በሰበታ ባለቤቱን ዓይኗን ረግጦ በሰንጢ ሆዷን የቀደደው ግለሰብ ተያዘ

ባለቤቱን በተለያዩ የሰውነት ክፍሏ ላይ በአሠቃቂ ሁኔታ በስለት ወግቶ የመግደል ሙከራ ያደረገው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋሉን የሰበታ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ማስታወቁን የኢትዮጵያ ፖሊስ ሚድያ አታወቀ፡፡

(amharic.zehabesha.com)

በሰበታ የክፍለ ከተማ ሁለት ፖሊስ ጣቢያ የወንጀልና የትራፊክ አደጋ መርማሪ ም/ሣጅን ስለሺ በቀለ እንደገለፁት ተጠርጣሪው ተበዳይን ወ/ሮ ጫልቱ ጎበናን ግንቦት 13 ቀን 2006 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ በሰበታ ከተማ 05 ቀበሌ ልዩ ቦታው ዲማ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ‹‹ብር እንድትሰጪኝ እፈልጋለሁ›› በሚል እና በመጠጥ ኃይል ተገፋፍቶ እንቢተኝነቷን ሰበብ በማድረግ በተኛችበት አንገቷን ከአነቃት በኋላ ስትፈራገጥ ቀኝ አይኗን ረግጧት በያዘው ሰንጢ ሆዷን ከላይ እስከ ታች በመቅደድ እንዲሁም በክንዷ እና ትከሻዋ ላይ በተመሣሣይ ሁኔታ በመውጋት ትንፋሿ አለመኖሩን አረጋግጦ ከጣላት  በኋላ እጁን ለፖሊስ ሰጥቷል፡፡


እንደ ም/ሣጅን ስለሺ ገለፃ ተበዳይዋ ጉዳቱ እንደደረሰባት ቤተሰቦቿ ወዲያውኑ ሆስፒታል የወሰዷት ሲሆን ከብዙ  የህክምና ጥረት በኋላ ሕይወቷ ሊተርፍ ችሏል፡፡  ተከሳሹ በአሁን ሰዓት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራው እየተጣራበት መሆኑንም ም/ሣጅን ስለሺ አያይዘው ገልፀዋል፡፡ 

ም/ሳጅን ስለሺ በመጨረሻ በአስተላለፉት መልዕክት ተከሳሽ ከተበዳይ ጋር በትዳር አለም የቆዩት ለሁለት ወር ብቻ ነበር ስለዚህ በመሃላቸው መጠናናትና መተዋወቅ የለም በዚህም ለእንዲህ ዓይነቱ አደጋ ተጋልጠዋል ሲሉ መርማሪው መግለጻቸውን የፖሊስ ሚዲያ መረጃ ያመለክታል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ባህርዳር ከተማ ሁለት ዓይነት የተቃውሞ ሰልፎችን አስተናግዳለች

2 Comments

Comments are closed.

Share