የኢሳት ማኔጅመንት የሃዘን መግለጫ – አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ ሃያሲ፣ ደራሲና፣ የፖለቲካ ተንታኝ ሙሉጌታ ሉሌ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው

አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ ሃያሲ፣ ደራሲና፣ የፖለቲካ ተንታኝ ሙሉጌታ ሉሌ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው የኢሳት ማኔጅመንት፣ ጋዜጠኞችና መላው የኢሳት ቤተሰብ ከፍተኛ ሃዘን ተሰምቶታል። አቶ ሙሉጌታ ሉሌ በተባ ብዕራቸው ሃገራዊ ፍቅርን፣ አንድነትንና ነፃነትን የሰብኩ፥ በአንደበታቸው ስለኢትዮጵያ የመሰከሩ፣ እስከመጨረሻ እስትንፋሳቸው ድረስ ኢትዮጵያን ያገለገሉና፣ ኢትዮጵያን ተቀምተው በስደት የቀሩ ሃገራዊ ሃብት ነበሩ።

የሙያ አባታችን ሙሉጌታ ሉሌ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ (ኢሳት) ዛሬ ለደረሰበት ደረጃና ህዝባዊ ተቀባይነት ያደረጉት ጉልህ አስተዋፆና የፈጠሩት ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ በኢሳት ማኔጅመንት፣ ጋዜጠኞችና ደጋፊዎች ዘንድ ሁሌም ደምቀው ሲታሰቡ ይኖራሉ። አንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ በመነንና በጦቢያ መፅሔቶች እንዲሁም በኢሳት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ አገልግለዋል። በዚህም ስለሰው ልጅ መብት፣ ስለፍትሃዊነት፣ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲያዊነት ያለመታከት ሲያስተምሩ ኖረዋል፥ዛሬ ስለነጻነት የሚሰብከው አንደበት ቢዘጋም፣ እውነትና እውቀት የሚዘራው ብዕር ቢነጥፍም፣ ስራቸው ህያው ሆኖ ከመቃብር በላይ እሳቸውን ሲያስታውሰን ይኖራል።

ሙሉጌታ ሉሌ እስከመቃብር ደጃፍ የተናገሩላት እና የመሰከሩላትን ሃገራቸው ኢትዮጵያን በነጻነት የማየት ህልማቸው ፍጻሜ ሳያገኝ፣ አጽማቸው ጭምር በባዕድ አገር መቅረቱ የሚያሳዝንና የሚያስቆጭ ቢሆንም እርሳቸው ግን ያለ ህሊና ወቀሳ በክብር ሄደዋል።የጀመሩትን ፍጻሜ ማድረስ የእኛ እዳ ሆኖ ይቀጥላል።የአንጋፋው ብዕረኛ ሙሉጌታ ሉሌ ርዕይ የሆኑት ነጻነትና ፍትህ በኢትዮጵያ እውን ሲሆኑ፣በቁጭት የሸኘነውን አጽም በክብር አንስተን ለሃገሩ አፈር ልናበቃው ቃል እንገባለን። በዚህ አጋጣሚ ቤተዘመዶች፣ ወዳጆቹና፣ አድናቂዎቹ ሁሉ ለደረሰባችሁ መሪር ሃዘን መጽናናት እየተመኘን በዚህ ቃልኪዳን ከጎናችን እንድትሆኑ ጥሪ እናቀርባለን።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለአቶ ዓለማየሁ አቶምሳ ፍትሃትና ሽኝት ሲባል ቅዳሴ መቋረጡ ምዕመናኑን አሳዘነ

የኢሳት ማኔጅመንት፣ ጋዜጠኞች እና መላው የኢሳት ቤተሰብ

መስከረም 26/2007

1 Comment

  1. ኢሳያስ ደግሞ ምን ነካው አስመራ ላይ የክብር ቀበራ አያደርግለትም አንዼ?

Comments are closed.

Share