ይድረስ ለኔልሰን ራህላሂላ ማንዴላ!

(ቴዲ – አትላንታ)

ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ሰማሁ። ታዲያ እስከዛሬ ስንቀራፈፍ ልነግርዎት ያሰብኩትን ሳልነግርዎ ነገር ቢበላሽ ጸጸት እንዳይሰማኝ ስል፣ በህይወት እያሉ ይቺን ጦማር ልልክልዎ ወደድኩ። ሆስፒታልዎ ውስጥ፣ አልጋዎ አጠገብ ደርሳ ያዩዋታል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ። ካልሆነም በመንፈስዎ ስሜቴ ይድረስዎ!

ውድ ማዲባ …! ምናልባት እርስዎ ለመላው ጥቁር ህዝብ ኩራት፣ ለመላው ህዝብ (ነጩንም ጨምሮ) ደግሞ ታላቅ አስተማሪ መሆንዎን አያውቁ ይሆናል። ብዙ ጊዜ ሲናገሩ “ምንም የስራሁት የተለየ ነገር የለም” ሲሉ ስለምሰማ ነው ይህን ማለቴ።

ከዚህ በላይ ምን ሊሰሩ ኖርዋል? መረገጥና መዋረድን አሻፈረኝ አሉ፤ ለዘረኞች አጎንብሰውና እጅ ስመው በብርሃን ማደር ሲችሉ፣ ከዚህ ይልቅ ውርደትን ተቃውሜ ጨለማ እስር ቤት ብገባ ይሻለኛል አሉ። በ27 ዓመት የእስር ጊዜዎ አንዴ ሮቢን ደሴት፣ አንዴ ፖልስሞር እስር ቤት፣ አንዴ ቪክቶር ቨርስተር እስር ቤት ሲያንገላቱዎ፣ እርስዎ ግን “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ከማለት ውጪ ሊበቀሏቸው እንኳን አልተመኙም።

በምን አወክ አሉኝ? ከእስር ከወጡ በኋላ ያደርጉትን የተመለከተ ሰው ሁሉ ያንን መገመት ያቅተዋል ብለው ነው? እርስዎን ሁላችንም የምንወድዎትና የምናደንቅዎት እኮ ሃያ ሰባት ዓመት እስር ቤት ስለታሰሩ አይደለም – ለነጻነታቸው ሲሉ የታሰሩ እጅግ ብዙዎች አሉና! … ዘረኝነትን ስለተቃወሙም አይደለም – ዘረኝነትን ድሮም ዛሬም የሚቃወሙ አሁንም አሉና ! …. ጥቁር የነጻነት ታጋይ ስለሆኑም አይደለም – ማርክስ ጋርቬይና ማርቲን ሉተር ኪንግን ጨምሮ በርካታ ጥቁር የነጻነት ታጋዮች እንዲሁ ሞልተዋልና !!

የምንወድዎና የምናደንቅዎ ፣ ትግልዎ ፍሬ አፍርቶ ከእስር ከወጡ በኋላ እርስዎን ያሰሩትን ሰዎች መልሰው በማሰር፣ እርስዎን የገረፉትን መልሰው በመግረፍ፣ እርስዎን ያዋረዱትን መልሰው በማዋረድ “አሸናፊ” ለመምሰል ባለመሞከርዎ እንጂ! …. እርስዎን ከሌላው የሚለይዎና ዛሬ በጥቁሩም በነጩም በክልሱም ሞገስና ክብር ያስገኘልዎ እርስዎን ጨለማ ቤት 27 ዓመት ያሰሩትን ሰዎች መልሰው በመሾም የበቀልን ባቡር በማቆምዎ ነው! ….. እርስዎን በጥፊ የመቱ እጆችን በመጨበጥ የይቅርታን ታላቅነት በማብሰርዎ ነው ! …. እግርዎ ላይ ሰንሰለት ያጠለቁትን ሰዎች እግር ነጻነት ሰጥተው “ሂዱ ተራመዱ” በማለትዎ ነው ! “ያለፈውን እንርሳው .. የወደፊቱን እንመልከት .. እኛ ጥቁሮቹም፣ እናንተ ነጮቹም የደቡብ አፍሪካ ልጆች ነን .. አንድ ጊዜ ተሳስተን ነበር፣ አሁን የናንተን ስህተት እኔ መድገም አልፈልግም .. አለበለዚያ የነጭን ዘረኝነት በጥቁር ዘረኝነት ብቀይር ከናንተ ምኑን ተሻልኩት? ይቅር ብያችኋለሁ” በማለትዎ ነው እንጂ !!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስ ለሚኒሶታ መድኃኔዓለም ምዕመናን፡ የተከፋፈሉት አባቶች 1 አስኪሆኑ ድረስ በአስተዳደር ገለልተኝነት ለመቆየት 7 ምክንያቶች

አርቀው ማሰብ ስለቻሉ የዛሬዋን ሳይሆን የነገዋን ደቡብ አፍሪካ በበቀል ሳይሆን በይቅርታ፣ በቁርሾ ሳይሆን በመቻቻል፣ በጉልበት ሳይሆን በመወያየት ፣ በእልህ ሳይሆን በትግስት መሰረት ላይ እንድትመሰረት አደረጉ። እንዲህ ባያደርጉማ ስልጣኑን ያገኘ ሁሉ የቀደመውን እያሰረ ፣ የእስር ታሪክ በነገሰ ነበር። እርስዎ ግን ነጻነትና እርቅን ፈትተው እስርን ራሱ አሰሩት። ለዚህ ነው ሁላችንም የምንወድዎት።

ውድ ማዲባ .. እርስዎ በጣም ዕድለኛ ነዎት! ምክንያቱም ፈጣሪ ከዚያ ሁሉ መከራና ስቃይ በኋላ 94 ዓመት ሰጥቶዎታል። በጨለማ ቤትና በቀዘቀዘ ሲሚንቶ ላይ አንድ ሳምንት እንኳን ማደር እንዴት ተስፋ እንደሚያስቆርጥ ይታወቃል። 27 ዓመት እግር ተወርች ሲታሰሩ ፣ የርስዎ መታሰር ሳይሆን የጥቁር ወገኖችዎ መንገላታት ይበልጥ ያስጨንቅዎ እንደነበር የህይወት ታሪክዎን በጻፉበት መጽሃፍ ገልጸውታል። እርስዎ ግን ከዚያ ጨለማ ወጥተው ፣ ድሮ እርስዎን ያንቋሽሹና ይንቁ የነበሩ ሁሉ ዛሬ የርስዎን ቲሸርት ለብሰው፣ ዛሬ ለህይወትዎ ሲጨነቁ በዓይንዎ አይተዋል። ታዲያ ይህ ዕድለኛ አያሰኝዎትም?

እኛ ኢትዮጵያውያንም ለርስዎ የተለየ ክብር አለን። እርስዎም አገራችንን እንደሚወዱ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተናገረዋል፣ አገራችንንም መጥተው አይተውልናል። አንድ ነገር ግን – እንደው ነፍስዎ ሳትወጣ ቢመክሩን ደስ ይለኛል … “እኔን ከወደዳችሁ እኔ ያደረኩትን አድርጉ” ይበሉን።

ባህላችን ሆኖ በአገራችን ሰው ከሞተ በኋላ ነው ስለሱ ጥሩ ጥሩ ነገር የሚነገረው። አንዳንዴማ መቼም አንዴ ሞቷል ተብሎ የሌለ ሙገሳ ሁሉ ይቀርባል። ራሱ ሟች ቢሰማ ሳይታዘበንም አይቀር! . በህይወት እያሉ መሞገስ የሚገባውን ማሞገስ ይገባል። እርስዎም ለርስዎ ያለንን ስሜት ነፍስዎ እያለች እንዲያውቁልን እንፈልጋለን። በህይወት እያሉ የሌለ ሙገሳ በመጻፍ አንብበው እንዲታዘቡን ስለማንፈልግ የምንጽፈው የልባችንን ነው ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የህወሓት ገመና ሲጋለጥ:- ሰብአዊ መብቶች ያልተከበሩበት የልማት ጎዳና ጥቅሙ ለጥቂቶች ብቻ ነው - አክሎግ ቢራራ (ዶ/ር)

በጣም የሚደንቀኝን ነገር ልንገርዎት። ከዚያ ሁሉ እስርና መከራ በኋላ፣ ነጻ ወጥተው እንደሁለተኛ ዘር የተቆጠሩበት አገር ፕሬዚዳንት ሆኑ። በጉልበትና በጠመንጃ ሳይሆን ተመርጠውና ሁሉም ለይኩን ለይኩን ብሎ ነው የሾመዎ። ታዲያ ያን ያህል የተሰቃየ ሰው ሥልጣን ከያዘ በኋላ በቀላሉ ይለቃል እንዴ? በአፍሪካ አይተን አናውቅም። እርስዎ ግን ያንኑ ሥልጣን እንኳን ከ 5 ዓመት በላይ ሊቆዩበት አልፈለጉም። በቃኝ አሉ። አሁን ይህን ማን ያደርጋል? .. ለደንቡማ ቢሆን ብዙዎች ከርስዎ መማር ነበረባቸው .. ግን ሩቅ ሳንሄድ፣ ጎረቤትዎ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ይኸው ከርስዎ ብዙም የማያንስ ዕድሜ ላይ ሆነው ሥልጣን ሙጥኝ ብለው የለም እንዴ? ኮሎኔል ጋዳፊና ፕሬዚዳንት ሙባረክስ 40 ዓመት ሙጥኝ ማለታቸው ምን እንዳመጣባቸው ይታወቅ የለ? እባክዎ ለአፍሪካ መሪዎች እንደው ህይወትዎ ሳያልፍ አንዲት ምክር ጣል ያድርጉልን!

አልጋዎ ላይ እንዲህ ደክመው ብዙ በመጻፍ፣ በንባብ ላደክምዎ አልፈልግም ፣ እንደው እስከዛሬ ከለፉት የበለጠ አይሆንምና ለመጨረሻ ጊዜ ቅድም የነገርኩዎትን ቃል አንዴ ብቻ ይድገሙልን .. እንዲህ በሉልኝ … “እኔን የምትወዱ ሁሉ ፣ እኔ ያደረኩትን የማታደርጉ ከሆነ መውደዳችሁ ምን ዋጋ አለው? ” !! ..

ውድ ማዲባ! እርስዎ በ1994 ፕሬዚዳንት ሆነው ሥልጣን በያዙ ጊዜ እርስዎን ያሰሩትን ሰዎች መልሰው ቢያስሩ ኖሮ፣ የገረፉዎትን ሰዎች መልሰው ቢገርፉ ኖሮ፣ .. ንብረትዎን የቀሙትን መልሰው ንብረታቸውን ቢቀሟቸው ኖሮ ..፣ በጥቁርነትዎ ያዋረዱዎትን ነጮች መልሰው ሥልጣን ስላገኙ ብቻ በነጭነታቸው ቢያዋርዷቸው ኖሮ፣ ትናንት ደቡብ አፍሪካ የነጮች ብቻ ነበረች፣ ዛሬ ግን የጥቁሮች ብቻ ሆናለች! ብለው ቢያውጁ ኖሮ፣ … እስከዛሬ የተበደላችሁ ጥቁሮች፣ ዛሬ እኔ ጥቁሩ ፕሬዚዳንት ሆኛለሁና የበደሏችሁን ነጮች ሁሉ ልክ ልካቸውን አስገቧቸው ብለው ቢሆን ኖሮ ፣ .. 27 ዓመት በጨለማ እስር ቤት ያቆዩዎትን ነጮች በሉ እኔ የቀመስኩትን ጨለማ እናንተም ቅመሷት የታባታችሁ ቢሉ ኖሮ ….. .. ደቡብ አፍሪካም የዛሬዋ ደቡብ አፍሪካ ባልሆነች .. እርስዎ ማንዴላም ዛሬ ያገኙትን ክብርና ውዳሴ ባላገኙ .. እኔም ይቺን ደብዳቤ ለርስዎ ባልጻፍኩ ነበር።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሱዳን ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውይን ስደተኞችን በተመለከተ የተጠናቀረ 3 ኛ ጹሁፍ ነው ።

ፈጣሪ የፈቀደውን ያህል ዕድሜ እንዲጨምርልዎ እመኛለሁ። ጤንነትዎ ተስተካክሎ ያለስቃይ በደስታ ለዘላለም ቢኖሩም እወዳለሁ። ያ ካልሆነም በህይወትዎ የሰሩት ሥራ የሚያኮራዎ፣ ነጩም ጥቁሩም ክልሱም የሚያወድስዎ፣ ቢሻልዎት የሚደሰትልዎ፣ ባይሻልዎትም የሚያለቅስልዎ ነው። እንወድዎታለን።

(ጸሃፊው የድንቅ መጽሔትና የአድማስ ሬዲዮ አዘጋጅ ናቸው – ይህ መጣጥፍ በሚሰሩበት ሚዲያ ስም ሳይሆን በግላቸው የተጻፈ፣ የግላቸው ሃሳብ ነው)

1 Comment

  1. Ejeg yemiyasdest melekt!!! L-Jawar newe lemibalew tebabem lakulet-na yanbebew!!! Mechem awko yetegnan…. newe negeru

Comments are closed.

Share