ከአሥር ወራት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ያጡ የፍቼ ነዋሪዎች ሰላማዊ ሠልፍ ሊወጡ ነው

June 22, 2014

ካህናትና የነዋሪዎች ተወካዮች ዋና መሥሪያ ቤቱን ተማፀኑላለፉት አሥር ወራት ከኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ኩራዝ ብርሃን ለመመለስ ተገደናል ያሉ በኦሮሚያ ክልል የፍቼ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች፣ ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ለከተማው አስተዳደር ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታወቁ፡፡

ነዋሪዎቹ ሠልፍ እንደሚወጡ የከተማውን አስተዳደር መጠየቃቸውን የገለጹት፣ ነዋሪዎቹን ወክለውና የከተማውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት አባቶችን ልብሰ ተክህኖ በመልበስና ሌሎች የሃይማኖት ተወካዮች እንደእምነታቸው ለብሰው፣ ፒያሳ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የደንበኞች አገልግሎት መስጫ ተገኝተው ቅሬታቸውን ባሰሙበት ወቅት ነው፡፡

የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች ላለፉት አሥር ወራት የኤሌክትሪክ ኃይል አጥተው መክረማቸውን የመሥሪያ ቤቱ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት እማኝ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ከፍቼ እስከ አዲስ አበባ ከተማ ያሉትን ቢሮዎች ቢያዳርሱም፣ አንዱ ወደ ሌላኛው ቢሮ እንዲሄዱ ከመንገር ባለፈ የፈየዱላቸው እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ ብሶታቸው እየባሰ በመምጣቱና ከመንግሥት አንድ ቁርጥ ያለ ምላሽ ማግኘት እንዳለባቸው በማመናቸው፣ ሁሉንም የከተማውን ነዋሪዎች በመወከል ከ25 የሚበልጡ ተወካዮች በዋናው መሥሪያ ቤት ተገኝተው ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

‹‹ጥያቄያችን የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ ነው፤›› ያሉት ነዋሪዎቹ፣ ለብዙ ጊዜያት በኤሌክትሪክ ኃይል መጠቀም የለመዱ ነዋሪዎች እንደገና ወደኋላ በመመለስ በኩራዝና በማገዶ እንዲጠቀሙ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑንና በተለይ በዕድሜ የገፉ እናቶችና ጨቅላ ሕፃናት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው የመንግሥት አካል መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ በመሥሪያ ቤቱ የተለመደው ምላሽ ‹‹ትራንስፎርመር አልተገዛምና የለም›› መሆኑ ማብቃት ስላለበት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መስጫ መሥሪያ ቤት አንድ ኃላፊ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ሁለት ሰው ይበቃ ነበር፣ ብዙ በመሆናችሁ ቅር ብሎኛል፡፡ እኛ እናንተን ማገልገል እንጂ ሌላ ዓላማ የለንም፡፡ ከእኛ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት አንድ ሰውና ከእናንተ አንድ ሰው ይበቃ ነበር፡፡ ወይም በወረቀት ደብዳቤ ብትጽፉም በቂ ነበር፡፡ ሁለተኛ እንዳይደገም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ችግሩን አጣርተው መፍትሔ ምላሽ እንደሚሰጡም ተናግረዋል፡፡

እንደ ፍቼ ነዋሪዎች ለአሥር ወራት የቆየው የኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋት ችግር ባያጋጥምም፣ ከአምስት ቀናት እስከ አንድ ወር ድረስ የኃይል መጥፋት ችግር የሚያጋጥማቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም በተለያየ መንገድ እሮሮ እያሰሙ ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ በሁሉም ክፍላተ ከተሞች በተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ኃይል እየጠፋ እንደሆነ ራሱ መሥሪያ ቤቱ ምስክር እንደሚሆን፣ እንደማይጠራጠሩ ስድስት ኪሎ የካቲት 12 ሆስፒታል አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ትዕግሥት በላቸው በእርግጠኝነት ይናገራሉ፡፡

ወ/ሮ ትዕግሥት የኤሌክትሪክ ኃይል በተከታታይ ለአራት ቀናት ካልጠፋ ‹‹የዓባይ ግድብ ደረሰ መሰለኝ፣ ተመስገን ያለምንም ችግር ጨለማ ሳይውጠን ከረምን፤›› እስከማለት መደረሱን ተናግረዋል፡፡

ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል እስከ ሾላ ገበያ ድረስ ያሉ ነዋሪዎች ለዘጠኝ ተከታታይ ቀናት የኤሌክትሪክ ኃይል በማጣታቸው ‹‹የዓለም ዋንጫ ለኛ ሲባል ሊደገም ነው አሉ…›› እያሉ በችግሩ ላይ ማሾፍ መጀመራቸውንም ወ/ሮ ትዕግሥት አንድ ዘመዳቸውን ለመጠየቅ በሄዱበት ወቅት መታዘባቸውን ጠቁመዋል፡፡

እንደነ ወ/ሮ ትዕግሥት አካባቢ ሁሉ በሽሮሜዳ፣ በፒያሳ፣ በሜክሲኮ፣ በቃሊቲ፣ በአቃቂ፣ በጎተራ፣ በቦሌ፣ በኮተቤ፣ በአስኮ፣ በላፍቶ፣ በልደታና በሌሎች አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ጉዳይ አነጋጋሪ ብቻ ሳይሆን ጥያቄም እያስነሳ መሆኑን ነዋሪዎች እየገለጹ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለሁለት መከፈሉ ይፋ ከተደረገ አንድ ዓመት ሳይሞላው እየተፈጠሩ ያሉት ችግሮች፣ ነዋሪዎችን ግራ እንዳጋቡ የሚገልጹ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚቋረጠው ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ወይስ ከእኛ ከገዙት ጁቡቲና ሱዳንም?›› በማለት ጥያቄ እያሰኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ሁለት ቦታ ተከፍሎ የሠራተኞች ምደባ እንደ አዲስ መደረጉ ለችግሩ ዋና ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ በተለይ የአገልግሎት ዘርፉን የተረከበው የህንዱ ኩባንያ ሥራውን በአግባቡ እየተወጣው አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ነባር ሠራተኞች ሥራውን በደንብ የሚያውቁት ቢሆንም፣ በተደረገው አዲስ የመዋቅር ለውጥ ድልድል ሳያኮርፉ እንዳልቀሩ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች፣ የሚመለከተው አካል ይኼንን ሁኔታ በደንብ አጥንቶ አስቸኳይ መፍትሔ ካልሰጠው፣ ችግሩ የከፋና ውጤቱም አደገኛ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል፡፡ የአገልግሎት ዘርፉን ከሚመራው የህንዱ ኩባንያ ጋር የሥርጭት ዘርፉን በኃላፊነት የሚመሩት የሥርጭት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቢትወደድ ገብረ አሊፍን ለማነጋገር ቢሞከርም ስልካቸውን ስለማያነሱ አልተሳካም፡፡

Source: Ethiopian Reporter

Previous Story

ፀረ ሙስና ኮሚሽን የምድር ባቡር የድሬዳዋ ኃላፊዎችን በቁጥጥር ሥር አዋለ

10478183 742597102465708 4057302345624676295 n
Next Story

አንድነት ፓርቲ በሀዋሳ ሊያደርገው የነበረው ሰልፍ አመራሮችንና አባላትን በማሰር ከተማዋን በፀጥታ ኃይሎች በመውረር ተደናቀፈ

Latest from Blog

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ | አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ | አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል | ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ\  አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

ከመጠምጠም መማርን እናስቀድም!

;በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) አብዛኛው አንባቢ ተገንዝቧል ብዬ እንደምገምተው ሕዝብ ለቡና ቲራቲም፣ ለግብዣ፣ ለበዓል፣ ለሰረግ፣ ለሐዘን፣ ለእድር፣ ለእቁብ ለውይይትና ለሌሎችም ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ሲገናኝ የሚበዛው አድማጭ ሳይሆን ተናጋሪ  ወይም ደግሞ ለመናገር  መቀመጫውን ከወንበር ወይም
Go toTop