የፖፕ ፍራንሲስ እና የፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ መገናኘት ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ ያስችል ይሆን?

መጋቢት 10 ቀን 2008 ዓ/ም

ጋዜጣዊ መግለጫ

የፖፕ ፍራንሲስ እና የፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ መገናኘት ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ ያስችል ይሆን?

ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ – የኢትዮጵያ ጉዳይ (ሕብረቱ) ፖፕ ፍራንሲስ እና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ፤ የካቲት 21 ቀን 2008 ዓ/ም በመገናኘታቸው፤ ለብዙ ዘመን ከቫቲካን ሲጠበቅ የነበረውን ፋሺሽት ኢጣልያን ደግፋ ኢትዮጵያ ላይ ለተፈጸመው የጦር ወንጀል የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ የመጠየቅ ውጤት እንደሚያስገኝ ያለውን ፅኑ ተስፋ ይገልጻል።

በተጨማሪም፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዚያ ከፍተኛ ደረጃ ግንኙነታቸው በመጠቀም ለኢትዮጵያ ስለሚያስፈልገው ፍትሕ ጉዳይ በማንሳት ፋሺሽት ኢጣልያ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከመጨፍጨፏ በላይ 2000 ቤተ ክርስቲያኖች 525000 ቤቶችና 14 ሚሊዮን እንስሶች አውድማ እጅግ ብዙ ከሆኑት የተዘረፉ ንብረቶች ከ500 በላይ የሆኑ ታሪካዊ ሰነዶች በቫቲካን ይዞታ የሚገኙ መሆኑ እንደ ተጠቀሰ ሕብረቱ ተስፋ አለው።

አይሑዶች በናዚ ጀርመኒ ሲጨፈጨፉ ቫቲካን ተቃውሞ ባለማሰማቷ ብቻ ለተፈጸመው የጦር ወንጀል በመደጋገም ይቅርታ ጠይቃለች።በተጨማሪም የአሁኑ የቫቲካን መሪ፤ ፖፕ ፍራንሲስ የላቲን አሜሪካን ሕዝብና ሜክሲኮን ያልተቆጠበ ይቅርታ ጠይቀዋል።

ነገር ግን፤ ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ በመደጋገም አቤቱታ ቢያቀርብም፤ ቫቲካን እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ አልጠየቀችም። በተጨማሪም፤ በሕብረቱ ድረገጽ በ(www.globalallianceforethiopia.org) እንደሚታየው እስካሁን ድረስ ከ30 ሐገሮች በላይ ነዋሪ የሆኑ 4839 ሰዎች የፈረሙት ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ የሚያመለክት አቤቱታ አለ።

ቫቲካን በኢትዮጵያ ላይ የተከናወነውን የጦር ወረራ መደገፏ ታሪካዊ ሐቅ ነው። ለዚህም እውነት ካሉት ማረጋገጫዎች ውስጥ፤ ፖፕ ፓየስ 11ኛ የኢጣልያን ንጉሥ “የኢጣልያ ንጉሥና የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት” በማለት መባረካቸው፤ ቁጥራቸው ብዙ የሆነ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳትና ጳጳሳት ለፋሺሽቱ ጦርነት ወርቃቸውን ማበርከታቸው፤ ካሕኖቻቸው የፋሺሽቱን ጦር መባረካቸው ይጠቀሳሉ። እንዲሁም፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በኢትዮጵያ ላይ የኢጣልያንን የበላይነት እንዲያውቁ ቫቲካን አንድ ሚሊዮን ስተርሊንግ ፓውንድ ጉቦ አቅርባ ተቀባይነት እንዳላገኘች ታውቋል። በቫቲካንና በቤኒቶ ሙሶሊኒ ይመራ በነበረው በኢጣልያ መንግሥት መሀል ስለ ነበረው ቅርብ መተባበር ሌላው ማስረጃ “ላተራን” (Lateran) የተሰኘው በሁለቱ ወገኖች የተፈረመው ውል ነበር። የታራኖ ጳጳስም ፋሺሽቶች በኢትዮጵያ ላይ የፈጸሙትን የጦር ወረራ ቅዱስ ጦርነት (holy crusade) ነው ብለውት ነበር።

ሌላው ተጨማሪና አሳሳቢ ጉዳይ እ.አ.አ. በነሐሴ 2012 (August 2012) ቢ.ቢ.ሲ. (BBC) እንደ ዘገበው፤ የኢትዮጵያ ጨፍጫፊ በመባል ለሚታወቀው የፋሺሽት ወንጀለኛ ለሮዶልፎ ግራዚያኒ፤ አፊሌ በምትሰኝ የኢጣልያ ከተማ አንድ

መታሰቢያ ሲመረቅ የቫቲካን ተወካይ እንደ ተገኙ ተገልጿል። ምንም እንኳ የግራዚያኒ ስም ክመታሰቢያው ስያሜ እንዲወገድ የፍርድ ቤት ውሳኔው ለሐምሌ ቀጠሮ የተያዘበት ቢሆንም የመታሰቢያው ሕንጻ እንዳለ ይገኛል።

የካቶሊክ ካሕን የፋሺሽት ጦሩን ሲባርክ የዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ ዋና ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው፤

(ሀ) ኢጣልያ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በቂ ካሣ እንድትከፍል፤
(ለ) ቫቲካን ከፋሺሽት ኢጣልያ ጋር በመተባበሯ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ፤
(ሐ) የተዘረፉ የኢትዮጵያ ንብረቶች እንዲመለሱ፤
(መ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ላይ ለተፈጸመው የጦር ወንጀል እውቅና እንዲሰጥና

የሚፈለገው ፍትሕ እንዲገኝ ማድረግ፤
(ሠ) ለፋሺሽቱ ወንጀለኛ ለሮዶልፎ ግራዚያኒ የተሠራው መታሰቢያ እንዲወገድ።

ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስፈልገው ፍትሕ እንዲገኝ ለማድረግ፤ ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ ለኢጣልያ መንግሥት፤ ለቫቲካን፤ ለሌሎች መንግሥታት እና እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ የአውሮፓ አንድነት ድርጅት፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ላሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አቤቱታዎቹን አቅርቧል።

ሕብረቱ በፍትሕ ለሚያምኑ ሰዎችና ድርጅቶች ለዘመናት ሲጠበቅ የነበረው ለኢትዮጵያ የሚገባው ካሣ፤ ንብረት መመለስና ይቅርታ መጠየቅ በተቻለ ፍጥነት እንዲከናወን ያልተቆጠበ ድጋፋቸውን እንዲያበረክቱ ያሳስባል።

የፖፕ ፓየስ 11ኛ ተወካይ፤ ካርዲናል ጋስፓሪ እና ሙሶሊኒ የ”ላተራን” ውሉን ሲፈራረሙ

ለተጨማሪ መረጃ ከዚህ ቀጥሎ በተዘረዘሩት ይጠቀሙ፤ (www.globalallianceforethiopia.org)

E-mail: [email protected] Address:

4002 Blacksmith Drive Garland, TX 75044 USA

Phone: (214)703 9022