ምሳሌ መሆን ያቅተዋል?

እግዚአብሄር ሃገራችንን ይጠብቅ፣ አሜን

1 Comment

  1. yewah bemidiya yemitsemaw dimocracy wushet new le zegochachew kibir yinorachew yihonal anten

Comments are closed.

Share