Sport: ከውቡ የብራዚል እግርኳስ በስተጀርባ ብዙ ያልተባለለት የደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ገመና

– ሴሌሳኦ በነጭ ተጨዋቾች ብቻ እንዲገነባ ይፈለግ ነበር
– ደሃው ማህረሰብ ተገቢው ትኩረት አይሰጠውም

ፔሌን ጨምሮ በርካታ ጥቁር የቆዳ ቀለም የነበራቸውን ተጨዋቾች በስብስቡ ያካተተው የብራዚል ብሔራዊ ቡድን በ1958 የዓለም ዋንጫ አሸነፈ፡፡ ድሉ ለብራዚል በታሪክ የመጀመሪያዋ ነበር፡፡ ከድሉ በኋላ ፀሐፊ ተውኔት ኔልሰን ሮድርጌስ ‹‹አንዲት ጥቁር ሴት ተመለከትኩ፡፡ ሴትየዋ የጭርንቁስ መንደር ነዋሪ ነበረች፡፡ ነገር ግን የብራዚላውያን ድል ለወጣት፡፡ አንገቷን ቀና አድርጋ በታላቅ ግርማ እና ደማምነት በጎዳናዎች ላይ ተመላለሰች፡፡ ለጥቁሩም ሰው ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነበር፡፡ ማራኪነቱ እና አስተዋይነቱ በቅፅበት ከኢትዮጵያውያን ልዑል ጋር ተመሳሰለ›› ሲል ፅፏል፡፡ ብራዚልም ከዚያ በኋላ ከሌሎች ሃገራት የተለየች ሆነች፡፡

እግርኳስ ብራዚል ብሔራዊ ማንነቷን እንድትገነባ አግዟታል፡፡ ብዙም እውቅና ያልነበራት ሀገር እንድትጎላ አስችሏል፡፡ እግርኳስ የብራዚልን ውበት፣ አስከፊ ገፅታ እና ብዙውን ጊዜ ችላ የሚባለውን የድሆች ህይወት ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል፡፡ በእርግጥ ብዙው የብራዚል እግርኳስ ታሪክ ሴቶችን ያገለለ ነው፡፡ ያም ቢሆን ግን ተፅዕኖውን አሳንሰን እንድናይ አያደርገንም፡፡ ግን እግርኳስ ስለ ብራዚል የሚገልፀው ምንድነው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ ከዚህ የተሻለ ጊዜ ያለ አይመስልም፡፡ ምንም እንኳን ብራዚል የዓለም ዋንጫን አምስት ጊዜ በማንሳት ቀዳሚ ብትሆንም ፈር ቀዳጅ ከሆነው ከጃኔት ሌቨር የማህበረሰብ ጥናት ውጤት ‹ሶከር ማድነስ› እና የአሌክስ ቤሎስ ‹ፉትቦል የብራዚላውያን የኑሮ ዘይቤ› (Futeball: the Brazilian way of Life) ከተሰኙት ሁለት መፅሐፍት በስተቀር በእንግሊዝኛ ተፅፎ የሚገኝ ሰነድ የለም፡፡ አሁን ብራዚል የዓለም ዋንጫውን ለማስተናገድ ሽር ጉድ እያለች ነው፡፡ በርካታ መፅሐፍትም ለገበያ በመቅረብ ላይ ናቸው፡፡ ከሁሉም ጎልቶ የሚመወጣው ግን የአንድሪያስ ካምፓማር ጥረት ነው፡፡ ኡራጓዊው የሚሰራው በለንደን በሚገኝ አሳታሚ ድርጅት ውስጥ ነው፡፡ ካምፓማር ብዙውን ጊዜውን በቤተ መፅሐፍት ያጠፋ ነበር፡፡ የደቡብ አሜሪካን እግርኳስ ታሪክን ጠንቅቆ በማወቁም ጥልቅ መረጃ ለመስጠት አልተቸገረም፡፡ ነገር ግን አብዛኛው አገላለፁ ከዘመነ ኢንተርኔት በፊት እንደነበረው የታጨቀ እና አሰልቺ ስሜት አለው፡፡ የተዘነጉ ጨዋታዎችን፣ የተረሱ የውድድር ዘመናትን እና ቶርናመንቶችን አንድ በአንድ ተርኳቸዋል፡፡ ምንም የተወው መረጃ የለም፡፡ ያም ሆኖ ካምፖማር የብራዚላውያንን ታሪክ ያቀረበው ከጠቃሚ አህጉራዊ አውድ አንፃር ነበር፡፡ ብሪታኒያ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በደቡብ አሜሪካ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ነበራት፡፡

እግርኳስም ቢሆን በአህጉሩ እንዲስፋፋ የወቅቱ ልዕለ ሃያል ሚና የጎላ ነበር፡፡ ነገር ግን በአርጀንቲና እና ኡራጓይ ካደረገችው አስተዋፅኦ አንፃር በብራዚል እግርኳስን ለማስፋፋት ያደረገችው ጥረት ዘገምተኛ እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡ ብራዚል ሌሎቹ የደረሱበት ለመድረስ ጥረት የጀመረችው በ1920ዎቹ ገደማ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በዚያን ወቅት እንኳን በዘር ማጥፋት እና ባርነት ላይ በተገነባችው አገር የበላይ የነበሩ ነጮች ጥቁሮች በጨዋታው እንዲሳተፉ አይፈቅዱም ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ሴሌሳኦ በነጭ ተጨዋቾች ብቻ የተገነባ እንዲሆን ይፈልጉ ነበር፡፡ ምክንያቱም ደግሞ የተቀረውን ዓለም በብራዚል ባለው የዘር ንፅህና ለማስደመም ነበር፡፡ ለ1950ው የዓለም ዋንጫ ሽንፈት እንኳን እንደ ምክንያት የተጠቀሰው ጥቁሩ ግብ ጠባቂ ባርቦሳ ነበር፡፡ ኡራጓውያን ድሉን ‹ማራካኛዞ› ብለው ይጠሩታል፡፡ ሌሎችም ያልታሰበ አሸናፊነትን ለመግለፅ ይህንን ቃል ሲጠቀሙበት ይደመጣሉ፡፡ አንዳንድ ብራዚላውያን ፀሐፊዎችም አጋጣሚውን ከ‹‹ዎተርሉ›› እና ‹‹ሂሮሺማ›› ጋር አነፃፅረውታል፡፡ በ1962 ብራዚል ‹‹የእግርኳስ አገር አልነበረችም፡፡ ነገር ግን በተቀረው ዓለም የምትታወቀው ለእግርኳስ ባላት ፍቅር ሆነ፡፡ ይህ ታሪክ በጥሩ ሁኔታ የተገለፀው ለብሪታኒያዊው ፀሐፊ ዴቪድ ጎልድብላት ነው፡፡ ጎልድብላት በእግርኳስ ታሪክ እጅግ ዝነኛ የሆነውን ‹‹The Ball is Round›› (ኳስ ድቡልቡል ነች) የተባለ መፅሐፍ የፃፈ ደራሲ ነው፡፡ አሁን ደግሞ የብራዚልን እግርኳስ ታሪክ አስነብቧል፡፡ ለምን? ተብሎ ሲጠየቅ ደግሞ ‹‹የሆነ ሰው ሊፅፈው ስለሚገባ›› ሲል ምላሽ ይሰጣል፡፡ ከእርሱ መፅሐፍ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ታሪክ የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በፖርቹጋልኛ እንኳን ማግኘት ያስቸግራል፡፡ ‹‹ይህ መፅሐፍ መፃፍ የነበረበት በሌላ ሰው ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ በብራዚላዊ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ፖርቹጋልኛን ጠንቅቆ መናገር በሚችል›› ሲል ጎልድብላት ሃሳቡን ይሰነዝራል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የተውኔት አውራ - የሀገር ባንዴራ።

በእርግጥም በአብዛኛው በእንግሊዝኛ የተፃፉ ምንጮችን መጠቀሙ እንደ ድክመት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ነገር ግን ጎልድብላት እግርኳስን በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አውዶች ውስጥ አስገብቶ በመግለፅ ችሎታው፣ ሃሳብን በመቀመር ተሰጥኦው እና ፍሰት ባለው አተራረኩ መፅሐፉ ጠንካራ እና ሳቢ እንዲሆን አድርጓል፡፡ የመፅሐፉ አጀማመር የጨፈገገ ስሜት የሚያሳድር ቢሆንም 1950ዎቹን ሲሻገር በከፍታ የተሞላ እና አስደሳች እየሆነ ይሄዳል፡፡ በመፅሐፉ ጎልድብላት እግርኳስ እንዴት ብራዚልን ድብልቅ ሃገር መሆኗን አምና እንድትቀበል እንደረዳት ያሳያል፡፡

በ1930ዎቹ የማህበረሰብ ጥናት ሳይንቲስት የሆነው ጂልቤርቶ ፍሬይር ብራዚል የድብልቅ ዝርያዎች አገር መሆኗ የኩራት ምንጭ እንጂ የሚያሳፍር እንዳልሆነ በመግለጽ ብሔራዊ መነቃቃት ለመፍጠር እንዳልሆነ በመግለፅ ብሔራዊ መነቃቃት ለመፍጠር ሙከራ አድርጓል፡፡ በሰሜናዊ ምስራቅ በሚገኙ የስኳር እርሻዎች ውስጥ በነበረው ህይወት ላይ በሚያጠነጥነው መፅሐፉ በነጭ አሳዳሪዎች እና በጥቁር ባሪያዎች መሀል ይደረግ የነበረውን ፆታዊ ግንኙነት አወድሷል፡፡ እንደ እርሱ ገለፃ ልዩ የሆነው የብራዚላውያን ዝርያ የተገኘው በዚያ ምክንያት ነው፡፡ ፍሬደር ብራዚል የባርነት ስርዓትን ማስወገዷ እና ባሮችን እንደ አንድ ባለሙሉ መብት የአገሪቱ ዜጋ አድርጋ መቀበሏ ወደ እግርኳሱ ዳንስ፣ ብልጣብልጥነትን እና ጥበብን አምጥቷል ብሎ ያምናል፡፡ ይህም ብራዚል እንደ እንግሊዝ እና አርጀንቲናን ከመሳሰሉ የነጮች ሃገሮች የተሻለ እና ማራኪ እግርኳስ እንድትጫወት አስችሏታል፡፡ ሌሎች ብራዚላውያን ፀሐፊዎችም ሃሳቡን ደግፈውት ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩ የላቲን አሜሪካ ምሁራንም አገራቸውን ከአውሮፓውያን ጋር ከማመሳሰል ይልቅ አገራዊ ቅርሳቸውን አጉልተው ለማሳየት ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡

በመጨረሻም ፔሌ እና ጋሪንቻ ወደ መድረኩ መጡ፡፡ ያም የፍሬይርን የዘር ንድፈ ሀሳብ የሚያጠናክር ነበር፡፡ በ1958 የዓለም ዋንጫ ብራዚል አዘጋጇን ስዊድን አሸንፋ የዓለም ዋንጫውን አነሳች፡፡ ‹‹ጨዋታው ሲጠናቀቅ ተጫዋቾቹ በደስታ ሰከሩ፡፡ የስዊዲኑ ንጉሠ ነገሥት እንኳን በፈንጠዚያው ለመሳተፍ ወደ ሜዳ ገቡ›› ሲል ጎልድብላት ፅፏል፡፡ የተቀረው ዓለምም በብራዚላውያን እግርኳስ ፍቅር ወደቀ፡፡ በ1962 ብራዚል ዳግም የዓለም ሻምፒዮን ሆነች፡፡ መለስ ብለን ስንመለከት እነዚያ ዓመታት ወርቃማ ዘመናት እንደነበሩ እንገነዘባለን፡፡ ያ የሆነው በእግርኳሱ ብቻ አልነበረም፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱም ፈጣን ነበር፡፡ ከአመፅም የፀዳች ነበረች፡፡ የ1964ቱ መፈንቅለ መንግሥት የተፈፀመው ከዚያ በኋላ ነው፡፡ ምርጥ ብራዚላውያን እግርኳስ ተጨዋቾችም ወደ አውሮፓ ከማምራት ይልቅ የሚመርጡት በብራዚል መጫወትን ነበር፡፡ ልጆች እግርኳስን የሚማሩባቸው ሰፋፊ ሜዳዎች ነበሩ፡፡
በ1970 ‹‹ውቡ›› የብራዚል ቡድን የዓለም ዋንጫውን አሸነፈ፡፡ ያም አገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ዝናዋ ጫፍ ደረሰበት ወቅት ነበር፡፡ እንዳውም አንዳንዶች አሜሪካኖች ጨረቃ ላይ ካረፉበት ክስተት ጋር አነፃፅረውታል፡፡ በኋላ ላይ ወታደራዊው መንግሥት ሴሌሳኦን ለመቆጣጠር ያለው ፍላጎት እያደገ መጣ፡፡ መሐይምነት በተንሰራፋበት እና የጦርነት ልምድ በሌለው አገር ብሔራዊ ማንነትን ለማጠናከር አስቸጋሪ ሆነ፡፡ በመሆኑም አምባገነኖቹ እግርኳስ አገሪቷን አንድ አድርጎ እንዲያቆማት ፈለጉ፡፡ ካምፓማር ተመሳሳይ ነገር በሌሎቹም የላቲን አሜሪካ አገራት ተከስቷል ባይ ነው፡፡
ቢያንስ እስከ 1994 ድረስ ላቲን አሜሪካ የተቀረውን ዓለም የምትመራበት አንደኛው መድረክ እግርኳስ ነበር፡፡ የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት ልዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ደ ሲልቫ የዚህን ዓመት የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት በቁርጠኝነት መነሳታቸው የማያስገርመው ለዚህ ነው፡፡ ምክንያቱም አገሪቱን የቆዳ ስፋት ያህል ውክልና በዓለም አቀፍ መድረክ የሚያስገኝላት እግርኳስ ብቻ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ብራዚላውያን ክፍለ ዘመኑን የሚለኩት እንኳን በዓም ዋንጫው ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢሕአዴግ የአ.አ ወጣቶች ማህበር 15 አመራሩን አገደ

ምንም እንኳን ብራዚል የዓለም ዋንጫውን በ1994 እና 2002 ያሸነፈች ቢሆንም ከ1970ው ድል ጋር በጭራሽ አይወዳደሩም፡፡ እያንዳንዱ የብራዚል ቡድን ከ1970ው ቡድን ትዝታ ጋር ይላተማል፡፡ ኃላፊነቱ ድርብ ነው፡፡ የዓለም ዋንጫውን ማሸነፍ ቀዳሚው ነው፡፡ ‹‹በማራኪ ጨዋታ›› ማሸነፍ ደግሞ ሁለተኛው፡፡ ምናልባትም ብራዚል በዚህኛውም ዓመት ይህንን ማሳካቷ ያጠራጥራል፡፡ እንዳውም የብራዚል እግርኳስ መመስረት ያለበት ‹‹ጉልበት›› ላይ ወይስ ‹‹ጥበብ›› ላይ የሚለው ንትርክ አሁንም እየተደመጠ ነው፡፡ ወታደራዊው አገዛዝ እና የሴሌሳኦ አሰልጣኞች ጉልበት እና ዲስፕሊን ይመርጣሉ፡፡ አብዛኛው ደጋፊ ግን ምርጫው ውበት እና ጥበብ ነው፡፡

ብራዚል መከተል ያለባት የተደራጀ ቡድን በመገንባት የሚታወቁ ሃገራትን ሞዴል ወይስ የራሷን ፈጠራ የሚያበረታታ እግርኳስ ለሚለው ክርክር መነሻው የ1982ቱ የዓለም ዋንጫ ነው፡፡ በቶርናመንቱ ብራዚል በጣልያን ስትሸነፍ ብራዚላውያን በየጎዳናው በእንባ ተራጭተዋል፡፡ ተሸናፊው ቡድን ወደ አገሩ ሲገባም የጀግና አቀባበል አድርገውለታል፡፡ በርካታ ብራዚላውያን ከ1994ቱ አሸናፊ ቡድን ይልቅ የ1982ቱን ተሸናፊ ቡድን ይመርጣሉ፡፡
‹‹ማራኪ እግርኳስ›› ብራዚል ውበትን ለማድነቅ ያላትን ስጦታ የሚያንፀባርቅ ነበር፡፡ ከ1970 ወዲህ ያለው የብራዚል ዘመናዊ እግርኳስ ግን የሚያንፀባርቀው የብራዚል አስቀያሚነት ነው፡፡ ሃገሪቷ ድሆችን የምትይዝበትን አግባብ ያልሆነ መንገድ ተመልከቱ፡፡ ደጋፊዎች በበሰበሱ መቀመጫዎች ላይ ተቀምጠው ጨዋታዎችን ይታደማሉ፡፡ ተጨዋቾች ደግሞ ማብቂያ በሌለው የሊጉ የውድድር መርሃ ግብር ከአቅም በላይ ይለፋሉ፡፡ (ኤፍ ሲ ሳኦፖሎ በአንድ ቀን ሁለት ጨዋታዎችን ያከናወነበት አጋጣሚ አለ) በዚያ ላይ አብዛኞቹ ብራዚላውያን ተጨዋቾች የሚያገኙት ዝቅተኛ ክፍያ ነው፡፡ ያውም በወቅቱ የሚከፈላቸው ከሆነ፡፡

ሌላው በብራዚል እግርኳስ እተለመደ የመጣ ነገር ጥቃት ነው፡፡ ደጋፊዎች በየጊዜው ይገደላሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንዳውም ድርጊቱ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት በሚታዩ ጨዋታዎች ላይ ይታያል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በዋናነት ጥሬ ዕቃዎችን ወደ ውጪ በመላክ ላይ መመስረቱም ሌላው ችግር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ብራዚላውያን ተጨዋቾች በሙሉ የሚጫወቱት ባህር ማዶ ነው፡፡ ይህም በአገሪቱ ካሉ የእግርኳስ አፍቃሪያን ይነጥላቸዋል፡፡ ይህም ስሜት መራራቅ አንዳንድ ተጨዋቾች ተመፃዳቂዎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ በአንድ ወቅት ዝነኛው የግራ መስመር ተከላካይ ሮቤርቶ ካርሎስ የሮሌክስ ሰዓቱን ውድነት ለመግለፅ ‹‹የምንጓዘው በእኔ አንጓ ላይ አንድ (የብራዚል) መንደር ተሸክሜ ነው›› ማለቱን ፈርናንዶ ዱ አርቴ የተባለ ፀሐፊ ያስታውሳል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  «አዲስ አበባን አላስፈላጊ እናደርጋታለን፣ ኢትዮጵያን እንድትመቸን አድርገን እንሠራታለን፣ ብልጽግና እንዲጠቅመን አድርገን መሥርተነዋል» (ሺመልስ አብዲሳ)

በብራዚል የተንሰራፋው ሙስናም መታለፍ የሌለበት ነገር ነው፡፡ የብራዚል ክለቦችን በዘልማድ የሚያስተዳድሩት የክለብ ዳይሬክተሮች የአውሮፓ ክለቦች የመልካም አስተዳደር ምሳሌዎች እንደሆኑ አድርገው ይቀርባሉ፡፡ ከ1958 እስከ 2012 ድረስ የብራዚልን እግርኳስ ማህበር የመራው አንድ ቤተሰብ ነው፡፡ ጆአኦ ሃቫላንጅ እና አማቻቸው ሪካርዶ ቴክሲዬራ፡፡ በቅርቡ አሳፋሪ የሆነው ምስጢራቸው ከተጋለጠ በኋላ ቴክሲዬራ ብራዚልን ለቅቀው በሚያሚ ከትመዋል፡፡ ነገር ግን የሄዱት አሻራቸውን ጥለው ነው፡፡ ጎልድብላት እንደፃፈው በዓለም ዋንጫው አዘጋጅ ኮሚቴ ውስጥ መጀመሪያ ላይ ቴክሲዬራ፣ ሴት ልጃቸው፣ ጠበቃቸው እና የግል አማካሪያቸው የሆነው ሰው ይገኙበት ነበር፡፡ በወታደራዊው ዘመን የባንክ ኦፍ ብራዚል ፕሬዝዳንት የነበሩት ግለሰብም በኮሚቴው ውስጥ ተካትተዋል፡፡ ነገር ግን ከመንግሥት የተወከለ አካል አልነበረም፡፡ መጪው የዓለም ዋንጫ የቴክሲዬራ ልጅ ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ወራሻቸው ጆዜ ማሪያ ማሪንም ቢሆኑ የወታደራዊው ዘመን ንክኪ የነበራቸው ናቸው፡፡ በይበልጥ የሚታወቁት ግን በታዳጊዎች ውድድር ሻምፒዮን ለሆነ ቡድን ሽልማት በሚሰጥበት ስነ ስርዓት ሜዳልያ ሰርቀው ወደኪሳቸው በከተቱበት አጋጣሚ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ህዝቡ በእግርኳስ ማህበሩ ላይ እምነት የለውም፡፡ በቅርቡ ዳታፎልሃ የተባለ የምርምር ተቋም ባደረገው የዳሰሳ ጥናት አብዛኞቹ ብራዚላውያን የዓለም ዋንጫው ከትርፍ ይልቅ በርካታ ኪሳራዎችን እንደሚያስከትል ያምናሉ፡፡

ሁኔታዎች እንዲህ አስቸጋሪ በሆኑበት ወቅት እንኳን አንዳንድ መሻሻሎች እየታዩ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በከፊል ሊመሰገን የሚገባው እግርኳስ ነው፡፡ የብራዚል ሰቆቃ በይፋ መታየት ጀምሯል፡፡ በአብዛኛው ሰላማዊ የነበሩትና በብዛት የመካከለኛው መደብ ነዋሪዎችን ያሳተፉት በባለፈው የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወቅት የተካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎች በብራዚል ታሪክ ከትልልቆቹ ተርታ ይሰለፋሉ፡፡ ሰዎች ከአውቶብስ ትኬት ዋጋ ጀምሮ እስከ ግብረ ሰዶማዊነት ያለውን ጉዳይ በተቃውሟቸው አሰምተዋል፡፡ እንደ ጎልድብላት ገለፃ ከሆነ ግን ቁጣው እንዲጋጋል ያደረገው የዓለም ዋንጫውን ለማስተናግድ በሚደረገው ዝግጅት እየፈሰሰ ያለው የተጋነነ ገንዘብ ነው፡፡ ቴክሲዬራ ሄደዋል፡፡ በስታዲየም ተገኝተው ቡድናቸውን የሚደግፉ ደጋፊዎች ቁጥርም ቀስ በቀስ እያደገ ነው፡፡ ብራዚል በቅርብ ጊዜ እያሳየች ባለው የምጣኔ ሀብት ዕድገት ምክንያትም ወደ ውጪ ሄደው ለመጫወት የሚፈልጉ ተጨዋቾች ቁጥርም ይቀንሳል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ምንም እንኳን ከአገሪቱ 12 አዳዲስ ስታዲየሞች ግማሽ ያህሉ ጥቅም አልባ የሚሆኑ ቢሆንም ቀሪዎቹ ግን ብራዚላውያን በተሻለ ደህንነት እና ምቾት እግርኳስን እንዲመለከቱ ያደርጓቸዋል፡፡ ለጊዜው ግን የብራዚል እግርኳስ በአብዛኛው አስቀያሚ ሆኖ ይቀጥላል፡፡

1 Comment

  1. It is is a fantastic article.But it would be better if u had mentioned the source or atleast the name of the writer.Because i have read the original story written by ABEL JEBESSA on the weekly news paper “ethio sport” before you post it on this site!

Comments are closed.

Share